1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ካሌ ስደተኞች ጣብያ የተቀሰቀሰዉ ግጭትና የኮሮና ስጋት 

ዓርብ፣ ሚያዝያ 16 2012

ስደተኞች ወደ እንግሊዝ የሚሻገሩባት በፈረንሳይዋ ካሌ ከተማ በፖሊስና በስደተኞች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ። በሃገሪቱ የተጣለዉ ጊዜያዊ እገዳን ተከትሎ ስደተኞች ይሰጣቸዉ የነበረዉ የንፅሕና መጠበቅያ ቁሳቁስና የምግብ እርዳታ ተስተጓጉሎአል ፤ ፖሊስ የስደተኞቹን መጠለያ እያፈራረሰም ነዉ ተብሎአል። በመጠለያዉ እስካሁን 5 ስደተኞች በኮሮና ተይዘዋል።

https://p.dw.com/p/3bMgg
Belgien - Grenze zu Frankreich
ምስል picture-alliance/AA/D. Aydemir

5 ስደተኞች በኮሮና ተይዘዋል


በርካታ ስደተኞች ወደ ታላቋ ብሪታንያ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመሻገር የሚጠቀሙበት የሰሜናዊ ፈረንሳይ ወደብ ከተማ በሆነችዉ ካሌ በያዝነዉ ሳምንት በፖሊስ የፀጥታ አባላትና በስደተኞች መካከል ግጭት መነሳቱ ተነገረ። ከኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት ጋር ፈረንሳይ ዜጎችዋ በቤት ዉስጥ ተወስነዉ እንዲቀመጡ ጊዜያዊ እገዳ መጣልዋን ተከትሎ በካሌና አካባቢዋ የሚገኙ ስደተኞች ከዚህ ቀደም በሰብዓዊ ርዳታ ሰጭ ግብረሰናይ ተቋማት በኩል ይደረግላቸዉ የነበረዉ የንፅሕና መጠበቅያ ቁሳቁስና የምግብ እርዳታ በእገዳዉ ሳብያ መስተጓጎሎ የሰብዓዊ ቀዉስ እያስከተለ ነዉ።  በያዝነዉ ሳምንት ረቡዕ ደግሞ ፖሊስ ካሌ ዉስጥ ሕገወጥ ናቸዉ ያላቸዉን የስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ድንኳኖች ማፈራረስ መጀመሩ ትልቅ ግጭት ቀስቅሶአል። 
ፖሊስ ማፈራረስ የጀመረዉ የስደተኞች መጠለያ በአብዛኛዉ ከሱዳን የመጡ ስደተኞች የሚገኙበት ሲሆን በግጭቱ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ታዉቋል። ስደተኞች ያለበቂ ምግብ እና መጠለያ በሚኖሩበት ቦታ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት ስጋት መደቀኑ ሲነገር እስካሁን አምስት ስደተኞች በተኅዋሲዉ መያዛቸዉ ታዉቋል። 


ሐይማኖት ጥሩነህ 
አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ