ወጣት አሸናፊ በ«ቤቶች» ድራማ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 25 2006አነጋገሩ ፈጣንና የብዙዎቹን ዘመናይ የከተማ ወጣቶች ስልት የተከተለ ነው። በረዥሙ አሳድጎ የጠቀለለው የራስ ፀጉሩ መለያው ይመስላል። በአንድ ቤተሰብ የዕለት ተዕለት ግንኙነት ዙሪያ በሚያጠነጥነው «ቤቶች» በተሰኘው አስቂኝ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ውስጥ አብይ ገፀ-ባሕሪያትን ተላብሰው ከሚጫወቱ ዋና ዋና ተዋንያን ዘንድ ይመደባል። በምናቡ ዓለም ይበቃል በእውኑ ደግሞ አሸናፊ ማኅሌት መጠሪያ ስሙ ነው።
ወጣት አሸናፊ ማኅሌት ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ጃን ሜዳ አካባቢ ልዩ ስሙ ኮርያ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነው። አሸናፊ ገና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነው ትወናን የጀመረው። በልጅነቱ በህፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት ውስጥም ሰርቷል። አሁን በሂደት ራሱን ወደ ዘርፈብዙ ተዋናይነት በመቀየር ላይ ይገኛል።
አርቲስት አሸናፊ ማኅሌት «ቤቶች» በተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ይበቃልን ሆኖ ከተጫወተው የተወሰደውን ነበር ያደመጣችሁት። የቴሌቪዥን ተመልካቹ ወክሎ የተጫወተውን ገፀ-ባህሪ እንደሚያደንቅለትና እንደተቀበለውም ገልጿል አሸናፊ።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወጣት እንደሚገጥመው ሁሉ የአሸናፊ ወላጆችም ልጃቸው ወደ ጥበቡ ዓለም ከመጠጋቱ ይልቅ ምርጫቸው ትምህርቱ ላይ ቢያተኩርላቸው ነበር። አሸናፊ ከቤተሰቡ ወደ ጥበብ ዓለም የተሳበ ብቸኛው ልጅ ነው።
ወጣት ተዋናይ አሸናፊ ማኅሌት ከትወናው ባሻገር ወደፊት የሚመኘው የድርሰትና የአዘጋጅነት ሙያም እውን እንዲሆንለት እንመኝለታለን። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ዘገባዉ ያድምጡ፤
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተክሌ የኋላ