1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሁለት ጀርመኖች ግጥሚያ

ሐሙስ፣ ሰኔ 19 2006

ዛሬ ማምሻዉን በጉጉት ከሚጠበቁት ዉድድሮች አንዱ በጀርመን እና በዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል የሚካሄደዉ የእግር ኳስ ግጥሚያ ነዉ። የብዙዎችን ዐይን ወደ ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንዲያተኩር የሚያደርገዉ ደግሞ በምናባዊ ትንታኔ በሁለት የጀርመን ቡድኖች መካከል የሚደረግ ፉክክር መምሰሉ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1CQlG
ምስል Reuters

ዩናይትድ ስቴትስ በእግር ኳስ ያን ያህል የሚነገርለት ቡድን አልነበራትም። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቡድኑ ተጠናክሮ በርካታ ደጋፊዎችን ከዚያዉ ይበልጥ ለቅርጫት ኳስና ለአሜሪካን ፉትቦል እንዲሁም ቤዝቦል ፍቅር ካለዉ አድናቂ መዉሰድ ችሏል። በዛሬዉ ዕለት ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን የሚያደርገዉ ግጥሚያም ለራሱ ህልዉና ብቻ ሳይሆን ለደጋፊዎቹም ወሳኝ እንደሆነ እየተነገረ ነዉ። የአሜሪካን ቡድን በመጀመሪያ ከጋና ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት 16 ሚሊዮን የአገሬዉ ህዝብ በቴሌቪዝን ተመልክቶለታል፤ ዉጤቱም ድል ነበርና ባለፈዉ እሁድ ከፖርቱጋል ሲጋጠም ወደ 24,7 ሚሊዮን አሜሪካኖች አሰፍስፈዉ በዚያዉ መስኮት አዩት። ዛሬ ደግሞ ከሁለቱም ቀን የሚበልጥ ተመልካች እንደሚኖረዉ ይጠበቃል። በዚህ አጋጣሚም የእግር ኳስ እነዚያን ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ተወዳጅ የአሜሪካን ስፖርቶች ገፋ አድርጎ በዜጎቹ ልብ ለመግባት መሠረት እንደጣለ ተነግሯል።አሰልጣኙ ዩርገን ክሊንስማን የቀድሞ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና አሰልጣኝ የነበረ ብቻ ሳይሆን እሱ ይጫወት በነበረበት ወቅት የጀርመን ቡድን አንዴ የዓለምን ሌላ ጊዜ ደግሞ የአዉሮጳ ሻምፕዮንን ዋንጫ ወስዷል። በተጫዋችነት በጀርመን፣ በጣሊያን፣ ፈረንሳይና ኢንግላንድ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ ቡድኖች ተጫዉቷል። ሁለት ጊዜም የጀመርን አንድ ጊዜ ደግሞ የእንግሊዝ የዓመቱ የእግር ኳስ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል። 2006, ጀርመን የዓለም ዋንጫን ስታስተናግድ ክሊንስማን አሰልጣኝ ነበር። ያኔ ቡድኑን ለፍፃሜ ያደረሰዉ ይኸዉ አሰልጣኝ ዛሬም እሱ ይዟቸዉ የቆዩ ተጫዋቾችን ነዉ አዲስ ባሰለጠነዉ የአሜሪካን ቤድን የሚያጋጥመዉ። እናም ብዙዎች እንደሚሉት ስለጀርመኖች አጨዋወት ዉስጥ አዋቂ ነቱ በዚህ ግጥሚያ ቡድኑን የተሻለ ተፎካካሪ አድርጎ ሊያቀርብ ይችላል። ተጫዋቾቹ ቅዳሜ ዕለት ከጋና እኩል ለእኩል የተለያየዉ የጀርመን ቡድን ካገኘዉ የእረፍትና የዝግጅት ጊዜ በአንድ ቀን ያነሰ ቢያገኙም ለዛሬዉ ጨዋታ ዝግጁነታቸዉን እየተገለፁ ነዉ። በሌላ በኩል ጀርመኖች የጣሊያንና የስፓኝ ቡድኖች በመጀመሪያዉ ዙር መሰናበት የእድል በር እንደከፈተችላቸዉ ነዉ የሚገመተዉ። ቡድኑ እሁድ ዕለት በጠንካራ ፉክክር ከተገዳደረዉ የጋና ቡድን አቻ ወጥቷል። በመጀመሪያ ጨዋታዉም ፖርቱጋልን 4 ለባዶ አሰናብቷል። ለዛሬዉ ግጥሚያም የሚቻለዉን ሁሉ ለማድረግ ተዘግጋጅቷል ይላል የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ሜሱት ዚል፤

Fußball Deutschland Nationalmannschaft Jogi Löw Mesut Özil
ምስል Alexander Hassenstein/Bongarts/Getty Images
Trainer Jürgen Klinsmann
ምስል picture-alliance/ZB

«USA እንደምንም ማለፍ እንደምትፈልግ ማየት ይቻላል። በአቋምና በሰዉነት ጠንካሮች ናቸዉ፤ በዚያ ላይ የመሮጥ ከፍተኛ ዝግጁነት አላቸዉ። ጨዋታ ላይ ከምር ሳይሆን 90 በመቶ ብቻ ጥንካሬ ብናሳይ አሜሪካኖቹ ምን ያህል አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ እናዉቃለን። ነገር ግን ራሳችንን በመመልከት አሰልጣኛችን የሚጠብቅብንን ተግባራዊ ካደረግን ዩናይትድ ስቴትስንም እናሸንፋለን።»

ዚል እንዳለዉም የአሜሪካን ቡድን ባለፉት ሁለት ጨዋታዎችን በትክክልም ጥንካሬና ብቃቱን አሳይቷል። ወደቀጣይ ጨማዋታዎች ለማለፍም ቡድኑ ተወዳጁንና ጠንካራዉን የጀርመን ቡድን ለማሸነፍ መስራት ይኖርበታል። በዛሬዉ ጨዋት ጀርመንና የዩያንትድ ስቴትስ ቡድኖች መሸናነፍ ብቻ ሳይሆን እኩል ለእኩል መዉጣትም ሁለቱንም ለቀጣይ ግጥሚያ የመሳተፊያዉን በር አይዘጋባቸዉም። ይህን ያስተዋሉ አንዳንዶች ከወዲሁ ትችት መሰንዘር ይዘዋል፤ ይህን አስበዉ ጥሩ ፉክክር የሌለበት የእንካ ለእንካ ጨዋታ ሊያሳዩ ይችላሉ በሚል።በዚህም ምክንያት የጀርመንና የዩናይትድ ስቴትስ ቡድን የዛሬዉ ግጥሚያ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ነዉ። ከዚህ በተገናኘ ግን የጀርመን የቀድሞ የእግር ኳስ ታሪክ መዝገብ መገላበጥ ተጀምሯል በጎርጎሪዮሳዊዉ 1986 በስፓኟ የወደብ ከተማ ጊኾ በኦስትሪያና ጀርመን መካከል የተካሄደዉ ጨዋታ የማይረሳ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነዉ። በዚህ ወቅት ሁለቱ ቡድኖች አልጀሪያ እንዳታልፍ ለማድረግ ማለፋቸዉን ሲያረጋግጡ ላለመሸናነፍ የማይረባ ጨዋታ አሳይተዉ ወጥተዋል። አሁንም በዚህ በዘንድሮዉ ግጥሚያ ጋናን ለመጣል የጀርመንና ዩናይትድ ስቴት ቡድኖች ይህን ይደግሙ ይሆን ወይ የሚለዉ ቅድመ ትንበያ በተለይ የጀርመን ተጫዋችና አሰልጣኙ ላይ እየቀረበ ነዉ። እንዲህ ያለዉ ነገር እንዳይደገም እንደሚሻ ያመለከተዉ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮአኺም ለቭ ዓላማዉ ማሸነፍ ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተናግሯል።

Bundestrainer Joachim Löw
ምስል picture-alliance/dpa
Jürgen Klinsmann und Joachim Löw bei der WM-Auslosung
ምስል picture alliance/AP Photo

«በዚህ ዉድርድ ለመቀጠልና ለፍፃሜ ለመድረስ የምንፈልግ ከሆነ እንዲህ ያለዉ ሃሳብ ቦታ አይኖረዉም። እናም ማንኛዉንም ተጋጣሚ ማሸነፍ ይኖርብናል። ለዚህም ነዉ ምን ሊከተል ይችላል ብለን ማስላትና መገመት የማንፈልገዉ እናም ለእኛ ወሳኝ የሚሆነዉ ቡድኑን ማሸነፍ ብቻ ነዉ። ያንን ነዉ የምንፈልገዉ እናም ነዉ በግልፅ የተቀመጠ ግባችን፣ መጫወት ማሸነፍ፤ ይህንን ነዉ ከምር መምወሰድ የምንፈልገዉ።»

አሰልጣኝ ለቭ እንዳለዉ ቡድኑ በጥሩ ጨዋታ የተሳካ ዉጤት ይዞ ከወጣ እና በጥንካሬዉ ከቀጠለ በአሜሪካን አካባቢ በተሰናዳዉ የዓለም ዋንጫ ዋንጫዉን ይዞ ወደቤቱ የሚገባ የመጀመሪያዉ ቡድን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ግምት እየተሠነዘረ ነዉ። ጎረቤት ተቀናቃኙ የኔዘርላንድ ቡድን ሳይረሳ።

የእግር ኳስ ጨዋታ ብዙም ትኩረት በማይሰጥበት በአሜሪካ ለዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በተለይም ለአሜሪካንና ለጀርመንና ብሄራዊ ቡድኖች የእግር ኳስ ጨዋታ የተሰጠው ቦታ ምን ይመስላል ? ስለጀርመናዊው አሰልጣኝ ዩርገን ክሊንስማንስ አሜሪካውያን ምን ይላሉ የዋሽንግተን ዲሲውን ወኪላችንን አበበ ፈለቀን በስልክ አነጋግረነዋል ።

ሸዋዬ ለገሠ

አበበ ፈለቀ

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ