1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፤ መጭዉ ምርጫና የሴቶች ተሳትፎ ተግዳሮቶች

እሑድ፣ መጋቢት 5 2013

ሴቶች ለኮታ ማሟያ እንጂ ወደ ስልጣን የሚመጡት አሁንም ወንዶች ብቻ ናቸዉ ዉሳኔ ሰጭዎች ብለዉ የሚከራከሩ አሉ። ራሳቸዉን ለእጩነት የሚያቀርቡ ሴቶች ቁጥርስ ምን ያህል ነዉ? ሴቶች ራሳቸዉ ያገባናል ብለዉ በፖለቲካዉ ለመሳተፍ ምን ያህል ዝግጁ ናቸዉ? ለምርጫ እየተዘጋጀች ባለችዉ ኢትዮጵያ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዴት ትገመግሙታላችሁ?

https://p.dw.com/p/3qcV5
Challenges and Opportunities of Women Political Participation in Ethiopia
ምስል Azeb Tadesse/DW

«ሴቶች ተማሪዎች ከከፍተኛ ተቋማት የሚታፈኑበት፤ አካላዊ ጥቃት የሚደርስበት፤ እናቶች እና ሕጻናት የሚገደሉበት ሆኖ ማየቱ ልብ የሚሰብር ነዉ»

ኢትዮጵያ በታሪክ አገር የመሩ ፣ ጦርነትን በቆራጥነት መርተው ያሸነፉ ሴቶችን በፖለቲካ ውስጥ ያሳተፈች ሀገር ናት። ይሁንና ህብረተሰቡ ለሴቶች ባለው አመለካከት እንዲሁም የባህልና የወግ ተፅዕኖ የተነሳ የፖለቲካ ተሳትፏቸው አሁንም ድረስ ጎልቶ አይታይም።በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖሩም ከደጋፊነትና ከአባልነት የዘለለ ሚና የላቸውም። በገዡም ይሁን በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ የውሳኔ ሰጭነትና የመሪነት ቦታዎች በወንዶች የተያዙ ናቸው። በምርጫ ወቅትም ቢሆን የፓርቲዎቹ  እጩ ተወዳዳሪዎች በአብዛኛው ወንዶች ናቸው። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስርት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአንፃራዊነት ወደ ከፍተኛ የአመራር የመጡ ሴቶች ቁጥር የተሻለ ነው። የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ብሎም የሃገሪቱ የሰላም ሚኒስትር ከሴቶች ከፍተና ባለስልጣናት መካከል ተጠቃሽ ናቸዉ። በካቢኔ ደረጃም ቢሆን የተሻለ የሴቶች ቁጥር ይታያል። ያም ሆኖ ሴቶች ያላቸው ተሳትፎ  ዝቅተኛ ነው የሚሉም ጥቂቶች አይደሉም። የሴቶች ወደ ከፍተኛ ስልጣን ምጣት ለለዉጡ አንድ ማሳያ ነዉ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ወደ ስልጣን የመጡት ሴቶች ስልጣን የተሰጣቸዉ ለይስሙላ ነዉ ስልጣናቸዉን በእዉነት መጠቀም አልቻሉም የሚሉም እንዲሁ ይሰማሉ። ከሴቶች አንጻር ተደረገ የሚባለዉ ለዉጥ ተግባራዊ እስኪሆን ገና ጊዜ ይወስዳል የሚሉም አሉ።  ሁኔታውን ሰብረው የወጡ  ጥቂት ጠንካራ ሴቶች መኖራቸው ባይካድም፤ አብዛኞች ከፖለቲካ ተሳትፎ የተገለሉ ናቸው። ዕድሉን ያገኙትም ቢሆን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ካገኙት ዕድል ተገፍቶ በመውጣት እና በመቆየት መካከል ናቸው ሲባል ይሰማል። ይህ ዉይይታችን በሳምንቱ መጀመሪያ የተከበረውን የዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን መነሻ በማድረግ፤  ስድስተኛዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫና የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ተግዳሮቶችን ይቃኛል። በዚህ ዉይይት ላይ ሃሳባቸዉን ለማካፈል የቀረቡት ፤ ጋዜጠኛ የፖለቲካ ተንታኝ መዓዛ መሓመድ ፤ደራሲ መስከረም አበራ፤ እንዲሁም  ሰናይት ታደገ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የምትከታተል ናቸዉ። ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ