የራድዮ አሰና የሳተላይት ሥርጭት መቋረጥ
ሐሙስ፣ የካቲት 26 2007
ራድዮ አሰና ላለፉት 6 ዓመት ከለንደን በዋነኛነት ወደ ኤርትራና አካባባቢዋ እንዲሁም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን የሚያስተላለፍ ጣቢያ ነው ። የጣቢያው መሥራችና ዋና አዘጋጅ አቶ አማኑኤል ኢያሱ ጣቢያው የግል ፕሬስ በሌለባትና የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ብቻ በሚደመጥባት ኤርትራ የተሟላ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እንዲያገልግል ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።
ይህን ዓላማ ይዞ በአጭር ሞገድ በሳምንት ሰወስቴ-ለየ-አንድ ሰዓት፤ ሳምንቱን በሙሉ ለ24 ሰዓታት በሳተላይትና በድረገፅ ደግሞ በየቀኑ የአንድ ሰዓት ስርጭቱን ሲያስተላልፍ የቆየው ራድዮ አሰና ካለፈው እሁድ አንስቶ በሳተላይት ማስተላለፉን አቁሟል ። አቶ አማኑኤል እንደተናገሩት ምክንያቱ የገንዘብ እጦት ነው ።
የቀድሞ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት አቶ አማኑ ኤል እንደሚሉት የራድዮ አሰና የሳተላይት ሥርጭት ብዙ አካባቢዎችን የሚያዳርስ ነበር ። በተለይ ኤርትራ ለሚገኙ አድማጮች የተለየ ጠቀሜታም ነበረው ።
ለጣቢያው ሳይሰለቹ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩ ሰዎችን ደግሞ ደጋግሞ ማስቸገሩ ስለከበደን የሰተላይት ስርጭቱን ለማቋረጥ ተገደናል የሚሉት አቶ አማኑኤል የተጠናከረ ድጋፍ ከተገኘ ግን ስርጭቱ የማይቀጥልበት ምክንያት አይኖርም ይላሉ ።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ