1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከደም አፋሳሹ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታወጀ

እሑድ፣ ሰኔ 16 2011

የሐይማኖት አባቶች ባሕር ዳር ተጀምሮ ዳፋው አዲስ አበባ የዘለቀው ጥቃት አገሪቱን ወደ ባሰ አለመረጋጋት ሊከታት እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል። የመከላከያ ምኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ሰራዊቱን ለመከፋፈል የተደረገ ጥረት ሲሉ፤ የትግራይ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ዶ/ር ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል ተጨማሪ ግድያ ሊፈጸም ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው

https://p.dw.com/p/3KxaQ
Äthiopien  Seare Mekonnen
ምስል Addis Abeba city mayor office

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲሆን አወጀ። የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባቶች በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ በተፈጸሙት ጥቃቶች የተሰማቸውን ድንጋጤ እና ሐዘን በብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። የሐይማኖት አባቶቹ ጥቃቱ አገሪቱን ወደ ባሰ አለመረጋጋት ሊከታት እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

የሐይማኖት መሪዎቹ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ለችግሩ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ እና የሕዝቡን ሰላም እና ደሕንነት የማስከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ትናንት ምሽት በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ቢሮ በነበረው ተኩስ ርዕሰ-መስተዳድሩ ዶክተር አምባቸው መኮንን እና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ መገደላቸው ተረጋግጧል። የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ በጥይት ቆስለው ሕክምና እየተደረገላቸው ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በባሕር ዳር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን  እና በጡረታ ላይ የነበሩት ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ ተገድለዋል። ሁለቱ ወታደራዊ ሹማምንት በጄኔራል ሰዓረ መኮንን መኖሪያ ቤት በጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጠባቂ መገደላቸውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አረጋግጧል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም እንዳሉት ጥቃቱ የተፈጸመው ጄኔራል ሰዓረ በባሕር ዳር ከተማ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግሥት በመከታተል ላይ ሳሉ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ ነበር።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር እና የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ሊቀ-መንበር ዶክተር ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው ተጨማሪ ግድያ ሊፈጸም ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ጄኔራል ሰዓረ እና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ «ከጸረ- ሕዝብ፤ ከሌላ ጥቃት ይከላከልልኛል፤ ይጠብቀኛል» ባሉት ጠባቂ መገደላቸውን የገለጹት ዶክተር ደብረ ጺዮን ጥቃቱን «የተናጠል፤ የአንድ ጥበቃ ወንጀል ብለን አንወስደውም። ከባሕር ዳሩ ድርጊት ጋር የተያያዘ ነው» ብለዋል። ጄኔራል ሰዓረ በአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ባላቸው ኃላፊነት ምክንያት በዕቅድ የተያዘ ጥቃት ዒላማ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የመከላከያ ምኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ የተፈጸሙ ድርጊቶችን አውግዘዋል። አቶ ለማ ጥቃቱ የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ለመከፋፈል የተደረገ ጥረት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲ ማምሻውን ባወጣው የሐዘን መግለጫ በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ ጥቃት በመፈጸም አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የገደሉ ኃይሎችን በፅኑ አወገዟል። አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ያለው ኤምባሲው የጥቃቱ ፈፃሚዎች ድጋፍ ሊደረግላቸው አይገባም ብሏል።

የአሜሪካ ኤምባሲ በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ በአራት ሹማምንት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በተቋማቱ ላይ ጭምር የተሰነዘረ ነው ብሏል። የኢትዮጵያን አንድነት በከፋ ኹከት የሚፈታተኑ ኃይሎች የአገሪቱን ሕዝብ ጥቅም ጭምር እየሸረሸሩ ነው ሲል ኤምባሲው ዘግየት ብሎ ባወጣው የሐዘን መግለጫ አትቷል።

እሸቴ በቀለ