1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን የሰላም ዉይይት መታጎል

ማክሰኞ፣ ጥር 17 2008

በሱዳን መንግሥትና በታጣቂዉ የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጭ ንቅናቄ ሰሜን « SPLM-N» መካከል በበርሊን ጀርመን ላይ የተካሄደዉ ይፋዊ ያልሆነዉ የሰላም ድርድር ያለ ስኬት ተጠናቆአል። ይህን ተከትሎ ሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በሱዳን ደቡባዊ አካባቢ ለሚገኙት ነዋሪዎች ርዳታን የማድረሱ ሂደት ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም።

https://p.dw.com/p/1HkG4
Afrika Südsudan Südkordofan Flüchtlinge
ምስል Cap Anamur

[No title]

« በዓለም አቀፉ ሕግጋቶች መሠረት፣ ተቀናቃኝ ቡድኖች በሚገኙበት ክልል የሚኖሩ ሰዎች ለረኃብ እንዳይጋለጡ ማድረግ የግድ ነው።» ይላሉ ጀርመን ገቲንገን ከተማ የሚገኘው ለተጨቆኑ ሕዝቦች የሚሟገተው ድርጅት «Gesellschaft für bedrohte Völker» ተጠሪ ኡልሪኽ ዴልዩስ። ግን እንዳለመታደል ሆኖ፣ ሱዳንን ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በሚገኙት በደቡብ ኮርዶፋን በብሉናይል ግዛቶች የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ይህ መሆኑን ነው ዴልዩስ ያስታወቁት። በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓ,ም በሕዝበ ዉሳኔ ነፃነትዋን ያገኘችዉ የደቡብ ሱዳን ተዋሳኝ በሆኑት በነዚሁ ግዛቶች የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እጎአ ከ2012 ዓ,ም ወዲህ በይፋ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ ርዳታ ደርሶአቸው አያዉቅም።

Eröffnung der Friedensgespräche zum Nordsudan in Addis Abeba
ምስል Cap Anamur

በእነዚህ ሁለት የሱዳን ግዛቶች ለቀጠለው ቀዉስ መፍትሔ ለማስገኘት ባለፈዉ ሳምንት በርሊን ጀርመን ላይ ይፋዊ ያለሆነ የሰላም ድርድር የተካሄደ ሲሆን፣ በድርድሩ የደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጭ ንቅናቄ ሰሜን «SPLM-N » ዋና ጸሐፊ ያሲር አርመን፤ የሱዳን መንግሥት፤ እንዲሁም፣ የአፍሪቃ ሕብረት ተወካዮች ተገኝተዋል። ምንም እንኳ የተቀናቃኞቹ ወገኖች ተደራዳሪዎች ለመፍትሄ ፍለጋው «ግልጽነት » አስፈላጊ መሆኑን ቢናገሩም፣ ዉይይቱ ያለምንም ውጤት ነዉ የተጠናቀቀዉ። ከዚህ ቀደም ሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች ለይፋዊ ድርድር አስር ጊዜ ቢገናኙም፣ ሰላም ላይ የሚያደርሳቸዉ ነጥብ ላይ ግን መድረስ አልቻሉም። ከዚያ በመቀጠል ከአንድ ወር ግድም በፊት አዲስ አበባ ላይ፣ ሰሞኑን ደግሞ በርሊን ላይ ቢደራደሩም ለውጤት ሳይበቁ ቀርተዋል። የበርሊኑ የሰላም ድርድር ውጤታማ ይሆናል በሚል ተስፋ ተጥሎ እንደነበር ለተጨቆኑ ሕዝቦች የሚሟገተው ድርጅት ተጠሪ ኡልሪኽ ዴልዩስ ገልጸዋል።

«ይህን ይፋዊ ያልሆነ ውይይት ወደ ይፋዊ የድርድር ሂደት የማራመድ ተስፋ አድሮ ነበር። የሚያሳዝነዉ ግን እነዚህ ግምቶችና ተስፋዎች እዉን ሊሆኑ አልቻሉም። ይህ ደግሞ ዉዝግብ በበዛባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩት ሰዎች መሪር ገሀድ ሆኖዋል።»

Karte Sudan Blauer Nil Süd-Kordofan mit Südsudan
ምስል DW

ከጎርጎረሳዉያኑ 2011 ዓም ጀምሮ በደቡባዊ ፊደራል ኮርዶፋን ግዛትና በብሉ ናይል የሚታየዉ ጦርነት እንደቀጠለ ነዉ። በአንድ በኩል እንደ ደቡብ ሱዳን ነፃ አዉጭ ንቅናቄ ሰሜን « SPLM-N » የመሳሰሉ ታጣቂ ተቀናቃኝ ቡድኖች ሲገኙ በሌላ ወገን ደግሞ የሱዳን ጦር ሰራዊትና ለመንግሥት ቅርበት ያላቸዉ አማፅያን ይዋጋሉ። አማፅያኑ ሙስሊሙንና ዓረብ ዘመሙን የካርቱም ማዕከላዊ መንግሥትን አይቀበሉም። ለዉጥረቱና ጦርነቱ ከረጅም ጊዜ ወዲህ የሚያወዛግቡት የመሬትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች በመንስዔነት ይጠቀሳሉ።

እንደ ተመድ ዘገባ፣ የሱዳን መንግሥት ዉጥረት በሚታይባቸዉ ቦታዎች ሁሉ የሰብዓዊ ርዳታ ሰጭዎች ወደ ቦታዉ እንዳይገቡ ያሰናክላል። ለተጨቆኑ ሕዝቦች የሚሟገተው ድርጅት ተጠሪ ጀርመናዊዉ ኡልሪኽ ዴልዩስ እንደገለፁት የመንግሥት ወታደሮች አብያተ ክርስትያናትን፤ የሐኪም ቤቶችንና፤ የገበያ ቦታዎችን በቦምብ ይደበድባሉ።

« በሲቪል ማኅበረሰቡ ላይ የሚደረግ ይህ ዓይነቱን የሽብር ጥቃት በመፈፀም፤ አማፅያንኑ በሚንቀሳቀሱባቸው ክልሎች ያሉት ነዋሪዎች መንግሥት ወደሚቆጣጠረዉ ክልሎች እንዲመጡ ለማድረግ የታሰበ ነዉ።»

የሱዳን መንግሥት ፍላጎት ለቁጥጥር እንዲያመቸዉም የርዳታ ቁሳቁሶችን በራሱ ክልል እንዲያልፍ ነዉ የሚፈልገዉ። ምክንያቱም ከርዳታ ቁሳቁስ ጋር የጦር መሳርያ ያልፋል የሚል ስጋት ስላለዉ እንደሆን ተመልክቶአል።

Afrika Südsudan Südkordofan Flüchtlinge
ምስል DW/G. T. Haile-Giorgis

ከጎርጎረሳዉያኑ 1993 ዓ,ም ጀምሮ ስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት አልበሽር መንግሥታቸዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትችትና ወቀሳ ዉስጥ እንደሆን ይታወቃል። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ተመልካች ፍርድ ቤትም አልበሽር በዳርፉሩ ቀዉስ፤ በዘር ማጥፋት፥ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ በተፈፀመ ወንጀልና በጦር ወንጀል የእስር ማዘዣ አስተላልፎ በቁጥጥር ለማዋል ጥረቱን እንደቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።

የሱዳን ውዝግብን ለማብቃት የአፍሪቃ ኅብረት የጀመረውን ጥረት የሚደግፈዉ የጀርመን መንግሥት ተቀናቃኝ ቡድኖች የሚደራደሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስፈልጉ አንዳንድ ቴክኒካው የምክር እገዛዎችን እንደሚያደርግ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።

ቴሬዛ ክሪኒንገር / አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ