ወጣት መራጮች በጀርመን
ዓርብ፣ መስከረም 10 2006የዶይቸ ቬለ ስቱዲዮ በሚገኝበት በዚህ የቦን ከተማ ፤ መንገዶች ሁሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በሚያስተዋውቁ የምርጫ ፖስተሮች ተሞልተዋል።የምርጫ ቀን መቃረቡ ለማንም ግልፅ ነው።በጀርመን ሀገር ደንብ መሰረት 18 ዓመት የሞላቸው ወጣቶች የመምረጥ መብት አላቸው። ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ መምረጥ የሚችሉ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ጀርመናውያን የምርጫ ወረቀት ደርሷቸዋል። አብዛኞቹም በመጪው እሁድ በጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ይሳተፋሉ። ግን የትኛውን እጩ ተወዳዳሪ እና ፓርቲ እንደሚመርጡ ግራ ነው የተጋቡት። ከጥቂቶቹ አስተያየት ውስጥ ፦
«አዎ እመርጣለሁ። በአጠቃላይ መምረጥ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ አስፈላጊነቱ እየቀነሰብኝ መጥቷል። ምክንያቱም ይህ ፓርቲ ወይም ይህን ሰው ነው መምረጥ የምፈልገው የምለው የለኝም።»
« በአሁኑ ሰዓት ገና አልወሰንኩም። ምክንያቱም ባሉን ፓርቲዎች በሙሉ በአሁኑ ሰዓት ደስተኛ አይደለሁም።»
« መምረጤን ርግጠኛ ነኝ። ማን እና ምን እንደሚሆን ግን አሁን ርግጠኛ አይደለሁም። በርግጠኝነት የማውቀው በግራ ካሉት ፓርቲዎች አንዱ እንደሚሆን ነው።»
« ሰዎች ለመምረጥ መሄዳቸው አስፈላጊ ነው። ይሁንና ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም።»
« ከፓርቲዎቹን አንዱን ለመምረጥ ከባድ ነው። ምክንያቱም የማልፈልገውን ነገር በፕሮግራማቸው አካተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሌላው አማራጭ ጭራስ የባሰ ነው ስል አስባለሁ።»
ግራ የተጋቡ ወጣቶች በየቦታው ይስተዋላሉ። ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጪውም በላይ በፌስ ቡክ እና ትዊተር የምርጫ ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ ይናገራሉ። በምርጫ የሚሳተፉት ሰዎች እድሜ በአማካይ ሲሰላ 45 ነው። አዳዲስ መራጮች በምርጫ ዘመቻው ችላ እንዳይባሉ አንዳንድ የወጣቶች ማህበሮች ወጣቱን የማነቃቃት ስራ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። የ 25 ዓመቷ ሶፊያ በፕ ከአነቃቂዎቹ አንዷ ናት « እንደሚመስለኝ በርካታ ወጣቶች የፖለቲካ ፍላጎት አላቸው አገራቸው ውስጥ እየተካሄደ ስላለው ነገር ማወቅ ይፈልጋሉ። ይሁንና ስላለው ልዩነት እና በርግጥ ለሀገሪቷ ስለሚጠቅመው ለመለየት ስለሚዳግት ነው።»
ወጣት ኢንጂኒየር ኃይሉ ታደሰ፤ አህን ከተማ በሚገኘው የጀርመን ዮንቨርሲቲ ያገለግላል። ከልጅነቱ ጀምሮ በጀርመን ሀገር ነው የሚኖረው። ዜግነት ወስዶ መምረጥ ከጀመረ አምስት ዓመቱ ነው። እስካሁንም በጀርመን የምክር ቤት ምርጫ እና የክፍለ ሀገር የተለያዩ ምርጫዎች ላይ ተሳትፏል። የአሁኑ እሁድም አንዱ መራጭ ነው። ሌላው እንዲሁ በእሁዱ ምርጫ የሚሳተፈው እስጢፋኖስ ሳሙኤል የሚንት ሚዲያ ኤጀንሲ ባለቤት ነው። በጀርመን ሀገር ስለሚካሄድ የምርጫ ስነ-ስርዓት ገልፀውልናል። ከድምፅ ዘገባው ያገኙታል
ልደት አበበ
ተክሌ የኋላ