1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሥነ-ቃል ውርስ

ሐሙስ፣ ጥር 16 2011

ሥነ-ቃል የአንድ ማህበረሰብ መገለጫ ነው ይሉታል። ተረት፣ ተረትና ምሳሌ፣ እንቆቅልሽ፣ እንካ ሰላንቲያ የኢትዮጵያዊያን ባህል ሆኖ፤ ቤተሰብን የሚያቀራርብ፣ ግብረ ገብን የሚያስተምር ፣ ታሪክን ማውረሻ መንገድ ፣ እንደመዝናኛም ይታያል።

https://p.dw.com/p/3C8Qe
Alexander von Humboldt Büchersammlung (Timothy Rooks)
ምስል Berlin-Brandenburgische Akademie der Wissenschaften/Foto: T. Rooks

የሥነ-ቃል ውርስ

በከተሞች ከደበዘዙት ባህሎች ሥነ -ቃል አንዱ ነው ሲባል ይደመጣል፤ በዘመኑ ቴክኖሎጂ ልጆች ባህላቸውን እንዳይወርሱ ተጽዕኖ ፈጥሯል፤ የባህል መወራረሱም ክፍተት ተፈጥሯል የሚሉ እሳቤዎች ይነገራሉ። ሥነ-ቃል ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የህብረተሰብ ሀብት ነው ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒበርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህል አካዳሚ የአማርኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ መስፍን መሰለ። “ሥነ -ቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የራሱ መከወኛ አጋጣሚ ያለው ሲከወን ደግሞ ግጥሙን የሚደረድር ወይም ተረቱን የሚተርክ ወይም እንቆቁልሹን የሚጠይቅ፤ የሚጠየቅ ተረቱ ሲወራ የሚያዳምጥ፤ ግጥሙ ሲደረደር የሚቀበል፤ በባህላዊ ልብሶችና በባህላዊ መሳሪያ ሊታጀብ የሚችል፤ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የአንድ ህብረተሰብ ሀብት ነው።” የህብረተሰቡን የህይወት ክንዋኔ ይገልጻል፤ የባህል መገለጫም ሆኖ እንደሚያገለግል ያስረግጣሉ። ተጽእኖ እንዳለ ሆኖ  ሙሉ ለሙሉ ግን ባህሉ ላይ ተመስርቷል ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ። በከተማ ሥነ ቃሉ ተቀይጦም ያለ ቢሆንም በህብረተሰቡ ዘንድ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝ፤ ከከተማው በበለጠ ግን በገጠሪቱ ክፍል የሥነ -ቃል ዘርፉን አለቀቀም ሲሉ አቶ መስፍን ይጠቅሳሉ። “ሥነ ቃሉ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ክንዋኔ የሚገልጽ ነው። የሚገልጸውም የህብረተሰቡን አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ እርስ በርሱ ያለውን ግንኙነት ይገልጻል።” የሥነ -ቃል ከትውልድ ትውልድ መወራረሱ ቀድሞ እንደነበረው ሳይሆን በተለየ ሁኔታ ሊተላለፍ ይችላል፤ ሊቋረጥም ይችላል ይሉናል፤ ግን በተለየ መልክ ይቀጥላል፤ የሚወራረሰውም ሥነ -ቃል ለውጥ አለበት ይሉናል።  ሥነ -ቃል ለአንድ ማህበረሰብ ዛሬም ሀብት ሆኖ ያገለግላል ሲሉ አቶ መስፍን ይገልጻሉ። “ዛሬ ላይ ሥነ -ቃል በከተማ በገጠርም እንዴት ይተላለፋል ብለን ስንመረምር ድሮ ከነበረው የተለወጠ ነገር ልናገኝ እንችላለን። ሥነ -ቃል በአንድ ወቅት የነበረው አገልግሎት አይቋረጥም ማለት አይደለም። ሊቋረጥ ይችላል፤ በተለየ መንገድ ግን አገልግሎቱ ሊቀጥል ይችላል።” ልጆች ባህላቸው ባእድ የመሆኑ ችግር በገዘፈ ሁኔታ አለ የሚሉት ወ/ሮ ሰተቴ ገ/ሀና ናቸው። የውጭ መረጃ ብዙውን ሲያውቁ፤ ሀገር በቀል የሆኑ ባህሎቻቸውን ግን አያውቁም ሲሉም ችግሩ የጎላ እንደሆነ ይናገራሉ። “ልጆች ለባህላቸው ባእድ ናቸው። በውጥ መገናኛ ብዙሀን ስለሚወጡ ነገሮች መረጃ ያውቃሉ። ባህሎቻቸውን አያውቁም።” አቶ ሚሊዮን ዘውዴ ወሰኔ 32 አመታት በመምህርነት አገልግለዋል። በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሁፍ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ዘዴ ላይ የማስተርስ ትምህርታቸውን ሰርተዋል። ሥነ-ቃል ተለዋዋጭነት ባህሪ አለው ይሉናል አቶ ሚሊዮን። ሥነ--ቃል አደጋ አጥልቶበታል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። “ሥነ -ቃልን ስናየው የተለዋዋጭነት ባህሪ አለው። በጊዜ፣ በቦታ፣ በምክንያት እንዲሁም በአቀራረብ ስልት ከዋኙም የሚቀያይረው ነገር ይኖራል። ይሁን እንጅ ተለዋዋጭነቱን አሁን የምናየው አይነት መልክ አልነበረም። የሥነ -ቃል የመጥፋት የመረሳት ነገር እየታየበት ነው ያለው።” ሥነ -ቃል የመማማሪያ መድረክ ነው ይላሉ አቶ ሚሊዮን። ማንነት ማጣት ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው፤ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል። ትውልዱ ባህሉን ማወቅ መምጣት አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

 

ነጃት ኢብራሂም 

ማንተጋፍቶት ስለሽ