1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዚምባብዌ በውድቀት አፋፍ ላይ

ሐሙስ፣ መስከረም 26 1998
https://p.dw.com/p/E0eI

182 ዓባል መንግሥታት ያሉት የምንዛሪ ተቋም በወቅቱ 300 ሚሊያርድ ዶላር ገደማ የሚጠጋ ሃብትን ይዞ ተግባሩን ያከናውናል። በአሁኑ ጊዜ በተቋሙ በኩል ገንዘብ እያበደሩ ወለድ የሚያገኙት መንግሥታት ቁጥርም ወደ 45 የሚጠጋ ነው።
ዚምባብዌ ባለፈው መስከረም ወር በዕዳ የተነሣ ከዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም ከመወገድ ለጥቂት ነው ያመለጠችው። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ላይ ብርቱ ችግር ባስከተለ ነበር። ዚምባብዌ የምንዛሪውን ተቋም የግድ ትፈልጋለች። ምክንያቱም ዓለምአቀፍ ገንዘብ አቅራቢዎች ብድር አሰጣጣቸውን የሚያከናውኑት ከምንዛሪው ተቋም አካሄድ ጋር በማጣጣም መሆኑ ነው።

ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም IMF ዚምባብዌ በኤኮኖሚ ውድቀት አፋፍ ላይ ትገኛለች ሲል የአገሪቱን መንግሥት እንደገና አስጠንቅቋል። የኑሮ ውድነት በተፋጠነ ግስጋሤ መጨመር፣ የሕዝቡ ድህነት መባባስና አገሪቱ ዕድገት-አልባ እየሆነች መሄዷ ነው የተቋሙን አስተዳዳሪዎች ብርቱ ስጋት ላይ የጣለው። የምንዛሪው ተቋም አሁን ባወጣው ዘገባው በፕሬዚደንት ሙጋቤ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ ካልተደረገ የዚምባብዌ የወደፊት ዕጣ የጨለመ እንደሚሆን አመልክቷል።

ዚምባብዌ ባለፈው ወር 300 ሚሊዮን ዶላር ከሚጠጋው የውጭ ዕዳዋ 120 ሚሊዮን የሚሆነውን ድርሻ በመጨረሻይቱ ደቂቃ በመክፈል ነው ከምንዛሪው ተቋም ዓባልነት ከመወገድ ለጥቂት ያመለጠችው። ገንዘቡ ሳይጠበቅ ድንገት ከየት እንደመነጨ እስካሁን በውል የሚታወቅ ጭብጥ ነገር የለም። የሚጠረጠረው ግን ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ገንዘቡን የአገሪቱን ኩባንያዎች ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ አሟጠው እንዳመጡት ወይም በወቅቱ አዲሷና ታላቋ አጋራቸው ቻይና ሳትሰጣቸው እንዳልቀረች ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዚምባብዌ በትናንትናው ዕለት ሌላ የ 15 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንዳንቀሳቀሰች ለመንግሥቱ የቀረበው የአገሪቱ ጋዜጣ “The Herald” አትቷል።

ሃቁ ያም ይሁን ይህ በሌላ በኩል ዚምባብዌን ተጠናውቶ የቆየው ዓመጽ፣ የማሳደድና የማሰር ዕርምጃ ባለበት እንደቀጠለ ነው። በዛሬው ዕለት ብቻ በቤንዚን እጥረት ሳቢያ በእግር ወደ ሥራ በማምራት ላይ የነበሩ የተቃዋሚ ወገን ዓባላት ተይዘው ታስረዋል። የተወነጀሉት በድርጊታቸው ዚምባብዌ ምንም ነዳጅ ዘይት የላትም የሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ አድርገዋል በሚል ነው። ፕሬዚደንት ሙጋቤ አገሪቱ ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዳለባትና በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ መራቡንም አምነው ለመቀበል ፈቃደኛ አይደሉም።
ይሁንና በተባበሩት መንግሥታት የምግብ ተቋም ግምት መሠረት የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልገው የዚምባዌ ሕዝብ ቁጥር ከአራት ሚሊዮን ይበልጣል። ሁኔታው ይህን ያህል አስደንጋጭ ቢሆንም የአገሪቱ መንግሥት እስካሁን የዕርዳታ ጥሪ ከመሰንዘር ይልቅ ነገሩን ማድበስበሱን ነው የመረጠው። እርግጥ እስከሚቀጥለው ዓመት አዝመራ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን ለሚበልጥ ሕዝብ በነጻ ምግብ እንደሚያከፋፍል ይፋ ማድረጉ ችግሩ ለመኖሩ ማረጋገጫ ነው።

ዚምባብዌ አንዴ የክፍለ-ዓለሚቱ የዳቦ ቅርጫት ነበረች። ይሁንና ሙጋቤ ከአምሥት ዓመታት በፊት ጥቁሮችን የመሬት ባለቤት ለማድረግ በያዙት ለውጥ በተሰላ ሁኔታ አራት ሺህ የሚጠጉ ነጭ ገበሬዎችን በሃይል ካባረሩ ወዲህ የእርሻው ልማት ተሰናክሏል። ሁኔታው በአገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ ያስከተለው ውጤትም በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ከዚያን ወዲህ የአገሪቱ አጠቃላይ ማሕበራዊ ምርት በግማሽ አቆልቁሏል፤ የኑሮ ውድነት ባለፈው ዓመት ከስድሥት ዕጅ በላይ እስከመናር ደርሶ ነበር። ይሄው ለጊዜው እንደገና ቢለዝብም በያዝነው ዓመት መጨረሻ መልሶ አራት ዕጅ እንደሚደርስ የምንዛሪው ተቋም ግምት ነው።

ዚምባብዌ ዛሬ ይህን ከመሰለ ከከፋ ማሕበራዊ፣ የኤኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ደርሣ ነው የምትገኘው። ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ፊት ባሰሙት ንግግር ፖሊሲያቸውን፤ በተለይም የመሬት ይዞታ መርሃቸውን ስኬታማ ነው ካሉ ወዲህ ለውጥ መጠበቁ ሲበዛ ያዳግታል። በአንጻሩ የዚምባብዌ መንግሥት “ቁሻሻን ማስወገድ” በሚል መርህ ድሆችን በማፈናቀል በያዘው ባለፉት ወራት ዘመቻው እንደቀጠለበት ነው። በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት እስካሁን መንደሩና ደሣሣ ጎጆዎቹ እንዲፈርሱ የተደረገበት ያላንዳች መጠለያ የቀረ ድሃ ሕዝብ ቁጥር 700 ሺህ ገደማ ይጠጋል።

መንግሥት ለዕርምጃው የሚሰጠው ምክንያት ድርጊቱ ወንጀልንና ሕገ-ወጥነትን ለመቋቋም የግድ አስፈላጊ ነው የሚል ነው። ዘመቻው በተካሄደባቸው ባለፉት ወራት ብቻ 14 ሺህ መንገድ አዳሪ ሕጻናትና አነስተኛ ችርቻሪዎች ወንጀል ፈጽማችኋል በመባል ታስረዋል። ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች የሚናገሩት ፕሬዚደንት ሙጋቤ ዘመቻውን ሥልጣናቸውን ለማጠናከርና ተቃዋሚዎችን ለማዋከብ እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው።