1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀምቡርግና የባህር ዳር ዩንቨርስቲዎች ስምምነት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 7 2007

« ጀርመን በነበርኩበት ጊዜ መዲና በርሊን ላይ በሴሜቲክ ቋንቋዎች በተለይ በግዕዝ ላይ ልዩ ጥናትን አድርጌ ሶስተኛ ዲግሪዬን ጨርሼ ነዉ ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት። ጀርመን ዉስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ይሰጣል። ሀምቡርግ ከተማ ዉስጥ በሚገኘዉ ዩንቨርስቲ በአፍሪቃ ጥናት ስር የኢትዮጵያ ጥናት ቋንቋ ይሰጣል።

https://p.dw.com/p/1GEnR
Kooperationsvertrag zwischen der Universität Hamburg und der Universität Bahirdar
ምስል Tesfaye Shiferaw

የሀምቡርግና የባህር ዳር ዩንቨርስቲዎች ስምምነት

በዚህ ጥናት ስር ታድያ የትግርኛ ፤ የአማርኛ የግዕዝ አልያም በሌሎች ቋንቋዎች ላይ ለየት ያለ ጥናት እና ምርምር አድርጎ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪን ማግኘት ይቻላል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን ይህ እስካሁን የለም፤ ገና አልተጀመረም። »
በግዕዝ ትምህርት የከፍተኛ ትምህርታቸዉን በጀርመን ያጠናቀቁት፤ ዶክተር ሙሉቀን አንዷለም የሰጡን አስተያየት ነዉ።

Kooperationsvertrag zwischen der Universität Hamburg und der Universität Bahirdar
ምስል Tesfaye Shiferaw

ባለፈዉ ሰሞወን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞአል። ሁለቱ ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት በተለይ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህል ጥናት ላይ በጋራ ለመሥራት ነዉ ያቀዱት። በዚህ ዝግጅታችን የሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎቹ በጋራ የመስራት ፋይዳ ምን እንደሆነ የሚነግሩንን የሁለቱን ተቋማት ባልደረቦች በእንግድነት ይዘናል።
ኢትዮጵያና ጀርመን ዘመናት የተሻገረ የሁለትዮሽ ግንኙነት በመካከላቸዉ የመሠረቱ ሃገራት መሆናቸዉ በመረጃዎች የተመዘገበ ነዉ። የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት፤ በታሪክ፤ በባህል ጥናትና ምርምር፤ እንዲሁም በዲፕሎማስያዊ ዉልን ከተፈራረሙም ከ 100 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩ ዘገባዎች ያሳያሉ።

በጀርመን የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ከፍተኛ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት ትምህርት ይሰጣል፤ ምርምርም ይካሄዳል። ባለፈዉ ሰምወን የሀምቡርግ ዩንቨርስቲ ባህር ዳር ከሚገኘዉ ዩንቨርስቲ ጋር የትብብር ሥራን ለመጀመር ዉል ተፈራርሞአል። ከሀምቡርግ ዩንቨርስቲ የአፍሪቃ ቋንቋዎች ጥናት ምሑር ከዴኒስ ኖስኒትሲን ጋር ወደ ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ዉሉን ለመፈራረም የተጓዙት በሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ የእስያና የአፍሪቃ ጥናት ተቋም መምህርና ተመራማሪ ጌቴ ገላዬ እንደገለፁት ይህን እድል ያገኙት ተወዳድረዉ አሽንፈዉ ነዉ።


« መጀመርያ DAAD ማለት የጀርመን መረሃ-ግብር ልዉዉጥ ማስታወቅያ አዉጥቶ በተቋማችን ስም ተወዳድረን አሸንፈን ነዉ። ይህ የዉድድር መረሃ-ግብር የነበረዉ አንድ የጀርመን ዩንቨርስቲ ከሌሎች ከዉጭ ሃገር ካሉ ዩንቨርስቲዎች በተለይ ከሶስተኛ ዓለም ሃገራት ጋር ዩንቨርስቲዎች ጋር ጥናትና ምርምርን የተማሪዎችን ልዉዉጥ በተመለከተ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል እቅድ ነዉ። እናም በዚህ መሰረት ይህን የዉድድር መረሃ-ግብር ባለፈዉ መጋቢት ወር ላይ አመልክተን፤ ከሀንቡርግ ዩንቨርስቲ ከፍተኛ ተጠሪዎች ብዙ የድጋፍ ደብዳቤዎችን ጨምረን ካስገባን በኋላ ተመርጠንና አሸንፈን ነዉ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ የበቃነዉ።»

Kooperationsvertrag zwischen der Universität Hamburg und der Universität Bahirdar
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn


በጀርመን የከፍተኛ ተቋም በግዕዝ ትምህርትና ምርምር ሶስተኛ ዲግሪያቸዉን የያዙት ዶክተር ሙሉቀን አንዱዓለም በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ዩንቨርስቲ የዓባይ ባህልና ልማት ጥናት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ናቸዉ። ከጀርመንዋ ከተማ ሀምቡርግ ጋር በተደረገዉ የትብብር ዉል መደሰታቸዉን ገልፀዋል።


«ጀርመን ዉስጥ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች፤ በኢትዮጵያ ባህል ላይ ብዙ ጥናትና ምርምር ይደረጋል። ጀርመናዉያን ስለኢትዮጵያ ታሪክ ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋ ብዙ ሥራን ነዉ የሰሩት። በተለይ በግዕዝ ቋንቋ ላይ ብዙ ነገሮችን ነዉ የሰሩት ። የግዕዙ ሀገር ኢትዮጵያ ሆኖ ሳለ ጀርመን እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ የትምህርት ማዕረግ ይሰጣል። ታድያ ይህ ነገር ለምንድን ነዉ? ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ፤ ኢትዮጵያ ላይ የማይሰጥበት ምክንያት ለምንድን ነዉ? ይህን ነገር ማሳደግ አለብን፤ ይህን ነገር ማሳደግ አለብን የሚል ሀገራዊ መንፈስ ይዘዉ ነዉ፤ በሁለቱ ዩንቨርስቲዎች መካከል ግንኙነት ፈጥረን ለምን አብረን አንሰራም ብለዉ ነዉ ከሀንቡርግ ዩንቨርስቲ ወደ ባህር ዳር የመጡት። ኢትዮጵያ ዉስጥ በግዕዝ ቋንቋ ላይ የመጀመርያ ዲግሪ እንኳ የሚሰጥበት ነገር የለም እስካሁን»

በባህር ዳር ዩንቨርስቲ የሥነ- ሰብ ማለት የሂዩማኒቲስ ተቋም ዲን ዶክተር ስዩም ተሾመ ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ከሀምቡርግ ዩንቨርስቲ ጋር የፈፀመዉ የሥራ ዉል በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይም ሆነ በሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት እጅግ ጠቃሚ ነዉ።


« በባህር ዳር ዩንቨርስቲ ማለት እኛ ጋር በተለይ በሁለተኛና በሶስተኛ ዲግሪ፤ ጀርመን ዉስጥ ያለ ልምድ አለ እኛ ጋርም ያሉ ልምዶች አሉ፤ ይህን በባህሉም በቋንቋዉም እያዳበርን ከሄድን የሁለቱም ሃገሮች ግንኙነት የበለጠ እየተጠናከረ ይሄዳል ብለን እንገምታለን። ይህ ብቻ ሳይሆን ጥናቶችንም በጋራ ማካሄድ እንችላለን፤ በባህል ዘርፍም እንዲሁም ስልጠናንም በተመለከተ ፤ እንዲሁም በሁለቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የተማሪዎችም ሆነ የመምህራንን ልዉዉጥ ማድረግ የሚቻልበት ይሆናል። ይህ ከሆነ ደግሞ የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል ብለን እንገምታለን። »

Mutter und Sohn Tannasee Baher Dahr Äthiopien
ምስል Tesfaye Shiferaw


ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ሂዩማኒቲስ የሚለዉ ቃል ሥነ-ሰብ የሚለዉ ቃል በደንብ ስለማገልፀዉ ሂማኒቲስ ፋኩልቲ ቢለዉ መርጦአል። ግን በዚህ ተቋም የሚሰጠዉ ትምህርትስ ምን ይሆን? የተቋሙ ዲን ዶክተር ስዩም ተሾመ በዚህ የትምህርት ክፍል ይላሉ፤ « በዚህ የትምህርት ክፍል በአጠቃላይ ቋንቋዎች የአማርኛም የእንጊሊዘኛም፤ የማህል ጥናትም ፤ጋዜጠኝነትና ተግባቦቱን በአጠቃላይ የሚያንቀሳቅስ የትምህርት ክፍል ነዉ።


የባህር ዳር ዩንቨርስቲ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዩ ሽፈራዉ፤ ባህር ዳር ዩንቨርስቲ ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ ወጣት ምሑራንን እያፈራ እንደሆነና ከሀንቡርግ ዩንቨርስቲ ጋር የፀደቀዉ የትብብር ሥራ የከፍተና ተቋሙን ጥንካሪ እንደሚያጎለብተዉ ገልፀዋል። እንደ ዶክተር ተስፋዬ በአሁኑ ዉቅት በዚህ ዩንቨርስቲ የሚማረዉ መደበኛና መደበኛ ያልሆነዉ ተማሪ በጠቅላላ 46 ሺ መሆኑን፤ በዩንቨርስቲዉ የሚያገለግሉት ምሑራን በቁጥር ወደ 1650 መሆናቸዉንና የአስተዳደር ሰራተኞች ወደ 3900 አካባቢ እንደሆኑ ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ በፊት ለምርምር ስራ ጀርመን የነበሩት ዶክተር ተስፋዩ ሽፈራዉ ኢትዮጵያና ጀርመን በትምህርትና ምርምር ስራ በርካታ ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
« እንደሃገር ሁለቱ ሀገሮች ለረጅም ዘመናት በአጋርነት በተለያዩ ዘርፎች ግንኙነት አላቸዉ። በምህንድስናዉ በባህል ልዉዉጡም በርካታ ተሞክሮዎች አሉ፤ የጀርመን መንግሥት ከፍተኛ እገዛንም እያደረገ ነዉ። ከዚህ በመነሳት የሁለቱ ሃገሮች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የልምድ ልዉዉጥ እና የአጋርነት ሥራን መስራት ይኖርባቸዋል። ከዚህ በመነሳት የሀንቡርግ ዩንቨርስቲና የባህር ዳር ዩንቨርስቲ ከረጅም ጊዜ ዉይይትና ምክክር በኋላ ባለፈዉ ዓመት የጋር የስምምነት ዉል ተፈራርመናል። ያም ሰነድ ሥራን ለመጀመር ያክል በመጀመርያ ምን ዓይነት የድሕረ ምረቃ ፕሮግራም ልንከፍት እንችላለን፤ ምን ዓይነት የምርምር ስራዎችን ልንሰራ እንችላለን በተለይ አሁን ግንኙነትን የጀመርነዉ ከባህልና ከቋንቋ በተያያዘ መልኩ በተለይ በግዕዝና አማርኛ ቋንቋ ላይ ለመስራት በባህል ልዉዉጥ ላይ ለመስራት ነዉ ያቀድነዉ።

Kooperationsvertrag zwischen der Universität Hamburg und der Universität Bahirdar
ምስል Tesfaye Shiferaw

ስለዚህም ይህን ያማከለ የድሕረ ምረቃ ፕሮግራም ምን እንክፈት፤ እንዲሁም በጋራ ምን ዓይነት ምርምሮችን እንስራ፤ ይህንን ስንሰራ ደግሞ የተማሪና የመምህር ልዉዉጥ ሊኖረን ይገባል የሚሉት ነጥቦችን አይተናል። በሃንቡርግ የሚገኙ ተማሪዎችና መምህራን ወደ ባህር ዳር መጥተዉ፤ በአንፃሩ እዚህ ያሉት ወደዝያ ሄደዉ በቦታዉ ላይ ያለዉን ነባራዊ ሁኔታ በማየት፤ የሚሰሩዋቸዉን ነገሮች የሚያስተምሩዋቸዉን ርዕሶች በማየት ትምህርት እንዲቀሰም የባህልና የእዉቀት ልዉዉ ጥ እንዲኖር ነዉ።»


በሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ የእስያና የአፍሪቃ ጥናት ተቋም መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ጌቴ ገላዬ፤ ሀምቡርግ ዩንቨርስቲ ከደብረ ማርቆስ ዩንቨርስቲ ጋርም የትብብር ሥራዉን ይጀምራል። « ሀምቡርግ ዩንቨርስቲ ከባህር ዳር ዩንቨርስቲ ጋር ብቻ ሳይሆን ከደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ ጋርም ይሰራል፤ ሶስቱ ዩንቨርስቲዎችን አጣምረን ነዉ በጋራ ለመሥራት እቅድ የያዝነዉ። ምክንያቱም ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ካሉት ከባህር ዳርና ከደብረማርቆስ ዩንቨርስቲዎች ጋር የመግባብያ ስምምነት ተፈራርመን ነበር። ይህ የመግባብያ ሰነድ እገዛን የሚሰጠዉ በተማሪዎች ልዉዉጥ በጋራ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ እንዲሁም የጥናትና የምርምር ዉጤቶችን በመለዋወጥ ፤ በጋራ የምርምር ዘርፎችን በመንደፍ እንድንሰራ የሚያስችል ነዉ። በተለይ ተማሪዎቻችን ከሀንቡርግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ፤ ከዝያም ከኢትዮጵያ ወደ ሃንቡርግ እንዲመጡ እና ጀርመን የደረሰበትን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጥናትና ምርምር እንዲሰሩ በተለይ በባህልና በቋንቋ ላይ ትምህርትን በመለዋወጥ በመቅሰም ምርምር በማድረግ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ነዉ።»


ኢትዮጵያ የግዕዝ ቋንቋ መፍለቅያየ ቋንቋዉ ባለቤት ሆና በቋንቋዉ ትምህርትን አግኝቶ ምርምር አድርጎ የዶክትሪት ማዕረግ ግን የሚገኘዉ ጀርመን መሆኑ ለሚያደምጠዉም ግራ ይገባል። በሌላ በኩል በጀርመን ሃገር በኢትዮጵያ ጥንታዊ የብራና ፅሑፍ ላይ በግዕዝ ቋንቋ ጥናትና በኢትዮጵያ ባህል ላይ ጀርመናዉያን ምርምር ማድረግ ከጀመሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል፤ ብዙም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክን የሚያመላክት ጽሑፎች አሉዋቸዉ። በግዕዝ ጥናት ምርምር የዶክትሪት ማዕረጋቸዉን በጀርመን ያገኙት ግን ያገኙት ሙሉቀን አንዱዓለም በጀርመን ሃገር በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ላይ ባህል ላይ ከፍተኛ ጥናት እንደሚደረግ ገልፀዋል።

Kooperationsvertrag zwischen der Universität Hamburg und der Universität Bahirdar
ምስል Tesfaye Shiferaw


የስምምነቱ በተለይ በዩንቨርስቲዉ ሥር በሚገኘዉ አባይ የምርምር ተቋም ጋር በጋራ ለመስራትና «የኢትዮጵያ ሴማዊ ቋንቋዎችና ባሕል ጥናት» በተሰኘ የትምህርት መስክ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ለመክፈት የታቀደበት መሆኑን የገለፁልን በሀምቡርግ ዩኒቨርስቲ የእስያና የአፍሪቃ ጥናት ተቋም መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ጌቴ ገላዬ ናቸዉ።
የባህር ዳር ዩንቨርስቲ የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዩ ሽፈራዉ በበኩላቸዉ፤ ይህ በዉል የታሰረዉ የስራ እቅድ ወደ ተግባር ተለዉጦ እንዲታይ ፤ ተከታታይነት እንዲኖረዉ፤ የሚዲያዉ ትኩረት እንዳይለየዉ ሳያሳስቡ አለለፉም።

የባህር ዳር ና የሀምቡርግ ዩንቨርስቲ የጀመሩት የትብብር ሥራ አብቦ በሁለቱም በኩል በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናት በጥንታዊ ባህል ረገድ ብዙ ምሁራንን እንዲያፈራ ምኞታችንን እንገልጻለን። ቃለ-ምልልስ የሰጡንን በማመስገን ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉዉን መሰናዶ እንድያደምጡ እንጋብዛለን።


አዜብ ታደሰ


አርያም ተክሌ