1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ንግግር

እሑድ፣ ታኅሣሥ 28 2005

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በድንበራቸዉ ላይ ከጦር ነጻ የሆነ የጋራ ክልል ለማስፈንና የነዳጅ ዘይት ዉላቸዉን ገቢር ለማድረግ መስማማታቸዉን አስታወቁ። ይህ የተገለጸዉ የሁለቱ መንግስታት ፕሪዝደንቶች በዚህ ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተዉ ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ነዉ።

https://p.dw.com/p/17EvS
ምስል KHALED DESOUKI/AFP/Getty Images

የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንቶች የነዳጅ ዘይት ሃብትንና የጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ በቆየ ውዝግባቸው ንግግራቸውን ለመቀጠል ባለፈው ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል። ሁለቱ መንግሥታት ባለፈው መስከረም ከወታደራዊ ሃይል ነጻ የሆነ የድንበር ክልል ለመፍጠርና እንዲሁም በሌሎች በርከት ባሉ ነጥቦች ሲስማሙ የውሉ ገቢር መሆን ገና እየተጠበቀ ነው። የደቡብ ሱዳን ዋና ተደራዳሪ ፓጋን አሙም ፕሬዚደንታቸው መላውን አወዛጋቢ ችግሮች በመፍታት ተሥፋ ወደ ጉባዔው መጓዛቸውን አዲስ አበባ ላይ አስረድተዋል። የጁባው ተደራዳሪ አያይዘው እንደገለጹት ፕሬዚደንት ሣልቫ ኪር ከሱዳኑ የሥልጣን አቻቸው ከኦማር-አል-ባሺር የሚያካሂዱት ንግግር የድንበር ጉዳዮችንና የአከራካሪዋን ግዛት የአብዬይን ዕጣም የሚጠቀልል ነው። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ከሰባት ዓመታት በፊት የሰላም ውል ካሰፈኑ ወዲህ ድንበር መካለል ተስኗቸው ቆይተዋል። ፓጋን አሙም አንዳስታወቁት ሁለቱ ወገኖች በአዲስ አበባው ንግግር መስማማት ካቃታቸው የሚቀረው አማራጭ ችግሩን በዓለምአቀፍ አማካዮች በኩል መፍታት ነው። በአፍሪቃ ሕብረት ጥላ ሥር በቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት በታቦ እምቤኪ አማካይነት የሚደረገው ንግግር በሚቀጥሉት ቀናት ቀጥሎ እንደሚሰነብት ይጠበቃል። ባለፈዉ ሰምወን የደቡብ ሱዳን ፕሪዚደንት ሳልቫኪር ከሱዳኑ አቻቸዉ ከፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አል በሽር ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን የደቡብ ሱዳን መንግስት ሜኒስቴር መስርያቤት ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቦ ነበር። ፕሪዚደንት ሳልቫኪር በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረገዉን የነዳጅ ዘይት ዝዉዉር እና ዉዝግብ ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸዉ የተሰማዉ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አል በሽር ከደቡብ ሱዳኑ አቻቸው ሳልቫ ኪር ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን ካስታወቁ በኋላ ነበር። ሳልቫ ኪርና አል በሽር ባለፈዉ መስከረም ወር አዲስ አበባ ውስጥ ከጦር ነፃ የሆነ ድንበር ለመከለልና የነዳጅ ዘይት ሽያጭም እንዲቀጥል ተፈራርመው እንደነበር ይታወሳል። የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ለሁለቱም አገሮች ኤኮኖሚ መሰረት መሆኑ ሲታወቅ፤ ሁለቱም ሱዳኖች በድንበሮቻቸዉ አቅራብያ አማፅያንን በመደገፋቸዉ እየተወቃቀሱ፤ ዉላቸዉ ላይ እንደ ቅድመ ግዴታ የተቀመጠውን ጦራቸውን ከጋራ ድንበራቸው አካባቢ ማስወጣቱን ሁለቱም አገራት እስከ ዛሬ ተግባራዊ አላደረጉም። ደቡብ ሱዳን 350 ሺህ በርሚል የሚጠጋ ዕለታዊ የነዳጅ ዘይት ሃብት ምርቷን ይዛ ፤ ለዉጭ ገበያ በሱዳን በኩል ለማቅረብ በተጠየቀችዉ ክፍያ ባለመስማማቷ፤ ባለፈው ጥር ወር፤ የነዳጅ ዘይት ንግዷን ማቋረጧ ይታወሳል። በያዝነዉ ሳምንት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ የሁለቱን ሱዳን ፕሪዚደንቶች ለመሸምገል ጁባንና ካርቱምን መጎብኘታቸዉ ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን ፖሊቲካ ውስጥ ጉልህ የአደራዳሪነት ሚና ስትጫወት ይታያል። በሁለቱ ሀገራት መካከል እየተካሄደ የነበረውን የፖሊቲካ ሽኩቻን ይፈታል ተብሎ በታመነው የመስከረሙ የአዲስ አበባ ድርድር፤ ኢትዮጵያ ዋና አደራዳሪ ነበረች። ምክንያቱ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሁኔታ በኢትዮጵያ ጸጥታ ላይ ተጽዕኖ ስላለው ነው ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ መናገራቸዉ ይታወሳል።

አዜብ ታደሰ

መስፍን መኮንን