ሥጋትና ተስፋ ያጠላበት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለዉጥ
እሑድ፣ መጋቢት 15 2011በኢትዮጵያ ለዉጥ ከጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላዉ ነዉ። በዚህ ለዉጥ የተገኙ በርካታ ፍሪዎች መጠቀሳጠዉን ያህል የለዉጥ ተስፋ የደበዘዘ መስሎ መታየቱን ብዙዎች ይናገራሉ። በሃገሪቱ እዚህም እዚያም የተከሰተዉ የዜጎች መፈናቀል፤ በዘር እና በብሔር ጎራ ለይቶ መወዛገብ ፤ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል በጥርጣሪ መተያየት እና ይህን ተከትሎ የሚመሩዋቸዉ ክልሎች እርስ በርስ መወዛገብ፤ ሕገወጥ ተብሎ የሚፈርሱ ቤቶችና የሚፈናቀሉ ዜጎች መበራከት እንዲሁም የማእከላዊ መንግሥት መዳከም ለዉጡን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ምናልባትም ሃገሪቱን ወደ ብጥብጥ ይወስዳታል ብለዉ የሚሰጉ ጥቂቶች አይደሉም። በሌላ በኩልም መንግሥት በሰላም ለሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን እንዲሁም በቀጣይ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ በማስፋት መጭዉ አገር አቀፍ ምርጫ ነጻ እና ተአማኒነት ባለው መልኩ እንዲከናወን አስፈላጊውን ጥረት እያደረኩ ነው ሲል በተደጋጋሚ ይነገራል። ሥጋት ኀስፋ ያጠላበት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለዉጥ በሚል በዉይይት የተሳተፉና ኃሳባቸዉን ያካፈሉን ፤ መምህርት መዓዛ መሐመድ፤ የኢትዮጵያዉያን ሃገራዊ ንቅናቄ ፓርቲ አባል፤ አቶ ኦልባና ሌሊሳ፤ የቀድሞ እስረኛ እና የኦሮሞ ፖለቲካ አቀንቃኝ፤ አቶ አበበ አካሉ፤ የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የቀድሞ እስረኛ እንዲሁም ፤ አቶ ገረሰፉ ቱፋ፤ የፖለቲካ አቀንቃኝ ናቸዉ ። ተወያዮችን በዉይይቱ ስለተካፈሉ በ «DW» ስም እያመሰገንን ፤ ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ