ወጣትዋ ደራሲ
ዓርብ፣ ግንቦት 5 2008
ደራሲ «ሰብለወንጌል ፀጋ» ነዋሪነትዋን ሃዋሳ ከተማ ያደረገችዉ ወጣትዋ ደራሲ ሰብለወንጌል ፀጋ የተወለደችዉ በባሌ ዞን ጎባ ከተማ ዉስጥ ሲሆን ቤተሰቦችዋ በሥራ ምክንያት ወደ አርሲ ነገሌ ሲዘዋወሩ አብራቸዉ እየተዘዋወረች የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዋን ካጠናቀቀች በኋላ በ 2007 ዓ,ም በመቀሌ ዩንቨርስቲ በአካዉንቲንግ እና ፋይናንስ በዲግሪ ተመርቃለች። በዩንቨርስቲ ቆይታዋ «መጽሐፉ» የተሰኘ የመጀመርያ መጽሐፍዋን አሳትማ አቅርባለች። ወደ መጽሐፉ ይዘት ከመግባታችን በፊት ሰብለወንጌልን በሕጻንነትዋ ስለነበራት የሥነ-ጽሑፍ ዝንባሌ እንድትነግረን ጠይቀናት ነበር።
« እንደምክንያትነት የምቆጥረዉ ቤተሰባችን ዉስጥ ታላቅ እህቴ ብዙ መጽሐፍትን ታነባለች። በዝያ ምክንያት ብዙ መጽሐፍት ነበሩን። እነዚህ መጽሕፍት ደግሞ ከኔ እድሜ ጋር የማይመጣጠኑ ስለነበሩ እህቴ እንዳላነባቸዉ ትደብቅብኝ ነበር። ግን የስዋን መጽሐፍቶች እየፈለኩኝ ከተደበቀበት እያወጣሁ አነብ ነበር። በሌላ በኩል የተሰማኝን ስሜት የመጻፍ ልምዱ አለኝ፤ ማለት ሲከፋኝ ወይም ስደሰት ለሰዉ ከመንገር ይልቅ የመጻፍ ልምድ አለኝ። ይህ ልምድ ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ ያለ ነዉ። እናም እያነበብኩ አደኩ ከዝያ በኋላ ነዉ እንደዚህ አጫጭር ነገሮችን የፈጠራ ጽሑፎችን መጫጫር ጀመርኩ እና እሱ ነዉ እያደገ የመጣዉ።»
የእለቱ የወጣቶች ዝግጅት የ 21 ዓመቷን ወጣት ደራሲ ሰብለወንጌል ፀጋን ያስተዋዉቀናል፤ ሙሉ ቅንብሩን ተከታተሉ
ዮኃንስ ገ/እግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ