1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከስፖርቱ ዓለም

ሰኞ፣ መስከረም 14 2005

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና ባለፈው ሰንበትም አንዳንድ ማራኪ ግጥሚያዎች የታዩበት ነበር።

https://p.dw.com/p/16DR2
ምስል picture-alliance/dpa

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና ባለፈው ሰንበትም አንዳንድ ማራኪ ግጥሚያዎች የታዩበት ነበር። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺንና በስፓን ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና ያላንዳች ሽንፈት ወደፊት መገሰገሳቸውን ሲቀጥሉ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ሣምንቱ በሊቨርፑልና በማንቼስተር ዩናይትድ ግጥሚያ እጅግ የደመቀ ነበር።

በስፓኝ ሊ-ሊጋ እንጀምርና ባርሤሎና ግራናዳን 2-0 በመርታት አምሥተኛ ግጥሚያውንም በድል ሲወጣ የፕሪሜራ ዲቪዚዮኑ ቁንጮ እንደሆነ መቀጠሉ ተሳክቶለታል። በ 15 ነጥቦች አንደኛ ነው። ባርሣ ጎሎቹን በመጨረሻ ሰዓት ሲያስቆጥር በተለይም ሻቪ ግጥሚያው ሊያበቃ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ያስገባት ጎል እጅግ ግሩም ነበረች። በጨዋታው ማብቂያ ላይ ሁለተኛዋ ጎል የተቆጠረችው ደግሞ በራሱ በተሸናፊው ቡድን ነው።                         

Fußball FC Barcelona Mannschaft
ምስል Getty Images

ባርሣ እስካሁን በአምሥት ግጥሚያዎቹ 14 ጎሎችን ሲያስቆጥር የገባበት ሶሥት ብቻ ነው። ሁለተኛው ማላጋ ከአትሌቲኮ ቢልባኦ 0-0 ተለያይቶ በጎል ልዩነት ወደ ሶሥተኛው ስፍራ ወረድ ሲል ማዮርካ ቫሌንሢያን 2-0 በማሸነፍ በቦታው ተተክቷል። በአሥር ነጥቦች አራተኛው ደግሞ ሬያል ቫላዶሊድን 2-1 የረታው አትሌቲኮ ማድሪድ ሲሆን አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ አምሥተኛው ሬያል ቤቲስ ነው።                                                                     

ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ በአንጻሩ ጥሩ ጅማሮ አለማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በትናንቱ ምሽት ከራዮ ቫሌካኖ ጋር የነበረው ግጥሚያ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በአስተናጋጁ ክለብ ስታዲዮም መብራት መጥፋት ሳቢያ መሰረዙ ግድ ሆኗል። ሬያል ማድሪድ እስካሁን ባካሄዳቸው አራት ግጥሚያዎች አራት ነጥቦች ብቻ ሲኖሩት አሁን በሊጋው አሰላለፍ 17ኛ ነው። ምናልባት ትናንት የተሸጋሸገው ግጥሚያ በዛሬው ምሽት ሲካሄድ በማሸነፍ ወደ ዘጠነኛው ቦታ ከፍ ማለቱ ይሳካለት ይሆናል። 

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቼልሢይ  ስቶክ ሢቲይን 1-0 ሲረታ በአምሥት ግጥሚያዎች 13 ነጥቦችን በመሰብሰብ በአመራሩ ቀጥሏል። የሊጋው ታላቅ ግጥሚያ ትናንት በአንፊልድ ስታዲዮም በሊቨርፑልና በማንቼስተር ዩናይትድ መካከል ሲካሄድ ይህም በሂልስቦሮህ ስታዲዮም 96 ተመልካቾች የሞቱበት አሳዛኝ ሁኔታ የታሰበበት ነበር። ከ 23 ዓመታት በፊት በሼፊልዱ ሂልስቦሮህ ስታዲዮም ከተመልካች ከመጠን በላይ መብዛት የተነሣ በተፈጠረ መጨናነቅ ሳቢያ በተለይም የሊቨርፑል ደጋፊዎች ተጨፍልቀውና ተረጋግጠው ሕይወታቸውን ሲያጡ አደጋው በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አስከፊው ሆኖ የሚታወስ ነው።                                                                      

Hillsborough Liverpool Desaster Unglück
ምስል picture-alliance/dpa

የሊቨርፑልና የማኒዩ ግጥሚያ ትናንት አምበሎቹ  ስቲቭን ዤራርድና ራያን ጊግስ ሟቾቹን በማሰብ 96 ባሎኖችን ወደ አየር ከለቀቁ በኋላ ሲካሂድ ጨዋታው የኔዘርላንዱ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ሮቢን-ፋን-ፐርሢ ባስቆጠራት የዘገየች ፍጹም ቅጣት ምት ነበር በማኒዩ አሸናፊነት 2-1 የተፈጸመው። ማንቼስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን ሲያሸንፍ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በዚህ ውጤት ከቼልሢይ በአንዲት ነጥብ ብቻ ወረድ ብሉ ሁለተኛ ነው።                                                                             

ያለፈው ጊዜ ሻምፒዮን ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ ከአርሰናል 1-1 ሲለያይ አርሰናል ወደ አምሥተኛው ቦታ ከፍ ብሏል። ፉልሃም በእኩል ነጥብ ስድሥተኝነቱን ሲይዝ ማንቼስተር ሢቲይም በተመሳሳይ ዘጠን ነጥብ ሆኖም በጎል በመበለጥ ሰባተኛ ነው።                     

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር  አራተኛው ሣምንት ሲገባደድ ሬኮርድ ሻምፒዮኑ ባየርን ሙንሺን በአራተኛ ግጥሚያውም  ሻልከን 2-0 አሸንፎ በመመለስ በፍጹም የበላይነቱ ቀጥሏል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ቶኒ ክሮስና ቶማስ ሙለር ነበሩ። ቡድኑ ሁለት ጎሎች ብቻ ገብተውበት 14 ሲያስቆጥር ጥንካሬውን ያዩት ተፎካካሪዎቹ ከወዲሁ ሻምፒዮን እንደሚሆን እየተነበዩለት ነው።

Fußball Bundesliga 4. Spieltag 1. FC Nürnberg - Eintracht Frankfurt
ምስል picture-alliance/dpa

ከሁለተኛው ዲቪዚዮን የወጣው አይንትራህት ፍራንክፉርትም በአራተኛ ግጥሚያው ኑርንበርግን 2-1 አሸንፎ እኩል 12 ነጥብ ሲይዝ በባየርን በአምሥት ጎሎች በመበለጥ ሁለተኛ ነው። ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን ዶርትሙንድ በአንጻሩ በ 31 ግጥሚያዎች ሲያሸንፍ ከቆየ በኋላ ባለፈው ሰንበት ለሃምቡርግ መንበርከኩ ግድ ሆኖበታል። ዶርትሙንድ በሃምቡርግ 3-2 ተሸንፎ ከስሜን ጀርመን ሲመለስ አሁን በሰባት ነጥቦች ከሃኖቨር ቀጥሎ አራተኛ ነው። የጀርመን ቡንደስሊጋ ክለቦች በዚህ ሣምንት ነገና ከነገ በስቲያ እንዲሁም በመጪው ሰንበት ድርብ ግጥሚያዎች ይጠብቋቸዋል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ጁቬንቱስ ቬሮናን 2-0 ሲያሸንፍ ከአራት ግጥሚያዎች በኋላ ሙሉ 12 ነጥቦችን ይዞ በመምራት ብቸኛው ነው። እንደ ጁቬንቱስ ሁሉ ቀደም ባሉ ሶሥት ግጥሚያዎቻቸው አሸንፈው የነበሩት ናፖሊና ሣምፕዶሪያ በእኩል ለእኩል ሲወሰኑ ላሢዮ እንዲያውም በሜዳው  በጌኖዋ 1-0 ተረትቷል። ሁለቱ የሚላኖ ክለቦች ኢንተርና ኤሲም ሰንበቱን ያሳለፉት በሽንፈት ነበር።  ጁቬንቱስ፣ ናፖሊ፣ ላሢዮ፣  ሣምፕዶሪያ፣ ፊዮሬንቲና ኢንተር ሚላን፤ በወቅቱ ከአንድ እስከ ስድሥት የሚከታተሉት ክለቦች እነዚህ ናቸው።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ኦላምፒክ ማርሤይ በስድሥተኛ ግጥሚያውም በማሸነፍ ሊጋውን በአራት ነጥቦች ልዩነት ከመምራት ባሻገር ከሃምሣ ዓመት በላይ በሆነ የሊጋው ታሪክ አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዝግቧል። ማርሤር ኤቪያን ዤይላርድን 1-0 ሲያሸንፍ ከሊል 1-1 የተለያየው ኦላምፒክ ሊዮን በ 14 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ፓሪስ-ሣንት-ዠርማንና ሎሪየንት ሁለት ነጥቦች ወረድ ብለው ይከተላሉ። በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮንም ሁኔታው ተመሳሳይ ሲሆን ትዌንቴ ኤንሽድ በስድሥት ግጥሚያዎቹ በሙሉ በማሸነፍ አንደኛ ነው፤ አርንሃይም በ 14፤ አያክስ አምስተርዳምና አይንድሆፈንም ደግሞ በ 12 ነጥቦች ተከታዮቹ ናቸው። በተቀረ ፖርቶ ቤንፊካ ሊዝበንን በማስከተል የፖርቱጋልን ሻምፒዮና ቀደምት ሆኖ እየመራ ነው።

Formel 1 Grand Prix in Singapur Vettel
ምስል REUTERS

ፎርሙላ-አንድ

በትናንትናው ዕለት ሢናጋፑር ውስጥ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል አሸናፊ ሆኗል። ባለፈው ዓመትም በዚያው ስፍራ አሸናፊ የነበረው ፌትል የብሪታኒያውን ጄሰን ባተንንና የስፓኙን ፌርናንዶ አሎንሶን ቀድሞ ከግቡ ሲደርስ በአጠቃላይ ነጥብ አሎንሶን በ 29 ነጥቦች ልዩነት ለመቃረብ በቅቷል። ፌትል በዘንድሮው ውድድር ካለፈው ሚያዚያ የባህሬይን እሽቅድድም ወዲህ ሲያሸንፍ የትናንቱ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።             

ውድድሩ ሊገባደድ ስድሥት እሽቅድድሞች ቀርተው ሳለ አሎንሶ በአጠቃላይ 194 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ፌትል በ 165 ሁለተኛ፣ የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን በ 149 ሶሥተኛ፤እንዲሁም ትናንት እሽቅድድሙን ማቋረጥ ግድ የሆነበት ሉዊስ ሃሚልተን በ 132 ነጥቦች አራተኛ ነው። የሚቀጥለው እሽቅድድም ከ 13 ቀናት በኋላ ጃፓን ውስጥ ይካሄዳል።   

Roger Federer US Open 2012
ምስል dapd

ቴኒስ

ጃፓን ውስጥ በሚካሄደው ፓን-ፓሲፊክ-ኦፕን የዓለም ቴኒስ ማሕበር የሴቶች ውድድር የመጀመሪያው ዙር ተጠናቆ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ተጫዋቾች ወደ ሁለተኛው ዙር አልፈዋል። ፈረንሣዊቱ ማሪዮን ባርቶሊ አገሬዋን ኪሚኮን 6-1,6-4 ስታሸንፍ የሰርቢያ አና ኢቫኖቪች ቼኳን አንድሬያ ሃቫኮቫን 6-3,6-2፤ ሩሢያዊቱ  ናዲያ ፔትሮቫ  ቻይናዊቱን ፔንግ ሹዋይን 6-1,6-4፤ የፖላንዷ ኡርሱላ ራድዋንስካ ጃፓናዊቱን ኩሩሚ ናራን 6-2,6-4፤ የጀርመኗ ዩሊያ ጎርገስ ሩሜኒያዊቱን ሞኒካ ኒኩሌስኩን  6-3,6-2 ረትታለች።

በማሊይዚያ የወንዶች ነጠላ ውድድር ደግሞ ዛሬ በተካሄዱ የመጀመሪያ ግጥሚያዎች የካናዳው ቫሤክ ፖስፒሲል የአውስትሪያውን ዩርገን ሜልትሰርን፤ የታይዋኑ ጂሚ ዋንግ የኢጣሊያ ተጋጣሚውን ሪካርዶ ጌዲንን፤ እንዲሁም የኔዘርላንዱ ኢጎር ሢይስሊንግ የማሌዚያን አሪስ-ደን-ሃሻምን በማሸነፍ ወደ ተከታዩ ዙር ተሻግረዋል። በተረፈ ዛሬ በወጣ አዲስ መረጃ መሠረት የስዊሱ ሮጀር ፌደረር በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱን ቦታ እንደያዘ ይቀጥላል። ፌደረር በ 11,805 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች በ 10,470 ነጥቦች ሁለተኛ ነው፤ የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ደግሞ በ 8,570 ነጥቦች ሶሥተኛ ሆኖ ይከተላል።

የቀድሞው የቡጢ የዓለም ሻምፒዮን ኮርኔሊዩስ ሣንደርስ ሳይታሰብ በታጠቁ ወንበዴዎች ቆስሎ መሞት የስፖርቱን አፍቃሪዎች በጣሙን አሳዝኗል። የደቡብ አፍሪቃው የአንዴ የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን ትናንት ማለዳ ላይ ያረፈው ቀደም ሲል ብሪትስ በተሰኘች  የሰሜን-ምዕራባዊው ክፍለ-ሐገር መንደር በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ የቤተሰብ ልደትን በማክበር ላይ እንዳለ በጥይት ክንዱና ሆዱ ላይ ተመትቶ ከቆሰለ በኋላ ነው። የ 46 ዓመቱ ሣንደርስ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ያሳዝናል ሊተርፍ አልቻለም። 

የታጠቁት ሶሥት ወንበዴዎች የተሰበሰበውን ሰው የኪስ ቦርሣና ሞባይል ስልኮች፤ እንዲሁም የተሽከርካሪ ቁልፎች ዘርፈው ሲሰወሩ ፖሊስ ፍለጋ በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል። በግራ ዕጅ ምቱ ብርቱነት «ስናይፐር» አነጣጥሮ መቺው የሚል ቅጽል ተሰጥቶት የነበረው ሣንደርስ በጎርጎሮሳውያኑ 2003 ዓመተ-ምሕረት ባልተጠበቀ ሁኔታ የኡክራኒያውን ቭላዲሚር ክሊችኮን በመዘረር የዓለም ቡጡ ማሕበር ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል። በሕይወቱ ካካሄዳቸው 46 ፕሮፌሺናል ግጥሚያዎች የተሸነፈው በአራቱ ብቻ ነበር። በርከት ያሉ አድናቂዎቹና መሰል የሙያ ባልደረቦቹ በትናንትናው ዕለት የሃዘን መግለጫቸውን ሲያስተላልፉ ውለዋል።     

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ