1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

ወጣቶች ሙስናን እንዴት መዋጋት ይችላሉ?

ዓርብ፣ የካቲት 2 2010

77 በመቶ አፍሪቃውያን ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች እንደሆነ በሚታመንበት አህጉር ወጣቱ ሙስናን እንዴት መጋፈጥ ይችላል? የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ትኩረት ነው።

https://p.dw.com/p/2s9Ch
Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ሙስናን መታገል

አዲስ አበባ ውስጥ የተጠናቀቀው የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የዘንድሮውን 2018 ዓም ሙስናን የሚዋጋበት ዓመት እንደሚሆን ገልጿል። የወቅቱን የህብረቱን ሊቀመንበርነት የተረከቡት የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ሀገራቸው ከአፍሪቃ ሙስና ካልተስፋፋባቸው ጥቂት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ይታመናል። የሀገራቸውን ተሞክሮ በአህጉሪቱ ተግባራዊ ያደርጉ ይሆን? ይህ ከጊዜ ጋር የሚታይ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ግን ህጉን የሚያስፈፅመው እና ተግባራዊ የሚያደርገው አካል ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የአገሮችን የሙስና ደረጃ የሚያጠናው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅትም ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው የሙስና ደረጃ መዘርዝር ኢትዮጵያ ከ176 ሀገራት 108 ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ለሀገሪቷ እድገት እንቅፋት ናቸው ካላቸው ችግሮች መካከል ሙስና አንዱ ነው። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተደረገ ነው? የወጣቱስ ሚና ምንድን ነው?

« የራሴ ቦታ ነበረኝ። ግን  እስከ 30 000 ብር ጉቦ መክፈል ነበረብኝ ያንን መክፈል ባለመቻሌ እና ባለመፈለጌ ይሄው 3 ዓመት ሆነኝ» ይላል ስሙን መናገር ያልፈለገው ወጣት። እሱም ይህ ችግር ወደፊት ይቀረፋል ብሎ አያምንም። ሌላው ወጣት ጌታቸው ነው። እሱም ከመሬት ጋር በተያያዘ በሙስና ተንገላቷል። ማስፈራራትም ደርሶበታል።ሌላው ወጣት ክብሮም ነው። እሱም  ብዙ ጊዜ ጉቦ ተጠይቆ ያውቃል። የጠየቁትም በእድሜ የሚበልጡት በከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እንደሆኑ በብስጭት ይናገራል። « የመንጃ ፍቃፍ ተግባር ፈተና ስወስድ ወደኩኝ። ያኔ አስተማሪው ጉቦ ብሰጥ እንደሚሻል ነገረኝ።» ክብሮም ግን ሁለት ጊዜ የመንጃ ፍቃድ ፈተናውን ወድቆ ጉቦ ሳይሰጥ ፈተናውን ሊያልፍ ችሏል። ቢሆንም እሱም ሆነ ሌሎች ከመታዘብ ውጪ ብዙ አማራጭ እንደሌላቸው ነው በተደጋጋሚ የህግ ባለሙያና የአንድ ድርጅት ነገረ ፈጂ የሆነው ክብሮም የታዘበው።

Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

ክብሮም ሙስና የጠየቁትን ሰዎች ለህግ ለማጋለጥ ባይሞክርም የሚጠቀየውን ገንዘብ ከመስጠት ተቆጥቧል። ጌታቸውም ቢሆን ተመሳሳይ ሀሳብ ነው ያለው። « ሙስና ከሚቀበለው ይልቅ የሚሰጠው ሰው ኃላፊነት መውሰድ አለበት ብዬ ነው የማምነው።»

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገር ኬንያን ከአፍሪቃ ሙስና ከተስፋፋባቸው ሀገራት በ4ኛ ደረጃ ሲሰጣት ከዓለም ደግሞ 145ኛው ስፍራ ላይ አስቀምጧታል። አበበ በዚህች ሀገር ነው የሚኖረው። በተለይ ከትራፊክ ፖሊሶች ጋር ያለውን ተሞክሮ ገልጿል።እሱም ሙስና በቶሎ የሚቀረፍ ችግር ነው ብሎ አያምንም። ስለሆነም በዕለት ከለት ኑሮው ውስጥ የተቀበለው ይመስላል። ሙስናንም በሁለት ጎኑ ከፍሎ ነው የሚያየው። በጥሩ እና በመጥፎ።

በ1994 ዓም የአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ ባካሄደው ጥናት መሰረት ሙስና ከስራ አጥነት ቀጥሎ የሀገሪቱ ሁለተኛ ችግር እንደሆነ ጠቁሟል። ጥናቱም የፌደራል ስነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲቋቋም ምክንያት እንደነበር በኮሚሽኑ የስነ ምግባር ትምህርት እና ኮሚኒኬሽን ዳሬክቶሬት ዳሬክተር የሆኑት አቶ ወንድአጥር ደነቀ ይገልፃሉ። በሀገሪቱ የዛሬ ሰባት ዓመት በተደረገው ጥናት መሠረት ደግሞ ከሌሎች የሀገሪቱ ችግሮች ጋር ሲነጻጸር ሙስና ሰባተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። « ጥናቱ የሚያሳየው በሁሉም ተቋሟት ውስጥ ደረጃው ይለያይ እንጂ ሙስና አለ። ይበልጥ የተጋለጡ የሚላቸው የፍትህ አካላትን፣ የግብር፣ የመሬት እና ፍቃድ የሚሰጡ ተቋማትን ነው።»

ታድያ ሰዎች ጉቦ ሲጠየቁ ምን ማድረግ አለባቸው?  አቶ ወንድአጥር  እንደሚሉት ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ካለማወቅ እና ህጉን ወይም አሰራሩን በሚጥሱ ሰዎች ምክንያት ሰዎች ተስፋ ለመቁረጥ ተዳርገዋል። ይሁንና ፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ይህንና ችግር ለመቅረፍ ትምህርት መስጠትን ዋነኛ አላማው አድርጓል።

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ