1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮማንድ ፖስቱ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች አስሯል ተባለ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 22 2010

በኢትዮጵያ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተላለፍ የተጠረጠሩ 1107 ሰዎች መታሰራቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር የሚመረምረው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ አስታወቁ። ከታሰሩት መካከል ባለሥልጣናት እንደሚገኙበት ያረጋገጡት ሰብሳቢው ማንነታቸውንና የታሰሩበትን አካባቢ ከመግለፅ ተቆጥበዋል። 

https://p.dw.com/p/2vI8h
Brasilien Handschellen der Gefängnisinsassen vor dem Hauptquartier der NGO Acuda
ምስል Reuters/N. Doce

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ባለስልጣናቱ "መታሰራቸው በጥቆማ ደርሶናል፣ የት ቦታም እንደታሰሩ ለይተናል" ብለዋል። ሰብሳቢው በእስር ላይ የሚገኙት ባለሥልጣናት ኮማንድ ፖስቱን አለመተባበር የሚል ክስ ጭምር እንደቀረበባቸው ተናግረዋል። አቶ ታደሰ ሆርዶፋ እንደሚሉት በእስር ላይ የሚገኙት 1107 ሰዎች በጸጥታ እና ሰላማዊ ኃይሎች ላይ የግድያ ወንጀል በመፈጸም፣ ቤት በማቃጠል፣ የመንግሥት እና ሕዝባዊ ተቋማትን በማውደም፤ መንገድ በመዝጋት እና ተሽከርካሪዎችን በማውደም፣ የማጓጓዣ እንቅስቃሴ እንዲስተጓጎል በማድረግ፣ የመማር ማስተማር ሒደት እንዲስተጓጎል በማድረግ የተጠረጠሩ ናቸው። የንግድ እንቅስቃሴ የመግታት፣ ቤት የማቃጠል፣ ንብረት እና ሰነዶች የማውደም፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪዎች የማዘዋወር፣የመንጠቅ፣ ይዞ የመገኘት፣ ብሔርን ከብሔር የማጋጨት፣ አመፅና ኹከት የማነሳሳት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩም ይገኙበታል።

 ማኅበራዊ ግንኙነት ሲያደርጉ የተያዙ ሰዎች ስለመኖራቸው በጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ታደሰ "ሰው ማኅበራዊ ግንኙነት እንዳያደርግ የተከለከለበት ሁኔታ የለም"ሲሉ ተናግረዋል። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ቅዳሜ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም በባሕርዳር ከተማ ተሰባስበው የግል ጉዳያቸውን ሲከውኑ የነበሩ የዩኒቨርስቲ መምህራንን እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ 19 ሰዎች መታሰራቸውን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

 በማግሥቱ እሁድ መጋቢት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ለቀድሞ እስረኞች በተዘጋጀ የምሥጋና መርኃ-ግብር መገባደጃ ላይ 11 ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተወስደዋል። በወቅቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ፖለቲከኛው አቶ አንዷዓለም አራጌ፣ ጋዜጠኞቹ እስክንድር ነጋ እና ተመስገን ደሳለኝ፣  ጦማሪያውያኑ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ማኅሌት ፋንታሁን እና ዘላለም ወርቅአገኘሁ ይገኙበታል። አቶ ታደሰ "እነዚህ ግለሰቦች የተያዙት ማኅበራዊ ግንኙነት ሲያደርጉ ነው አይደለም የሚለውን የምናይበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም" በማለት ድፍን ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። በይቅርታ ተፈተው ዳግም የታሰሩ ሰዎች "የታሰሩበት ቦታ እስካሁን ድረስ በዝርዝር ስላልደረሰን የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ አልጀመርንም" ሲሉም አክለዋል።

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

አዲስ አበባ ዙሪያን በሚያጠቃልለው አንደኛ ቀጠና 450 መታሰራቸውን ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ዘጠኝ ክፍለ ከተሞች፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ አምቦ፣ ፍቼ፣ ሞጆ፣ ቢሾፍቱ እና ዱከም መሆኑ ተገልጿል። ከባሌ ሮቤ፣ ምሥራቅ ሸዋ (አዳማ ከተማ) ፣ ምሥራቅ አርሲ እንዲሁም ከምዕራብ አርሲ በቁጥጥር ሥር የዋሉ 39 ሰዎች በአዋሳ በሚገኘው እና ቀጠና ሁለት ተብሎ በተደለደለው ኮማንድ ፖስት ይገኛሉ። አቶ ታደሰ እንደተናገሩት ቀጠና ሶስት ድሬዳዋ የታሰሩት 178 ሰዎች ሲሆኑ በቀጠና አራት ነቀምት ደግሞ 388  ተርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ይገኛሉ። በቀጠና 5 ባሕር ዳር 43 ሰዎች መታሰራቸውን የዘረዘሩት አቶ ታደሰ በቀጠና 6 ሰመራም ዘጠኝ ሰዎች በእስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል። የታሰሩ ሰዎች ዝርዝር ወደ ክልሎች እንደሚላክ የገለጹት ሰብሳቢው ክልሎች በበኩላቸው ዞኖች እና ወረዳዎችን የማሳወቅ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው አብራርተዋል። 

ተጠርጣሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪነሳ በእስር ሊቆዩ እንደሚችሉ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ተነግሯል። "አዋጁ የገደባቸው ብዙ መብቶች አሉ" ያሉት አቶ ታደሰ በምሳሌነትም ተጠርጣሪዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው መገደቡን አንስተዋል "ኮማንድ ፖስቱ እነዚህን ሰዎች ይዞ እስከ አዋጁ ፍፃሜ ሊያቆይ እንደሚችል፣ ምርመራ አድርጎ ወደ ሕግ ማቅረብ እንደሚችል እዚያም ሳይደርስ ደግሞ መክሮ መልቀቅ እንደሚችል አስቀምጦታል" ብለዋል።  

አቶ ታደሰ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወደ 130 ጥቆማዎች ለመርማሪ ቦርዱ ከሕብረተሰቡ እንደደረሰው ተናግረዋል። ሰብሳቢው ደርሰውናል ካሏቸው ጥቆማዎች መካከል "ሰዎች እየታሰሩ ያሉት በቂም በቀል ነው" የሚል ይገኝበታል። "በተለይም ከአመራር ጋር በኪራይ ሰብሳቢነት ሲደረግ በነበረው ትግል ቂም በቀል ተይዞ ዛሬ አዋጁን መነሻ በማድረግ ያለ አግባብ እየጠቆሙ እያሳሰሩ ነው በሚል የሚቀርቡ ጥቆማዎች አሉ" ሲሉ ተናግረዋል።  

Äthiopien vertriebene Moyale-Bewohner in der Oromia-Region
ምስል privat

ከተቋቋመ አንድ ወር ገደማ የሆነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ የእስረኞችን አያያዝ ከመርመር ባሻገር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ እንዳይሆኑ የመቆጣጠር እና የመከታተል ኃላፊነትም ተጥሎበታል። ባለፈው መጋቢት 19 በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ የተፈጸመውን ግድያ ቦርዱ መመርመር ጀምሮ ማቋረጡን አቶ ታደሰ አስታውቀዋል። በሞያሌ በተሳሳተ መረጃ ምክንያት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ 10 ሰዎች መገደላቸው እና 11 መቁሰላቸው ይታወሳል። ግድያውን ተከትሎ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ የሞያሌ ነዋሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ መሰደዳቸውም አይዘነጋም። 

አቶ ታደሰ ቦርዱ በሞያሌ ግድያ በተፈጸመበት ቦታ የጀመረውን ምርመራ ቢያቋርጥም ሙሉ ለሙሉ አለመሰረዙን አስረድተዋል። "ወደዚያ የምናደርገው ጉዞ ሌሎች ማዕከላትን በመለየት፣ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ለመፈጸም የሚያስችለንን ሌላ መርኃ-ግብር መቀየስ አስፈላጊ ስለሆነ መርኃ-ግብሩ እንዲዘገይ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው" ሲሉ ተናግረዋል። "ተጠያቂነት መረጋገጥ አለበት" ያሉት አቶ ታደሰ መርማሪ ቦርዱ ክትትል እንደሚያደርግ ገልጸዋል። 

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ