1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 8 2002

ሰንበቱ ለደቡብ አፍሪቃው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ቀሪዎቹን ቲኬቶች ለመቁረጥ ማጣሪያ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። እርግጥ ማጣሪያው በቀሩት አገሮች ዘንድ የፌስታና የብሄራዊ ስሜት መለያ ሆኖ ቢያልፉም በሌላ በኩል የአንዴው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በረኛ የሮበርት ኤንከ አሳዛኝ ሞትና ስንብት የጋረደው ሆኖ ማለፉም አልቀረም።

https://p.dw.com/p/KYIX
ሮበርት ኤንከ
ሮበርት ኤንከምስል picture-alliance / augenklick/Rzepka

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ማጣሪያ

በዚህ በአውሮፓ ለደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ የተካሄደው የምድብ ማጣሪያ ውድድር ሲጀምር በክፍለ-ዓለሚቱ ጠንካሮች ተብለው ከሚመደቡት መካከል የሚቆጠሩትን ፈረንሣይንና ፖርቱጋልን የመሳሰሉት፤ ምናልናትም ሩሢያን ጨምሮ በቀጥታ ማለፍ ይሳናቸዋል ብሎ ለመተንበይ የቃጣ ብዙም አልነበረም። እነዚህ አገሮች እንዲያውም የምድብ ውድድራቸውን በሁለተኝነት ባይፈጽሙ ኖሮ አሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተጨማሪ ቀዳዳ የማግኘት ዕድል ባላገኙም ነበር። ሶሥቱም አገሮች በሰንበቱ የመጀመሪያ ግጥሚያ ለማሽነፍ ሲበቁ በፊታችን ረቡዕ በሚያካሂዷቸው የመልስ ግጥሚያዎች የተሻለ ዕጣ የሚጠብቃቸው ነው የሚመስለው። ግን ላይሳካላቸውም ይችላል። ፈረንሣይ ዳብሊን ላይ አየርላንድን በደካማ አጨዋወት ለዚያውም በስንት መከራ 1-0 ስትረታ ፓሪስ ላይ የሚካሄደው የመልስ ግጥሚያ ቀላል ሽርሽር የሚሆንላት አይመስልም። የአየርላንድ ብሄራዊ ቡድን በመታገል በሚገባ የታወቀ ነው። አየርላንድ ከስምንት ዓመታት በፊት ኔዘርላንድን ያህል ታላቅ ቡድን በመጨረሻዋ ደቂቃ በማሰናከል ከዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ማስቀረቷ የሚዘነጋ አይደለም። ኢጣሊያዊው የቡድኑ አሠልጣኝ ጆቫኒ ትራፓቶኒም ከዳብሊኑ ግጥሚያ በኋላ ፓሪስ ላይ የፈረንሣይን ያህል እኩል ዕድል አለን ሲሉ ነው ትግሉ ገና እንዳላበቃ ያመለከቱት።

ፖርቱጋልም ሊዝበን ላይ ተከላካይላ ብሩኖ አልቬስ በመጀመሪያው አጋማሽ በአናቱ ባስቆጠራት ብችኛ ጎል ቦስናን 1-0 ለማሸነፍ በቅታለች። ጥያቄው ይህ ጠባብ ውጤት ለመልሱ ጨዋታ ይበቃል ወይ ነው። የቦስናው አሠልጣኝ ሚሮስላቭ ብላዤቪች በበኩሉ ከነገ በስቲያ ዜኒትሣ ላይ በሚካሄደው የመልስ ግጥሚያ ቡድኑ ውጤቱን እንደሚገለብጠው ያምናል። የመጀመሪያው ጨዋታ ድክመት አይደገምም፤ በአዲስ ስልት ፖርቱጋልን እናስደንቃለን ነእ ያለው። በዕውነትም ቢቀር በተናጠል ጠንካራ ተጫዋቾች ካሉት ከቦስና ብሄራዊ ቡድን የእስካሁኑ ማጣሪያ እንዳሳየው አስደናቂ ውጤት ሊጠበቅ የሚችል ነው። ቦስና ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለመሳተፍ ያለው ፍላጎት ወሰን የለውም። ምናልባት ጎጂ ነገር ቢኖር ሶሥት መደበኛና የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች በቢጫ ካርዶች የተነሣ ከመጪው ግጥሚያ መታገዳቸው ነው። ቢሆንም የፖርቱጋል ተጫዋቾች በጣሙን ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል።

ሩሢያ ስሎቬኒያን 2-1 ረትታለች። ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ዲኒያር ቢልያሌትዲኖቭ ነበር። ሆኖም ስሎቬኒያ ዘግየት ብላ ጨዋታው ሊያበቃ ሶሥት ደቂቃዎች ሲቀሩ በውጭ ያስቆጠረቻት ጎል በፊታችን ረቡዕ የመልስ ግጥሚያ ላይ ወሣኝ ተጽዕኖ ሊኖራት ይችላል። በጠቅላላ ውጤት ወደ ፍጻሜው ለማለፍ ለስሎቬኒያ 1-0 ድል የሚበቃ ሲሆን ሁኔታው ለሩሢያ በአንጻሩ እፎይ የሚያሰኝ አይደለም። የስሎቬኒያ ዕድል ገና አላከተመም ማለት ነው። በአራተኛውና በመጨረሻው የአውሮፓ መለያ ግጥሚያ ግሪክና ኡክራኒያ እዚህ ግባ በማይባል ጨዋታ ባዶ-ለባዶ ተለያይተዋል። የኡክራኒያ ቡድን በአቴን ኦሎምፒያ ስታዲዮም ቢቀር በመከላከል ታክቲኩ ጥቂት ሻል ያለ ሆኖ ሲታይ በተቀረ ግሪክ እንዳለፈው ቅዳሜ አጨዋወቷ ቦታውን ለሌሎች ብትተወው ባልከፋ ነበር። ከነገ በስቲያ ምሽት ዶኔትስክ ላይ በመንፈስ ይበልጥ የጠነከረ ከባድ የኡክራኒያ ቡድን የምጠብቃት ነው የሚመስለው። በአውሮፓው ማጣሪያ ቀደም ሲል በቀጥተኛው ማጣሪያ ዘጠኝ አገሮች ለደቡብ አፍሪቃው ፍጻሜ ሲያልፉ በሣምንቱ አጋማሽ አራቱ ታክለው በጠቅላላው 13 ይሆናሉ።

የአውሮፓ ሁኔታ ከሞላ ጎደል ይህን የመሰለ ሲሆን ኒውዚላንድ በእሢያና በኦሺኒያ መለያ ባሕሬይንን ከመጀመሪያው ባዶ-ለባዶ ውጤት በኋላ በመልሱ 1-0 በመርታት በጥቅሉ ለደቡብ አፍሪቃው ፍጻሜ ደርሳለች። ኒውዚላንድ ለፍጻሜ ስትደርስ ከ 17 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። ይህም ደስታውን እጥፍ-ድርብ ያደርገዋል። ከአካባቢው አውስትራሊያ ቀደም ብላ ማለፏን ማረጋገጧ ይታወቃል። ሰንበቱ በደቡብ አሜሪካና በኮንካካፍ (ሰሜንና ማዕከላዊ አሜሪካ) አካባቢም የመጨረሻውን የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመለየት በኮስታ ሪካና በኡሩጉዋይ መካከል የመጀመሪያው ግጥሚያ የተካሄደበት ነበር። የደቡብ አሜሪካው ምድብ አምሥተኛ ኡሩጉዋይ የኮንካካፉን አራተኛ ኮስታ ሪካን በአገሩ 1-0 ስትረታ በፊታችን ረቡዕ ሞንቴቪዲዮ ውስጥ ለሚካሄደው የመልስ ግጥሚያ አመቺ ሁኔታን ፈጥራ ተመልሳለች። ለሁለት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኡሩጉዋይ በ 22ኛዋ ደቂቃ ላይ ወሣኟን ጎል ያስቆጠረው ዲየጎ ሉጋኖ ነበር።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ካሜሩንና ናይጄሪያ ከበድ ካለ የማጣሪያ ሂደት በኋላ በዓለም ዋንጫው ፍጻሜ አስተናጋጇን ደቡብ አፍሪቃን፣ ጋናንና አይቮሪ ኮስትን ሊቀላቀሉ በቅተዋል። ካሜሩን ሞሮኮን 2-0 ስታሸንፍ ናይጄሪያም ያለፈችው ናይሮቢ ላይ ኬንያን ከኋላ ተነስታ 3-2 ከረታች በኋላ ነው። ናይጄሪያ በዚሁ ባለፈው ውድድር ከተሰናከለች በኋላ እንደገና ለዚያውም በአፍሪቃ ምድር ወደ ዓለም ዋንጫው መድረክ ለመመለስ በቅታለች። ለካሜሩን ደግሞ መጪው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ስድሥተኛው ሲሆን ይሄም በአፍሪቃ ራሱን የቻለ ክብረ-ወሰን ነው። ከሁለት አንዷንና ወሧኛን ጎል ያስቆጠረው ዝነኛው አጥቂ ሣሙዔል ኤቶ ሲሆን በቴሌቪዥን ጨዋታውን የተከታተሉት አባቱ ዴቪድ ኤቶ ከእንግዲህ የሚያልሙት በቡድኑ የዓለም ዋንጫ ባለቤት መሆን ላይ ሆኗል።
“የኛ ልጆች ለፍጻሜው እንደሚያልፉ ሁሌም አውቅ ነበር። ጥሩ ጨዋታ ነው ያሳዩት፤ ከተጠበቀው በላይ። አሁን የሚቀራቸው የዓለም ዋንጫዋን ወደ ካሜሩን ማምጣት ብቻ ነው።

በእፍሪቃው ማጣሪያ በግብጽና በአልጄሪያ መካከል ለመጨረሿዋ ቦታ የሚካሄደው ትግል ውሣኔ በአንጻሩ በይደር ማለፉ ግድ ሆኖበታል። ለዚህም ምክንያቱ ሁለቱ ቡድኖች ካይሮ ላይ ካካሄዱት ግጥሚያ ውጤት በኋላ በምድባቸው ውስጥ በነጥብም በጎል ልዩነትም እኩል መሆናቸው ነው። በካይሮው ግጥሚያ ግብጽ ገና በሁለተኛው ደቂቃ ላይ 1-0 ብትመራም መደበኛው ሰዓት አልፎ አምሥት ደቂቃዎች እስከተቆጠሩ ድረስ አልጄሪያ ለድል ተቃርባ ነበር። ሆኖም ሞሐመድ አቡትሪካ ባስቆጠራት ሁለተኛ ጎል ግብጽ ከመንቀጥቀጥ ባሕር ወጥታ እንደገና ነፍስ ልትዘራ ችላለች። ከአፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ አገሮች የመጨረሻው ማን ይሆናል? ግብጽ ወይስ አልጄሪያ! በፊታችን ረቡዕ ሱዳን ውስጥ ይለይለታል።

የዓለም ዋንጫን ተሳትፎ ካነሣን ይሄው ሕልሙ ዕውን ሳይሆንለት ባለፈው ሣምንት ሕይወቱን በራሱ ያሳለፈው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በረኛ ሮበርት ኤንከ ይገኝበታል። ከሁለት ዓመት በፊት ተሥፋው ብሩህ ነበር።

“ለኔና ብሄራዊ ተጫዋች ለሆኑ ሁሉ፤ ለጀርመኖች ብቻ ሣይሆን ደግሞ ለሌሎችም ጭምር አስደሳቹና ታላቁ ነገር ነው። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በበረኝነት ለመሰለፍ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ”
ያሳዝናል፤ ሕልሙ ሕልም ብቻ ሆኖ መቅረቱ! ለዚሁ በመንፈስ ነክ ሕመም ሲሰቃይ ከቆየ በኋላ በአሳዛኝ ሁኔታ ላለፈው ስፖርተኛ በክለቡ በሃኖቨር-96 ስታዲዮም ትናንት ከአርባ ሺህ ሕዝብ በላይ በተገኘበት ታላቅ ስንብት ተደርጎለታል። በዓለም ዙሪያ በተካሄዱ የተለያዩ ግጥሚያዎች በየቦታው የደቂቃ የሕሊና ጸሎት መደረጉም የኤንከ አሟሟት ከጀርመን ባሻገር ብዙዎችን ምን ያህል እንዳሳዘነ የሚያሳይ ነው። ሟቹ ሮበርት ኤንከ ድክመት ማሳየት አስቸጋሪ በሆነበት በፕሮፌሺናሉ የስፖርት መድረክ ላይ ከታላቅ ግቡ ለመድረስ ስቃዩን በድብቅ ይዞ ብዙ መከራውን ማየት ነበረበት። ሕይወቱን እንዲያሳልፍ ያደረገውም ይሄው በይፋ ድክመቱ እንዳይታይ ያደረበት ፍርሃት ነው። የጀርመን እግር ኳስ ፌደሬሺን ፕሬዚደንት ቴዎ ስቫንሲገር በስንብቱ ሥነ-ሥርዓት ወቅት ባሰሙት ንግግር ልጆቻቸውን በእግር ኳስ ለማራመድ የሚሹ ወላጆች ሁሉ ይህን መሰሉ ሁኔታ እንዳይደርስ ሰብዓዊ ሁኔታዎችን እንዲያጤኑ ነበር ያስገነዘቡት።

“እግር ኳስ ሁሉም ነገር ሆኖ መታየት የለበትም። ልጆቻችሁ አንዴ ብሄራዊ ተጫዋች ሊሆኑ ይችላሉ ብላችሁ በምታስቡበት ጊዜ ስለዚህ ስፖርት በመገናኛ አውታሮች የሚቀርበውን ሽፋኑን ብቻ አትመልከቱ። የሰውልጅ ፍርሃቻና ድክመትን የተላበሰ ፍጡር መሆኑም መዘንጋት የለበትም”

የሮበርት ኤንከ ቀብር በስታዲዮም የተካሄደው ሥነ-ሥርዓት እንዳበቃ በዚያው በሃኖቭር ተፈጽሟል። ላለፈው ቅዳሜ ከቼሌ ጋር ታቅዶ የነበረውን የወዳጅነት ግጥሚያ በሃዘኑ የተነሣ የሰረዙት የብሄራዊ ቡድን ባልደረቦቹ በመጪው ረቡዕ ከአይቮሪ ኮስት ይጫወታሉ። ያለፈው አለፈ፤ ሕይወት ግን ትቀጥላለች። በተቀረ በዓለም ዙሪያ በተካሄዱት የወዳጅነት ግጥሚያዎች ብራዚል እንግሊዝን 1-0 ስትረታ፤ ከብዙ በጥቂቱ ስፓኝ ከአርጄንቲና 2-1፤ ኢጣሊያ ከኔዘርላንድ 0-0፤ ስሎቫኪያ ከዩ.ኤስ.አሜሪካ 1-0፤ ደቡብ አፍሪቃ ከጃፓን 0-0፤ ዌልስ ከስኮትላንድ 3-0፤ እንዲሁም ፖላንድ ከሩሜኒያ 0-1 ተለያይተዋል።

ጥሩነሽ ዲባባ አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዘገበች

የቤይጂንግ ኦሎምፒክ የአምሥትና አሥር ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ጥሩነሽ ዲባባ ሰንበቱን ኔዘርላንድ ውስጥ በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር አዲስ የ 15 ኪሎሜትር ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ በቅታለች። ጥሩነሽ ያሻሻለችው ሰሥት ዓመት ተኩል ያህል ጸንቶ የቆየውን የጃፓኗን አትሌት የካዮኮ ፉኩሺን ክብረ-ወሰን ነው። በወንዶች ሩጫ ደግሞ ስለሺ ስሂኔ ሲያሽንፍ የኡጋንዳው ኒኮላስ ኪፕሮኖ ሁለተኛ ሆኗል። ከዚሁ ሌላ ዮኮሃማ ላይ በተካሄደ ዓለምአቀፍ የሴቶች ማራቶን ሩጫ ሩሢያዊቱ ኢንጋ አቢቶቫ አሸናፊ ሆናለች። ኪዮኮ ሺማሃራ ከጃፓን ሁለተኛ፤ እንዲሁም ካትሪን እንዴሬባ ከኬንያ ስሥተኛ ስትሆን ከኢትዮጵያ ሮቤ ጉታ ደግሞ ሩጫውን በስድሥተኝነት ፈጽማለች። ለማጠቃለል የፓሪስ-ማስተርስ የቴኒስ ውድድር ደግሞ በሰርቢያው ኮከብ በኖቫክ ጆኮቪች አሸናፊነት ተፈጽሟል። ጆኮቪች በስድሥት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ሶሥተኛው ለሆነው የፍጻሜ ድል የበቃው የፈረንሣይ ተጋጣሚውን ጌል ሞንፊልስን 3-1 በሆነ ውጤት በመርታት ነው።

DW/RTR/AFP

MM/HM