የስደተኛ አስተርጓሚዎች
ዓርብ፣ ነሐሴ 29 2007በአሁኑ ሰዓት በአውሮፓ እጅግ አነጋራሪ እና አሳሳቢ የሆነው የስደተኞች ጉዳይ ነው። ሠሞኑን ጀርመን የሚገቡት አብዛኞቹ ስደተኞች ፤ የሶርያ እና የአፍጋኒስታን ዜጎች ሲሆኑ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ከመካከላቸው አልጠፉም። እነዚህ ስደተኞች እዚህ ሀገር ሲገቡ እና ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው አስተርጓሚ ያስፈልጋቸዋል።
ዳንኤል ተሰማ፤ በምዕራብ ጀርመን - የኮሎኝ ከተማ ነዋሪ ነው። በሙያው ምግብ አብሳይ ሲሆን በትርፍ ጊዜው ደግሞ ወደ ጀርመን ለሚገቡ ስደተኞች በአማርኛ አስተርጓሚነት ያገለግላል። ላለፉት 14 ዓመታት ጀርመን ቤቱ የሆነችው ዳንኤል ፤ ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ለስደተኞች በአማርኛ ቋንቋ ከሚያስተረጉሙ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ነው። የዮንቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ቤተል እንደሻውም በትርፍ ጊዜዋ ትተረጉማለች። ጀርመን ሀገር 13 ዓመት ያስቆጠረችው ቤተል «አውስሌንደር ዓምት » በመባል ከሚጠራው የውጭ ዜጎችን ጉዳይ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት አልፎ አልፎ የስልክ ጥሪ ይደርሳታል።
ዳንኤል መተርጎም ከጀመረ አምስት ዓመት ገደማ ሆነው። እሱም ይሁን ቤተል የሚተረጉሙት አልፎ አልፎ ነው። ሁለቱም ወጣቶች ሲተረጉሙ ትልቁ ፈተናቸው የሚሰሙትን ታሪክ በትክክል መተርጎሙ ሳይሆን፤ የስደተኞቹ ችግር ውስጣቸው መቅረቱ ነው።ከዚያ ባለፈ ግን ፤ ያለ ክፍያ ርዳት ለሚፈልጉ ስደተኞች ድጋፉን እየለገሰ እንደሆነ ዳንኤል ይናገራል።
ዳንኤል ጊዜ ካለው ከሚኖርባት ከተማ ኮሎኝ በአቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች እየተዘዋወረ ይተረጉማል። አንዳንዴ ፤እንደ ቤተል አስተርጓሚዎች በአካል መገኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ደግሞ መስሪያ ቤቱ በስልክ እንዲተረጉሙላቸው ይጠይቃል።
ጀርመን ለገቡ ስደተኞች በአማርኛ ቋንቋ ስለሚያስተረጉሙ ሁለት ወጣቶች የስራ ተሞክሮ የበለጠ ከድምፅ ዘገባው ያገኛሉ።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሐመድ