የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አሜሪካ ጠየቀች
ቅዳሜ፣ ሰኔ 8 2011አሜሪካ በሱዳን እንደ ጎርጎርያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2 ቀን 2019 ዓ.ም. የተከሰተው ግድያ እና ሌሎች ወንጀሎች ምንጩ ምን እንደሆነ ለጊዜያዊ ወታደራዊ ምክር ቤቱ በትክክል የተከሰተው ምን እንደሆነ ፣ ለምን እንደተከሰተ ፣ ትዕዛዙን የሰጠው ምን እንደሆነና ምን ያህል የጉዳቱ ሰለባዎች እንዳሉ ለመለየት ነጻ እና ተአማኒነት ያለው ምርመራ እንዲደረግ ማሳወቋን የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቲቦር ናጊይ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በሱዳን የተወሰኑ የጥቃቱ ሰለባዎችን እንዳነጋገሩ የገለጹት ባለስልጣኑ ሰዎች ከመገደላቸው በላይ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ብዙዎች ተደብድበዋል ለሌሎች አስደንጋጭ ጥቃቶችም ተጋልጠዋል ብለዋል።በመሆኑም የሚደረገው ገለልተኛ ምርመራ በድርጊቱ የተሳተፉት ሁሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። ከሰኔ 2 2019 በፊት ሱዳናውያኑ በመጨረሻም ከ35 አመታት በኋላ ነገሮች በጎ መስመር ያዙ የሚል ተስፋአድሮባቸው እንደነበር አውስተው ሆኖም ይህ ተስፋ በነጋታው ተንኖ እንደጠፋ እና ወደ እልቂት መሻገሩን አመልክተዋል።
ይህ ይሆናል የሚል ምንም ምክንያትም ሆነ መነሻ እንዳልነበረም ተናግረዋል። ከጊዜያዊ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ፤ አለም በችግር እና ፈተና ውስጥ መሆኑ እየታወቀ ሱዳን ላይ ለምን ይህን ያህል ትኩረት ተደረገ የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው ጠቅሰው ይህ ሁኔታ ነገሩን በተለየ መልኩ እንዲያስቡ እንዳደረጋቸውም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቲቦር ናጊይ አክለውም በሌሎች ሃገሮች እንደሚስተዋለው ወታደሮች በንጹሃን ላይ ጥፋት አድርሰው ነጻ መሆናቸውና ሟቾችም ደመ ከልብ ሆነው መቅረታቸው ሀቅ በመሆኑ ይህ ነገር በሱዳን በተከሰተው ግድያ እንደማይታይ እና አጥፊዎች ከምርመራ ውጤት በኋላ ተጠያቂ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን እለለብን ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ