1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሲየራ ሊዮን ችሎትና፧ በጦር ወንጀለኛነት ጥፋተኞች ሆነው የተገኙት 3 ሰዎች፧

ሐሙስ፣ ሰኔ 14 1999

በሲየራ ሊዮን የተቋቋመው በጦር ወንጀለኛነት የተከሰሱ ሰዎችን የሚመረምረውና የሚዳኘው ፍርድ ቤት፧ በትናንት ችሎቱ፧ ቀድሞ የሚሊሺያ ጦር አዛዦች የነበሩ፧ ሦስት ሰዎች፧ በግድያ፧ አስገድዶ በመድፈርና የሲቭሎችን አካላት በመቆራረጥ፧ ጥፋተኞች ሆነው መገኘታቸውን አስታወቀ።

https://p.dw.com/p/E0as
ጠብመንጃ ያነገበ የ 11 ዓመት ልጅ፧ የሴራሊዮን የትናንት እውን ታሪክ፧
ጠብመንጃ ያነገበ የ 11 ዓመት ልጅ፧ የሴራሊዮን የትናንት እውን ታሪክ፧ምስል AP
ለአቅመ-አዳምና ለአቅመ-ሔዋን ያልደረሱ ልጆችን ለውትድርና በመመልመልም ረገድ ጥፋተኞች መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል። የተጠቀሱት ወንጀሎች የተፈጸሙት፧ እ ጎ አ በ 1991 እና በ 2002 ዓ ም መካከል ነው። ይሁንና «ጥፋተኞች አይደደለንም« በማለት የሚከራከሩት ሦስት ተከሳሾች፧ በሀምሌ ወር መጀመሪያ ሳምንት ፍጻሜ ላይ፧ ብይን ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። የዶቸ ቨለ ባልደረባ Meike Scholz የላከችውን ዘገባ፧ ተክሌ የኋላ፧ እንደሚከተለው ያቀርበዋል።
(ድምጽ...ከፍርድ ቤት)
ምርመራው ሁለት ዓመት ወስዷል። 60 ያህል ምሥክሮች ቃላቸውን ሰጥተዋል። በዛ ያሉ ሰነዶች ተመርምረዋል። የጠበብት ቃልም ተደምጧል። ይህን መሠረት በማድረግ ችሎት የተቀመጡት ዳኞች ሦስቱን ተከሳሾች ጥፈተኞች ሆነው አግኝተዋቸዋል። ዋና ከሳሽ፧ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ካሪም ካን አጋ፧
«ክሱ፧ በቀረቡ አያሌ መረጃዎች መሠረት፧ ሦስቱን ተከሳሾች፧ አሌክስ ታምባ ብሪማ፧ ብሪማ ካማራንና ሳንቲጊ ካኑን በግል ወንጀል በመፈጸም ረገድ ጥፋተኞች፧ ኀላፊነትም ያለባቸው ሆኖ አግኝቷቸዋል።«
የዓይን ምሥክሮች እንዳስረዱት፧ እ ጎ አ በ 1990 ኛዎቹ ዓመታት፧ የታየ የጭካኔ ተግባር ነበር። ዝርፊያ፧ አስገድዶ መድፈር፧ ተፈጽሟል። ህጻናት በህይወት እንዳሉ ወደ እቶን እሳት እየተወረወሩ እንዲቃጠሉ ተደርጓል። ወንዶች ወጣቶች ለውትድርና ልጃገረዶች ለወሲብ ባርነት ወይም ግድያ ይዳረጋሉ። ቀድሞ፧ የጦር ኀይሎች አብዮታዊ ምክር ቤት(AFRC)ይባል የነበረው የአማጽያኑ ቡድን አባል፧ ወንጀል መፈጸሙን አምኖ በመቀበል እንዲህ ነበረ ለፍርድ ቤቱ ያብራራው።
«በግድ የያዝናቸውን ልጆች በመጨረሻ ለውጊያ አሠልጥነናቸው ነበር። በአህጽሮት SBU ማለት Small Boys Units/የትንንሽ ወንዶች ልጆች ቡድን/ ነበረ የምንላቸው። እነዚህን ልጆች፧ የሰዎችን እጅና እግር እንዲቆርጡ እናዛቸው ነበር። ይህን ሲያደርጉም በመሃላቸው ተገኝቼ ተመልክቼአለሁ።«
ብሪማ፧ ካማራና ካኑ ሦስቱም ተከሳሾች፧ የረጅም ጊዜ እሥራት ሳይበየንባቸው አይቀርም። ብያኔ የሚሰጠው ሐምሌ 9 ቀን 1999 ዓ ም ሲሆን፧ ከብዙዎቹ ከቀድሞዎቹ አማጽያን በተለየ ሁኔታ እነዚህ ሦስቱ፧ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ ያስተላልፉ ስለነበረና የእርስ በርሱ ጦርነትም እንዲጀመር ያደረጉ በመሆናቸው፧ ይበልጥ ተጠያቂዎች መሆናቸው ነው የሚነገረው።
ችሎቱ በመካሄድ ላይ እንዳለም አንል የጦር ሠራዊቱ መኮንን፧.....
«እነዚህ ሰዎች መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱ በመሆናቸው ተጠያቂዎች ናቸው!« ሲሉ ጮኸዋል።
እ ጎ አ በ 1997 ዓ ም፧ የሲየራ ሊዮንን መንግሥት በኃይል ያስወገዱ፧ በመጨረሻም፧ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ፧ እጅግ ይፈራ ከነበረው አብዮታዊ የአንድነት ግንባር ይባል ከነበረው የአማጽያን ቡድን ጋር በመተባባር ይሠሩ ነበር። ዋናው ክስ መሥራች፧ ዐቃቤ ህግ አጋ።.....
«ዓላማቸው፧ ሽብርን ማዛመትና የማይደግፋቸውን ሲቭሉን ህዝብ መቅጣት ነበር።«
ችሎት የተቀመጡት ዳኞች፧ ተከሳሾቹ ከቀረቡባቸው ባለ አሥራ አራት ነጥብ ክሶች፧ በአሥራ አንዱ ጥፋተኞች ሆነው መገኘታቸውን እንደገለጡ፧ በተለይ ለጋ ወጣቶችን በማስገደድ በውትድርና በማሠማራት ጥፋተኞች ናቸው በመባሉ ጭምር የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፧ ረክተዋል። ይኸው የትናንቱ ችሎት፧ በእጅግ ታዋቂው ተከሳሽ በቀድሞው የላይቤሪያ መንግሥት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴይለር ላይ ወንጀሉን ሳያከብድባቸው እንደማይቀር ተመልክቷል። የሲየራ ሊዮንን አማጽያን በመደገፍ ጭምር የተከሰሱት፧ ቴይለር በፀጥታ ችግር ሳቢያ ለምርመራ የቀረቡት በደን ኻኽ ነው። በቀድሞዎቹ አማጽያን ብሪማ ካማራና ካኑ ላይ የሚተላለፈው ብይን በቴይለርም ላይ ሳይፈጸም እንደማይቀር ይገመታል።