1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካርዛይና ዩናይትድ ስቴትስ

ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2006

ወታደሮቻቸውን አፍጋኒስታን ያዘመቱት የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO አባል ሃገራት ካርዛይ ውሉን በአስቸኳይ ካልፈረሙ ሃገሪቱ የሚሰጣት የእርዳታ ገንዘብ ይቋረጣል ሲሉ እየዛቱ ነው ። የሃገሪቱ የፀጥታ ጥበቃም አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ማስጠንቀቃቸውን ቀጥለዋል ።

https://p.dw.com/p/1ATrx
ምስል Getty Images/Afp/Shah Marai

የአፍጋኒስታኑ ፕሬዝዳንት ሃሚድ ካርዛይ ከአሜሪካን ጋር የፀጥታ ውል ላለመፈረም ማንገራገራቸው በአፍጋኒስታን ላይ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎችን አስከትሏል ። ወታደሮቻቸውን አፍጋኒስታን ያዘመቱት የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO አባል ሃገራት ካርዛይ ውሉን በአስቸኳይ ካልፈረሙ ሃገሪቱ የሚሰጣት የእርዳታ ገንዘብ ይቋረጣል ሲሉ እየዛቱ ነው ። የሃገሪቱ የፀጥታ ጥበቃም አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ማስጠንቀቃቸውን ቀጥለዋል ። ካርዛይ ግን ያስቀመጧቸው ቅድመ ግዴታዎች ሳይሟሉ ውሉን እንደማይፈርሙ አስታውቀዋል ። የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ NATO የአፍጋኒስታኑ ፕሬዝዳንት ሃሚድ ካርዛይ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የፀጥታ ውል በአስቸኳይ እንዲፈርሙ ግፊቱን አጠናክሯል ። ይህ አጠቃላይ የፀጥታ ጥበቃ ውል አብዛኛዎቹ የውጭ ኃይሎች አፍጋኒስታንን ለቀው ከሚወጡበት እጎአ ከ 2014 በኋላ የአሜሪካን ወታደሮች አፍጋኒስታን መቆየት የሚያስችላቸው ስምምነት ነው ። ዩናይትድ ስቴትስና የNATO ባለሥልጣናት በተቻለ ፍጥነት አፍጋኒስታን ውሉን እንድትፈርም ይፈልጋሉ ። ይህ ተግባራዊ ካልሆነ ወደፊት በአፍጋኒስታንን ለማከናወን የታቀዱትን ሥራዎች እንደሚታጎሉ NATO እያስጠነቀቀ ነው ። የNATO ዋና ፀሃፊ አንደርስ ፎግ ራስሙሰን ከትናንት በስተያ ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ እንደተናገሩት ካርዛይ ውሉን አለመፈረማቸው መዘዞች አሉት ።

Afghanistans Präsident Hamid Karzai
ካርዛይምስል Shah Marai/AFP/Getty Images

« ህጋዊ ስምምነቱ ካልተፈረመ ወታደሮችን አይሰፍሩም ፤ የታቀደው ድጋፍም ችግር ላይ መውደቁ አይቀርም ። »

ይሁንና የአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት ሃሚድ ካርዛይ ውሉን ለመፈረም በተደጋጋሚ ልዩ ልዩ ቅድመ ግዴታዎችን ከማስቀመጣቸውም በላይ ስምምነቱን በሚያዚያ በሚካሄደው ምርጫ ለሚተካው ፕሬዝዳንት እንደሚተዉ አስታውቀዋል ። የአፍጋኒስታንና የዩናይትድ ስቴትስ ውል የተዘጋጀው አንድ ዓመት ከፈጀ ውዝግብና ጭቅጭቅ በኋላ ነበር ። ከዚያን ወዲህ ካርዛይ ውሉን ከመፈረማቸው በፊት ተጨማሪ ቅድመ ግዴታዎችን አቅርበዋል ። ከነዚህም መካከል በኽዋንታናሞ እስር ቤት የተያዙት አፍጋናውያን እስረኞች በሙሉ እንዲለቀቁ የቤት ለቤት አሰሳን የሚያካትቱ አፍጋኒስታን ውስጥ የሚካሄዱ ወታደራዊ ዘመቻዎች እንዲቆሙ የሚሉት ይገኙበታል ። የNATO አባል ሃገር ጀርመን ካርዛይ በጊዜ መጫወታቸውን አቁመው ውሉን እንዲፈርሙ አሳስባለች ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዶ ቬስተርቬለ አፍጋኒስታን እርዳታ ለማግኘት የሚጠበቅባትን አሟልታ መገኘት እንዳለባት አስታውቀዋል ።

« ለኛ ግልፅ ነው ። ከ2014 በኋላም አፍጋኒስታንን ለመርዳት ዝግጁ ነን ። ለዛች አገር የሚቀርበው እርዳታ እንዲቀጥል ለማድረግ ቅድመ ግዴታዎች መሟላት አለባቸው ። በመሆኑም በመንግሥታቱ መካከል ለሚፈረመው የፀጥታ ትብብር ውል የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ በአንድነት መቆም አለባቸው ። »

Afghanistan Polizei Ausbildung
የአፍጋን ፖሊስ ሥልጠናምስል picture-alliance/dpa

ካርዛይ ውሉን በመገባደድ ላይ ባለው የጎርጎሮሳውያኑ 2013 መጨረሻ ማለትም እስከ ታህሳስ 22 ፣ 2006 ዓም ድረስ ካልፈረሙ የዩናይትድ ስቴትስም ሆነ የNATO አባል ሃገራት በጎርጎሮሳውያኑ 2014 መጨረሻ ወታደሮቻችን ሙሉ በሙሉ ከአፍጋኒስታን እናስወጣለን ሲሉ እየዛቱ ነው ። ይህ ብቻ አይደለም የውጭ ኃይሎች በብዛት ከአፍጋኒስታን ሲወጡ ከ 8 ሺህ እስከ 12 ሺህ የሚደርስ አሰልጣኝና አማካሪ ኃይል አፍጋኒስታን ውስጥ ለማስቀረት የተነደፈውን እቅድም እንሰርዛለን እያሉ ነው ። ራስሙሰን እንደሚሉት ሥልጠናው አለመሰጠቱ ችግር ሊያስከትል ይችላል ።

« አፍጋኒስታን ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የሚሰጥ ኃይል ማስፈር ካልተቻለ በሃገሪቱ የፀጥታ ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊያደርግ መቻሉ ያሳስበኛል ። ከዚህ በተጨማሪም አፍጋኒስታን በምታገኘው የገንዘብ እርዳታም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሊኖረው ይችላል ። »

በኔቶ ባለሥልጣናት አባባል የውጭ ኃይሎች ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ከወጡ አፋጋኒስታን በየዓመቱ ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የምታገኘውን 8 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ልታጣ ትችላለች ። የውሉን ሰነድ ሎያ ይርጋ የተባለው የአፍጋኒስታን አዛውንቶች ምክር ቤት ባለፈው ወር አፅድቆታል ። ካርዛይ ግን ከሚያዚያ ምርጫ በፊት አልፈርምም በሚለው አቋማቸው እንደፀኑ ነው ። በጎርጎሮሳውያኑ 2011 አሜሪካን ኢራቅ ውስጥ የተወሰኑ ወታደሮቿን ለማስቀረት የሚያስችል ውል ላይ ማግኘት ባለመቻሏ ወታደሮቿን ከኢራቅ ለማስወጣት መገደዷ ይታወቃል ። በአሁኑ ጊዜ አፍጋኒስታን የዘመተው ኔቶ መራሹ የውጭ ኃይል 84 ሺህ ይደርሳል ።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ