1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዐብይ ይሮጣሉ-ጊዜዉ ይከንፋል። ዓመት!

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2011

የትግራይ መሪዎች ግን ሌላዉ የኢትዮጵያ ግዛት ከሞያሌ-እስከ ቅማት፣ከነጆ  እስከ ጂጂጋ በግጭት-ዉዝግብ ሲተራመስ የግዛታቸዉን ሠላም አስከብረዉ በመኖራቸዉ ይኩራራሉ።ተኩራሩም-አፈሩ፣ ለዉጡን ባያደናቅፉ-ለለዉጡ ስኬት በሒደቱ ሙሉ ተሳታፊ መሆናቸዉ የሚጠቁም ምግባር በግልፅ አልታየም።

https://p.dw.com/p/3G2nB
Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed in Addis Ababa | Demonstration mit Anhängern
ምስል Reuters

የለዉጥ ጉዞዉ ዐመት ዞሮ ገጠመ።ዉጤት?

አምና የነገን ቀን።ቃል ገቡ።«ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ።» እንዲል ባለቅኔዉ።እሳቸዉም አሉት።አምና ክረምት።  ቃላቸዉን ገቢር አድርገዉ ይሆን? «እንዴታ ባይናቸዉ-እሳቸዉ፣ ባለፈዉ ሳምንት።                       
ዶክተር ዐብይ አሕመድ ዓሊ ሮጠዋል።ይሮጣሉም።ጊዜዉ ግን ይከንፋል።አንድ ዐመት።የዐመቱ ሩጫ፣ድል፣ ዉጤት፣ጥፋት-ዉድቀቱ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።
                            
በርግጥም ሮጡ፣ የሕዝብ ድጋፍም ጎረፈላቸዉ።አዲስ አበባ።ሰኔ።
           
አስመራ-ሐምሌ።
 
ዋሽግተን-ሐምሌ
      
ፍራንክፈርት-ጥቅምት
         
ከሙስሊሞች ጋር ዋሽግተን።
             
ከኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ጋር-ዋሽግተን።እያሉ ቀጠሉ።ጊዜዉም፣ ባለቅኔዉ እንዳለዉ «በጊዜ ቀለበት ሰተት-----» ነገ አንድ ዓመት።ዉጤት።
                                  
ጀዋር መሐመድ፣ የፖለቲካ አጥኚ፣ የኦሮሞ መብት አቀንቃኝና የOMN ሥራ አስኪያጅ።በሐገር ዉስጥ፣ በርግጥም ዐብይ ሥልጣን ከመያዛቸዉ በፊት ቢጀመርም የኢትዮጵያ ወሕኒ ቤቶች ለዐመታት ያጨቁ-ያሰቃዩቸዉን እስረኞች ወደ ዉጪ «የተፉት» በዐብይ ዉሳኔና እርምጃ ነዉ።150 ሺሕ ገደማ።ስደተኛ ፖለቲከኞች  በአሸባሪነት የተወነጀሉ፣ የታጠቁ፣የደም የተቃቡ ሳይቀሩ ወደ ተግተልትለዉ ኢትዮጵያ ገብተዋል።ታፍነዉ የነበሩ መገናኛ ዘዴዎች ተለቅቀዋል።አፋኝ የሚባሉ ሕጎች ተሻሽለዋል ወይም እንዲሻሻሉ ተወስኗል።ሙሰኞች በከፊልም ቢሆን ተጠያቂ እየሆኑ ነዉ።ኖሮዊያዉ የፖለቲካ አጥኚ ፕሮፌሰር ክጄቲል ትሮንቮል የዐብይ ድል ባጭር ዓረፍተ ነገር ይገልፁታል።
                                     
«ፈላጭ ቆራጩን መንግሥት መነቃቅረዉ፣የተለያዩ ሐሳቦች በአደባባይ እንዲወጡ ከመቀበል አልፈዉ ጋብዘዋልም።»የምጣኔ ሐብት አዋቂና የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮሰፈር መሐመድ አባጀበል ጣሒሮ የፈጣኑ ለዉጥ በጎ ዉጤት መጥፎም አስከትሏል ባይ ናቸዉ።
                                          
መጥፎ ከሚባሉት ዋናዉ በየስፍራዉ ሺዎችን የገደለ፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለዉ ግጭት ነዉ።አብዛኛዉ ግጭት የጎሳ መልክና ባሕሪ የተለባሰ ነዉ።ጀዋር እንደሚለዉ ግጭት ትርምሱ የዴሞክራሲዊ ሥርዓት ግንባታ ገና ያለመጀመሩ ጉድለት አብነት ያደርገዋል።
                                        
ፕሮፌሰር ክጄቲል ዐብይ ቃል-ንግራቸዉን እንደማያጥፉ እርግጠኛ ናቸዉ።ግን ለዉጡን ተቋማዊ አለማድረጋቸዉ ምናልባት የጉድለቱ ምንጭ ሳይሆን አይቀርም።እንዲያዉም ዐብይ አንድ ሰዉ መሆናቸዉን መረዳት አለብን ባይ ናቸዉ።
                               
«በቃላቸዉ እንደሚፀኑና የለዉጥ መርሐቸዉን እንደሚያከብሩ አልጠራጠርም።በዚሕ ረገድ ለዉጥ የሚያደርጉና ለለዉጥ እንደቆሙ ጠቅላይ ሚንስር ነዉ የማያቸዉ።ይሁንና የምናየዉ ለዉጦቹን ተቋማ የማድረጉ ሒደት መዘግየቱን ነዉ።ከግባቸዉ ለመድረስ የሚጓዙበትን ፍኖተ ካርታ ወይም ስልት (ስትራቴጂ) በግልፅ ባለማሳወቃቸዉ ይተቻሉ።አንድ ሰዉ መሆናቸዉን መገንዘብም አለብም።» 
ዐብይ አንድ ሰዉ ናቸዉ።ድጋፍ ይፈልጋሉ።ድጋፍ ለማግኘት ግን ለመደገፍ ዝግጁ መሆን አለባቸዉ።የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ-ማሕበራዊ ጉዞ ለ27 ዓመታት በበላይነት የዘወረዉ ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) ዛሬ በብዙዎች እምነት «አኩራፊ» ነዉ።ከፓርቲዉ ባለስልጣናት አንዳዶቹ ትግራይን ጨምድደዉ ይዘዉ ለዉጡን ለማደነቃፍ እስከማሴር ይደርሳሉ ተብለዉ ይታማሉ።የትግራይ መሪዎች ግን ሌላዉ የኢትዮጵያ ግዛት ከሞያሌ-እስከ ቅማት፣ነጆ  እስከ ጂጂጋ በግጭት-ዉዝግብ ሲተራመስ የግዛታቸዉ ሠላም አስከብረዉ በመኖራቸዉ ይኩራራሉ።ተኩራሩም-አፈሩ፣ ለዉጡን ባያደናቅፉ-ለለዉጡ ስኬት በሒደቱ ሙሉ ተሳታፊ መሆናቸዉ የሚጠቁም ምግባር በግልፅ አልታየም።
የገዢዉ ፓርቲ ኢሕአዴግ አጋር የሚባሉት የበኒ-ሻንጉል፣የጋምቤላ፣የአፋር፣የሶማሌ፣ የሐረሪና የድሬዳዋ ገዢ ፓርቲዎች አንድም ገና ከለዉጥ ጋር በቅጡ አልተዋወቁም፣ ዓለያም ከአዲስ አበባና ከመቀሌ በሚደርሳቸዉ «ተቃራኒ ትዕዛዝ» ግራ-ቀኝ እንደዋዠቁ ነዉ።ሰወስትም አድፍጠዋል።ሰወስቱ-ወይም ከሰወስቱ አንዱ እዉነት ሆነም-ሐሰት ባለፈዉ አንድ ዓመት ለዉጡን ለማገዝ ብቁ አልነበሩም። 
ሕወሐት በሚመራዉ መንግሥት ክፉኛ ደቀዉ ብርዥ ጥርዥ ይሉ የነበሩት የሐገር ዉስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች-የ27 ዓመታት አጀንዳቸዉ አንድም በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ-ሁለትም በፖለቲካ አቀንቃኞች በመቀማቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለምሳም-ለራትም፣ድርድር-ዉይይትም፣ ሲጠሯቸዉ «አቤት» ለማለት ከማጠደፍ፣ አለያም እንደ አብዛኛዉ ተራ ኢትዮጵያዊ «መደመርን» ከማቀንቀን በላይ ለዉጡ ፈር እንዳይስት የሚታገሉበት ስልት፣ዕቅድ፣ዝግጅትም ያላቸዉ አይመስልም።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ነባር ሕግ-አዋጅ ሽረዉ ከዉጪ የጋባዟቸዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች-አማፂ ይሁኑ ሠላማዊ ታጋይ አዲስ አበባን በረገጡ ማግስት አንዳቸዉ ከሌላለቸዉ ወይም ከገዢዎች ጋር መወዛገብ፣ ደጋፊዎቻቸዉን ማጋጨት፣የጠቅላይ ሚንስትሩን ድጋፍ ለማግኘት መራወጡ በርግጥ ሠምሮላቸዋል።የለዉጡ እንጭጭ ፍሬ-እንዲጎመራ አደረጉ የሚባለዉ አስተዋፅኦ ማግኘት መጥቀስ ከባድ ነዉ።
የግል ወይም ነፃ የሚባሉ መገናኛ ዘዴዎችንና ጋዜጠኞችን ከአቀንቃኞች ወይም ከማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ የግል አስተያት ሰጪዎች መለየት ሲበዛ ከባድ ነዉ።
የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ለጠቅላይ ሚንስትሩ ማመልከቻ መፃፋቸዉን አንብበናል።ከዋሽግተን-አዲስ አበባ መመላለሳቸዉን እናዉቃለንም። ጭናቅሰን፣ ነጆ፣ እስቴ፣ ጌድኦ፣ኮሬ፣መተሐራ፣አዋሳ፣ ብቅ ብለዉ-ለጠብ የሚጋብዙ ሰበብ፣ስሜት ምክንያቶችን ለየጠበኞቹ ለማስረዳት የጣረ፣የየግጭት ሰለቦችን ለማፅናናት የሞከረ ሙሁር፣የኃይማኖት ሰባኪ ካለ-እሱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባለዉለታ ነዉ።
ሞያሌ ለአዲስ አበባ በጣም ሩቅ ነዉ።ቡራዩ ስንት ቀን ያጉዝ ይሆን? ለጋ ጣፎ ለመጓዝ የአንጋች አጀብ ይጠይቅ ይሆን? 
ብዙዎች እንደሚሉት ዐብይ የመሩት ለዉጥ ከግብ እንዲደርስ ሁሉም መሳተፍ-የዐብይ መንግስትም ሁሉም የሚሳተፍበትን ስልት ግልፅ ማድረግ አለበት።የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይስ አጥኚ መረሳ ፀሐይ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ዉስጥ እዉነተኛ ሠላም፣ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ፍትሕ እንዲሰርፅ ያሁኑ ግጭት-ቁርቁስ ሽኩቻ መቆም አለበት።
ደም አፋሳሹ ግጭት የሚቆመዉ ደግሞ በድርድር ነዉ።ዉይይት።
                             
ጀዋር መሐመድ እንደሚለዉ ግን ድርድር-ዉይይቱን መምራት ወይም መዘጋጀት የነበረባቸዉ ሊሕቃን እራሳቸዉ የደም አፋሳሹ ጠብ-ግጭት ዘዋሪ መሆናቸዉ ነዉ ዕዳዉ።
                                
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከዉጪ መርሐቸዉ ብዙ ድጋፍ፣አድናቆት፣ዉዳሴም ያገኘዉ ከኤርትራ ጋር ያደረጉት የሰላም ስምምነት ነዉ።መለስ ካንጀት-ይሁን ካገት ከኤርትራ ጋር ሰላም ማዉረድን ተናግረዉታል፣ ኃይለማርያም-ሆድ ሲያዉቅ---ቢባሉም አሥመራ ለመሔድ ዝግጁ ነኝ»ን ብለዉታል።ዐብይ አደረጉት።
                                 
ዐብይ ምናልባት መቶ ሺዎች የረገፉበትን ጦርነት፣ ሃያ ዓመት የተንተከተከዉ ቂም፣ለያዥ-ለገራዥ ያስቸገረዉን ቂም ባጭር ጊዜ መንቀላቸዉ በርግጥ አስደናቂ ነዉ።እዚያም የሚቀር አለ።
                                   
«የሠላም ሒደቱ ማለት፣ ከኤርትራ ጋር የተደረገዉ ስምምነት ሕጋዊ ማቀፍ ይጎድለዋል።ሐምሌ ላይ አስመራ ዉስጥ የመግባባት (ፍላጎት) አዋጅ (Deceleration of intent ተፈርሟል።ኋላ ጂዳ ዉስጥ እንደገና ፈርመዉታል።ይሁንና አስገዳጅ ሕጋዊ ሰነድ አይደለም።ሥለዚሕ ንግድ፤ ቀረጥ፣ ሸርፍ፣ዜግነት፣ ፀጥታ፣ወዘተ የሚመሩበት አዲስ የጋራ ሥምምነት ይጎድላል።»
ዐብይ ከግድያ ሙከራ ተርፈዋል።መፈንቅለ መንግስት የመሠለ የጦር ሠራዊት ባልደረቦች ከበባን አክሽፈዋል።ፈተናዉ ግን በዚሕ አያበቃም።ግን ትችትም አይወዱም።ግን ከዚያች ወንበር ላይ እስካሉ ድረስ አይቀርላቸዉም።
                                          
«ዘቅላይ ሚንስር ሲኮን፣ በዚሕ እሳቤ አለቃ ሲኮን ትችትን ማስቀረት ከባድ ነዉ።ምንም ነገር ብታደርግ መተቸትሕ አይቀርም።ሥለዚሕ ጠንካራ አመራር ያስፈልግሐል።»
አሉ ፕሮፌሰሩ።ወፍራም ቆዳ-እንበለዉ ይሆን።ዘንድሮ ሊደረግ የታቀደዉ የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ ተሰርዟል።የተሰጠዉ ምክንያት በርካታ ሕዝብ በመፈናቀሉ የሚል ነዉ።እርግጥ ነዉ የትግራይ መስተዳድር የመንግስት የማፈፀም አቅም ደካመነት ብሎታል።ኢትዮጵያ በተፈናቃዮች ቁጥር ከዓለም አንደኛ የመሆንዋን ዜና መቀሌ አልደረሰ ይሆን? በመጪዉ ዓመት ምርጫ ይደረጋል ተብሏል-እሱስ ይሰረዝ ይሆን? አናዉቅም። ሰዉዬዉ ግን ይሮጣሉ-ጊዜዉም ይበራል። ዘንድሮ-አምና ሊሆን። ቸር ያሰማን።

Äthiopien Präsident  Isaias Afwerki und Premierminister Abiy Ahmed in Asmera
ምስል Yemane G. Meskel/Minister of Information
PM Abiy Ahmed in der Frankfurt Arena
ምስል DW/W. Tesfalem
PM Abiy Ahmed in der Frankfurt Arena
ምስል DW/W. Tesfalem
Anhänger von Ministerpräsident Abiy Ahmed demonstrieren in Addis Abeba
ምስል DW/Y. Gebregziabher

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ