የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ቃጠሎ አልቆመም
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 5 2011በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ወደ 400 ሔክታር መሬት አጥፍቷል። የእሳት ቃጠሎው በተለይ ዋልያ እና ጭላዳ ዝንጀሮ በሚገኙባቸው የፓርኩ ክፍሎች መድረሱን ወደ ቦታው የተጓዘው ሰለሞን ሙጬ ዘግቧል። አስታ እና ወጨኒ የተባሉ የዛፍ አይነቶች፤ የጓሳ ምድር፤ የወፍ ጎጆዎች እና የአይጥ ዝርያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የአማራ ክልል እና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ባለሥልጣናት የእሳት ቃጠሎውን መቆጣጠር እንዳልተቻለ ወደ ቦታው ላቀናው የጋዜጠኞች ቡድን ተናግረዋል። ከደቡብ አፍሪቃ ወይም ከኬንያ በውሰት ይመጣሉ የተባሉት የእሳት ማጥፊያ ሔሊኮፕተሮች ጉዳይ ገና መቋጫ አላገኘም።
በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ባለፈው መጋቢት 19 በተመሳሳይ ሁኔታ የተነሳው እሳት ለሳምንት ያህል ቆይቶ ጠፍቷል። በወቅቱም ከ342 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል መቃጠሉን ኃላፊዎች ገልጸው ነበር፡፡ በፓርኩ ላይ የእሳት ቃጠሎው እንደገና ያገረሸው ባለፈው ሰኞ መጋቢት 30 አመሻሽ ላይ ነው።
በዚህ አመት ብቻ የባሌ ብሔራዊ ፓርክ፤ ሀላይደጌ አሰቦት ብሔራዊ ፓርክ ተመሳሳይ ቃጠሎ ደርሶባቸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲህ አይነቱን ቃጠሎ አስቀድሞ ለመከላከል ሆነ ለማጥፋት የዜጎችን ትብብር ሲጠይቅ ከርሟል። ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮቿን ለመጠበቅ ቸልተኛ ሆናለች ሲል ይወቅሳል።
ዘገባዎቹን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ