1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚሎሰቪች ሞት ያስከተለዉ ጥርጣሬ

ሰኞ፣ መጋቢት 4 1998

ባለፈዉ ቅዳሜ ዕለት በአገሩ አቆጣጠር ከንጋቱ 3 ሰዓት ላይ ነበር የሰርቢያና የዩጎዝላቪያ ፕሬዝደንት የነበሩት ስሎቦዳን ሚሎሰቪች በተባበሩት መንግስታት እስር ቤት ክፍላቸዉ በምትገኘዉ አልጋቸዉ ላይ ሞተዉ የተገኙት።

https://p.dw.com/p/E0ix
ስሎቦዳን ሚሎሰቪች
ስሎቦዳን ሚሎሰቪችምስል picture-alliance/dpa

ሚሎሰቪች ህይወታቸዉ ያለፈዉ በልብ ህመም ሳቢያ መሆኑም በሄጉ ፍርድ ቤት ተነገረ። በአስከሬኑ ላይ ከተደረገ ምርመራ በኋላ ግን አንዳንድ ትችቶች ከአካባቢዉ እየተሰነዘሩ ነዉ። ይኸዉም ሰዉየዉ ተመርዘዋል፤ እንዲሁም የጦር ወንጀለኞችን የሚዳኘዉ ዓለም ዓቀፍ ችሎት ሚሎሰቪች ተገቢዉን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም በሚል።
የችሎቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ወይዘሮ ትናንት ማምሻዉን ለጋዜጠኞች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ብቅ ብለዉ ነበር።
«ሀኪሞች እንዳረጋገጡት ስሎቦዳን ሚሎሰቪች የሞቱት በልብ ህመም ሳቢያ ነዉ። ሁለት ዓይነት የልብ ህመም ችግር ነዉ ሀኪሞቹ ያገኙባቸዉ። እነዚህ ችግሮች ሳይሆኑ አይቀርም ለህልፈት ያበቋቸዉ። የአቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት የፍርድ ቤቱን አስተዳደር በማነጋገር ተመርዘዋል የሚባለዉን ለማጣራት ጠንካራ ክትትል እያደረገ ነዉ። የመጨረሻ የምርመራዉ ዉጤት በተቻለ መጠን በቅርቡ ይፋ ይሆናል።»
የ64 ዓመቱን የሚሎሰቪችን አስከሬን ቀደም ብለዉ የኔዘርላንድና የሰርቢያ ህጋዊ ባለሙያዎች በሚገባ በሽታ ካለ በሚል መርምረዉታል።
ጥርጣሬንና ሊፈፀም የሚችል ማንኛዉንም ግድፈት ለማስወገድ ሲባልም ምርመራዉ በካሜራ ተቀርጿል።
ምክንያቱም ዜና ህልፈታቸዉ ከተሰማበት ቅዳሜ ዕለት ጀምሮ በርካታ ጥርጣሬና ጭምጭምታዎች ተናፍሰዋል።
እሁድ ዕለትም የሚሎሰቪች ጠበቃ ዜዲንኮ ቶማኒቪች በበኩላቸዉ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዲህ ነበር ያሉት
«ከጥቂት ቀናት በፊት አንድ አዲስ ሰነድ ደርሶኛል። በግልፅ እንደሚታየዉ ባለፈዉ ጥር 4 ዓ.ም ከባድ መድሃኒቶች እንዲወስዱ ተደርገዋል። ዘገባዉ እንደሚያሳየዉ እነዚህ መድሃኒቶች ለስጋ ደዌና ለሳንባ ህመም ብቻ የሚወሰዱ ናቸዉ።»
ቶማኒቪች የሚሏቸዉ እነዚህ መድሃኒቶች ሚሎሰቪች የደም ግፊታቸዉን ለመቀነስ ይወስዱት የነበዉን መድሃኒት ጥቅም አልባ አድርገዉታል።
ትችቱም ቢሆን የምርመራ ዉጤቱ ዘገባ ገና ይፋ ሳይሆንም ቀጥሏል። ዋናዉ ጥያቄም መድሃኒቶቹን ለሚሎሰቪች የሰጣቸዉ ማን ነዉ፤ ወይም ደግሞ የሚያስከትለዉን ችግር እያወቁ ራሳቸዉ ናቸዉ ወይ የወሰዱት የሚለዉ ነዉ።
ለረዥም ዓመታት በከባድ ወንጀል ተከሰዉ የፍርድ ሂደታቸዉ ይጠበቅ የነበረዉ እኝህ ሰዉ በተባበሩት መንግስታት እስር ቤት ሳሉ ራሳቸዉን በአደገኛ መድሃኒት መርዘዋል።
ምናልባትም ሚሎሰቪች አጋጣሚዉ ሞስኮ ተወስደዉ የተሻለ ህክምና ለማገኘት ሲሉ አድርገዉት ይሆናል።
ፍርድ ቤቱ ከጥቂት ወራት በፊት ይህን መሰሉን ጥያቄ ዉድቅ አድርጎት ነበር። በአንድ ወቅት ኃያል የነበሩት የሚሎሰቪች ሞት ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ላይ ለተነሳዉ የዉሳኔ ትችት ጠቅላይ አቃቤ ህጓ ካርላ ዴል ፖንቴ በሰጡት አስተያየት ተገቢ ነዉ ይላሉ
«የወንጀል ችሎቱ በትክክል ወስኗል። ሚሎሰቪች እዚህ የሚያስፈልጋቸዉን የህክምና እርዳታ አግኝተዋል። ሲጎበኟቸዉና ሲያማክሯቸዉ የነበሩትን ባለሙያዎቹንም መዘንጋት የለብንም። በእአሱ ምርመራ ዉጤት መሰረትም የሚያስፈልጋቸዉን የህክምና እርዳታ እዚሁ ስለሚያገኙ ራሺያ መሄድ እንደማያስፈልጋቸዉ ተረግጋጧል።»
የሚሎሰቪች ባለቤትና ወንድ ልጃቸዉ ቀደም ብለዉ ሩሲያ ገብተዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ግለሰቦች ሃላፊነቱን መዉሰድ አልፈለጉም።
ምናልባትም እሳቸዉ እዚያ ከገቡ በኋላ አይመለሱም ከሚል ስጋት ተነስተዉ ሊሆን ይችላል የተቃወሟቸዉ።
ለሞታቸዉ ምክንያት ምን እንደገጠማቸዉ ግልፅ ባይሆን የሟቹ አስከሬን ዛሬ ለቤተሰቦቻቸዉ ተሰጥቷል።
ሚሎሰቪች ከሌላዉ ነገር በተጨማሪ በቦስኒያ በዘር ማጥፋት ወንጀል ስለተከሰሱም በብሄራዊ ደረጃ የቀብር ስርዓታቸዉ አይፈጸምም።
የሰርቢያዉ ፕሬዝደንት ቦሪስ ታዲክ ይህን አልተቀበሉትም። በሚሎሰቪች ላይ የተመሰረተዉ ክስ ሂደት አራት ዓመታት አስቆትሯል ከበርካታ ወራት በኋላም ያበቃል ተብሎ ነበር።