«መዝናኛ» መፅሔት
ዓርብ፣ ጥር 11 2010«መዝናኛ» ካናዳ ውስጥ በየሁለት ወሩ በአማርኛ ቋንቋ ታትሞ ለአንባቢያን የሚቀርብ መፅሔት ነው። የመፅሔቱ መስራች እና ዋና አዘጋጅ ዳንኤል ገብረማሪያም እንደሚለው መፅሔቱ ትኩረቱን ያደረገው ወጣቶችን በሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው። «ወጣቱ ባህሉን እና ማንነቱን እንዲያከብር ነው እኛ የምንፈልገው ይላል። ዳንኤል ይህንን መፅሔት እንዲጀምር የገፋፋው ሔኖክ አበጀ የተባለው ጓደኛው እንደሆነ ይናገራል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ አሌክሳንደር ሰማሁ ከተባለ ጓደኛው ጋር መፅሐፉን በጋራ ያዘጋጃል። መፅሐፋ መታተም ከጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። ዳንኤልም ሙሉ ትኩረቱን አሁን ወደ መፅሔቱ አድርጓል።
ዳንኤል «ተፅዕኖ ፈጣሪ» ናቸው የሚላቸውን እውቅ ኢትዮጵያውያን እንግዶቹ አድርጎል። ካናዳ ውስጥ በራሱ ቋንቋ የራሱን መፅሔት ማሳተም በመቻሉም ደስተኛ ነው። በመፅሄቱ የተለያዩ ርዕሶችን ለመዳሰስ ይሞክራል።
መፅሔቱ እስካሁን በሰሜን አሜሪካ ሲሆን ለገበያ የቀረበው ወደፊት ደግሞ ወደሌሎች አህጉሮች የማከፋፈል እቅድ እንዳለው ዳንኤል ይናገራል። ኢትዮጵያ ጃፓን እና አውስትራሊያ ሀገራት በአሁኑ ሰዓት ትኩረት አግኝተዋል።
«መዝናኛ» መፅሔት ታትሞ ብቻ ሳይሆን በዲጂታል መልክም ኢንተርኔት ላይ ይገኛል። አዘጋጁ ዳንኤል በካናዳ ሲኖር 10 ዓመታት ተቆጠሩ ፤ ኢትዮጵያ እያለም ከመገናኛ ብዙኃኑ ዓለም ብዙ አልራቀም ነበር።
በካናዳ «መዝናኛ» የተሰኘ መፅሔት መስራች እና ዋና አዘጋጅ ዳንኤል ገብረማሪያም ከዶይቸ ቬለ ጋር ያደረገውን ቆይታ መስማት ከፈለጉ የድምፅ መልዕክቱን ይጫኑ።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ