1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ የሰዉ ዋጋዉ ስንት ነዉ?

እሑድ፣ ሰኔ 19 2014

ቶሌ ላይ በመቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ገበሬዎች በመደዳ የተገደሉት ጋሌማ-አርሲ ዉስጥ የወረዳ አስተዳዳሪና የፖሊስ ኮሚሽነር ጭምር በታጣቂዎች መገደላቸዉ በተዘገበ በሳልስቱ ነዉ።በዚያዉ ሳምንት ጋምቤላ፣ጊምቢና ዶንቢዶሎ ከተሞች--- በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል።ባለፈዉ ሚያዚያ ጥንታዊቷ ጎንደር ከተማ ዉስጥ---- 30 ሙስሊሞች ተገድለዋል

https://p.dw.com/p/4DDWF
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

«ጭፍጨፋዉ በገለልተኛ ወገን መጣራት አለበት» ተወያዮች

ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 11 2014 ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በመቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች መጨፍጨፋቸዉ ከዉጪም ከዉስጥም ቁጣ፣ ተቃዉሞና ዉግዘት አስከትሏል።ሟቾች በአብዛኛዉ የአማራ ተወላጆች ሲሆኑ ገዳዮች ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ጦር ወይም ኦነግ ሸኔ የተባለዉ ታጣቂ ቡድን አባላት እንደሆኑ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።ይሁንና ተቃዋሚዎቹ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባወጡት መግለጫ ግድያዉ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ከመጠየቅ ባለፍ በገዳዮቹ ማንነት ላይ ግልፅ አቋም አልያዙም።

ቶሌ ላይ በመቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ገበሬዎች በመደዳ የተገደሉት ጋሌማ-አርሲ ዉስጥ የወረዳ አስተዳዳሪና የፖሊስ ኮሚሽነር ጭምር በታጣቂዎች መገደላቸዉ በተዘገበ በሳልስቱ ነዉ።በዚያዉ ሳምንት ማክሰኞች ሰኔ 7 ጋምቤላ፣ጊምቢና ዶንቢዶሎ ከተሞች ዉስጥ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች፣ ከኦሮሞ ነፃ አዉጪ ጦርና ከጋምቤላ ነፃ አዉጪ ግንባር ጋር በገጠሙት ዉጊያ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸዉ ተዘግቧል።ባለፈዉ ሚያዚያ ጥንታዊቷ ጎንደር ከተማ ዉስጥ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት  30 ሙስሊሞች ተገድለዋል።ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዓመታት ያስቆጠረዉ የጎሳ፣የግዛት ይገባኛልና የስልጣን ጥያቄ ዘንድሮ ተባብሶ በተለይ ደራሼ፣ጂንካ ወይም ደቡብ ኦሞና ጎጂ ዉስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።ባለፉት ወራት ሰሜን ሸዋ፣ምስራቅና ምዕራብ ሸዋ ዉስጥ አማፂያንና የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች አባገዳዎችን ጭምር ገድለዋል።የሰሜኑ ጦርነት፣ ድርቅና ረሐብ ያደረሱና የሚያደርሱት ጥፋት አልበቃ ያለ ይመስል በጎሳ፣ በሐይማኖት ወይም በሥልጣን የበላይነት የሰከሩ ኃይላት የገዛ ወገናቸዉን፣ ያዉም መከላከያ የሌለዉን ሰላማዊ ሰዉ በመደዳ ለመግደል፣ለማፈናቀልና ሐብት ንብረቱን ለማጥፋት መጨከናቸዉ ብዙዎችን እያሳሰበ ነዉ።ኢትዮጵያ እንደ ሐገር መቀጠሏም እያጠያየቀ ነዉ።የጎሉትን ጥያቄዎች አንስተን ባጭጭሩ እንነጋገራለን

ነጋሽ መሐመድ