የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሹ ድርድር ውጤት
ሰኞ፣ ጥቅምት 10 2007የግድቡ ግንባታ ያስነሳውን ውዝግብ በውይይት የተነሱት አጀንዳዎች፣ የድርድሩ ውጤቱ እና ቀጣይ ሂደትን ምን ይመስላል?
ሶስቱ ሀገራት ባለፈው መስከረም በካርቱም፣ ሱዳን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የግድቡ ግንባታ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ትልቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ የሚያጠና አንድ ዓለም አቀፍ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ይታወሳል። ኮሚቴው ከተቋቋመ ወዲህም ሶስቱ ሀገራት ተገናኝተው ምክክር ሲያደርጉ ያለፈው ሳምንቱ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር። ከኢትዮጵያ 10 ያህል ልዑካንን ይዞ ወደ ካይሮ የተጓዘው ቡድን ከሁለቱ ሀገራት ጋር በአራት አጀንዳዎች ላይ መወያየቱን በውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የወሰን እና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ተሾመ አጥናፌ ገልጸውልናል።
በዚህ ስብሰባ ፤ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሰባት ዓለም አቀፍ አማካሪዎች ተመርጠዋል። በተጨማሪም የተደረሱትን ውጤቶች አቶ ተሾመ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።
ለሁለት ሙሉ ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ሶስቱም ሀገራት ባነሱዋቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ቢደርሱም፣ ግብጽ የግድቡ ግንባታ ከወንዙ የምታገኘውን የውሃ ፍሰት ይቀንስብኛል በማለት አሁንም ስጋት እንዳላት ነው የምትገልጸው። ያም ቢሆን ግን ኢትዮጵያ በጀመረችው እና አሁን ወደ 40 በመቶ ያህሉ የተጠናቀቀውን የህዳሴ ግድብ ግንባታን እንደምትቀጥልበት አስታውቃለች። የአሁኑ የሶስትዮሽ ድርድር በዚሁ የኢትዮጵያ አቋም ላይ ሳይሆን፣ በተለይ የግድቡ ግንባታ ሊያስከትላቸው በሚችላቸው ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ላይ በይበልጥ ያረኮረ ነበር አቶ ተሾመ እንዳስረዱት።
በትልቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረው የሶስትዮሹን ውይይት ሂደትን በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የግብፅ እና የሱዳን ተወካዮች ከአንድ ወር ከ 10 ቀን በኋላ ካርቱም ላይ ለግምገማ ስብሰባ ይገናኛሉ።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ