ኦሳማ ቢን ላደንና አልቃይዳ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 27 2008
ኦሳማ ቢን ላደን ከመጀመሪያው አንስቶ የአሸባሪው ቡድን የአልቃይዳ መሪ ነበር ። ድርጅቱን አልቃይዳ ሲል የሰየመውም ሆነ አፍጋኒስታን የበሩ ተዋጊዎችንም በገንዘብ ይደግፍ የነበረውም እርሱ ነው ። ኦስማ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የወጣው በ1980 ዎቹ አፍጋኒስታን ከነበረው የሶቭየት ህብረት ጦር ጋር ጦርነት በተካሄደበት ወቅት ነው ። ያኔ የአረብ ተዋጊዎች አፍጋኒስታን የሚገኙ በእምነት አንድ የሆኑ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ህብረት ፈጠሩ ። ለብዙ ጊዜያት ልል ሆኖ የቆየው ይህ የጂሃዲስቶች ህብረት በኦሳማ ቢን ላደንና በሁለተኛው ሰው በአይማን አል ዛውሃሪ በጎርጎሮሳዊው 1997 ዓለምን ስጋት እና ሽብር ውስጥ ወደከተተው ወደ «አልቃይዳ» ተቀየረ ። ከዚያም የአልቃይዳ ማሰልጠኛ ካሞፖች ተገንብተው ቢን ላደን በሙስሊሙ አለም የምዕራባውያንን ተጽእኖ ለመታገል የሚያካሂደው ትግል የጂሃዲስቶች ትግል ሆነ ። ድርጅቱ ከተቋቋመ ከ4ዓመታት በኋላ ቢን ላደን ጥንካሬውን ለዓለም ያሳየበትን እጅግ አደገኛ የሽብር ጥቃቶች በጎርጎሮሳዊው መስከረም 11 2001 አም በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጣለ ። ከዚያም አሸባሪዎችን ለመቅጣት የአሜሪካን የአፀፋ ጥቃት ተከተለ ።በዚያው አመት አሜሪካን አልቃይዳንና ታሊባንን ለመውጋት ጦርዋን አፍጋኒስታን አዘመች ። ቢን ላደንና ተዋጊዎቹም ወደ ሰሜን ፓኪስታን አፈገፈጉ ። የአልቃይዳ ሚሊሽያዎችም በአንዳንድ የአፍጋኒስታንና የፓኪስታን ክፍሎች ጠንካራ ይዞታቸውን አጡ ። ከዚያ በኋላም ቢን ላደን አብዛኛውን የድርጅቱን ሥራና በየቦታው ለተበታተኑት ጂሃዲስት ቡድናት የሚተላለፈውን መልዕክት ለምክትሉ ለዛዋሀሪ ትቶ ተሰወረ ። አል ቃይዳ በኢራቅ ውስጥ ተጠናክሮ መንቀሳቀስ የጀመረው ደግሞ አሜሪካን በ2003 ዓም ኢራቅን ከወረረች በኋላ ነው ። አፍጋኒስታን ውስጥ ለብዙ አመታት የተዋጋው አቡ ሙሳብ አል ዛርካዊ ከተባባሪዎቹ ጋራ ኢራቅ ውስጥ ያለውን በጣም ጨካኙን ቅርንጫፍ ድርጅት መሪነት ያዘ ። የቢን ላደን ትግል ከምዕራባውያኑና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ነበረ ። ሺአዎችን እንደሚጠላ ይነገርለት የነበረው ዛርካዊ በሺአ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ያደርስ ስለነበረ ይህን እንዲያስተካክል ቢጠየቅም ውጤት አልተገኘም ። በበርሊኑ የሳeineስና የፖለቲካ ጉዳዮች ጥንate ተቋም የሽብር ጉዳዮች አዋቂ ጊዶ ሽታይንበርግ እንደሚሉት በዚህ የተነሳ ዛርካዊ እና ቢን ላደን ይጋጩ ነበር ። ለዚህም እንደ አብነት ያነሱት በአንድ ወቅት ከአልቃይዳ አመራር ለዛርካዊ የተፃፈውን ደብዳቤ ነው ።
«ዝዋሃሪ ፣ ዛራካዊ ስልታዊ ለውጥ እንዲያደርግ የሞከረበትን ዝነኛ ደብዳቤ በጎርጎሮሳዊው 2005 ዓም ጽፎለት ነበር ይሄ ደብዳቤ ምንም ያመጣው ነገር የለም ። ይህም የኢራቁ አልቃይዳ በራሱ ፍላጎት የሚንቀሳቀስ መሆኑን ነው የሚያሳየው ።
አቡ ሙሳ ዛርካዊ በ2006 ዓም በአሜሪካኖች ጥቃት ተገደለ ። የኢራቁ አልቃይዳ ከዛርካዊ ሞት በኋላ ቢዳከምም ፈፅሞ አልጠፋም ። ከአምስት ዓመት በኋላም የአልቃይዳው መሪ ኦስማ ቢን ላደን በተደበቁበት ፓኪስታን ውስጥ በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 2 2011 ዓም በዩናይትድ ስቴትስ ተገደሉ ።ይህንንም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለህዝባቸውና ለዓለም ይፋ አደረጉ ።
« ዛሬ ለአሜሪካን ህዝብ እና ለዓለም ዩናይትድ ስቴትስ የአልቃይዳ መሪና በሺህዎች ለሚቆጠሩ ወንዶች ሴቶችና ህፃናት ግድያ ተጠያቂ የሆነው ኦሳማ ቢንላደን የተገደለበትን ዘመቻ ማካሄዷን አሳውቃለሁ ። »
የዛሬ አምስት ዓመት የተገደለው ኦሳማ ቢን ላደን ምንም እንኳን መንፈሳዊ መሪ ነኝ ብሎ ባይናገርም ሽታይንበርግ እንዳሉት በተከታዮቹ ዘንድ ሃይማኖትና ፖለቲካን አጣምረው እንደያዙት ጥንታዊ መሪዎች ከፍተኛ ተቀባይነት ክብርና ግርማ ሞገስ ነበረው ። እሱን የተካው ዛዋሃሪ ግን በቀጣዮቹ አመታት ጂሃዲስቶችን እንደ ቢንላደን ማነሳሳት አልቻለበትም ። እንደ ሽታይንበርግ ይህም ከአውሮጳና ከመላው ዓለም የተሰባሰቡት የአልቃይዳ ወጣት ተዋጊዎች ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራውን ቡድን የተቀላቀሉበት አንዱ ምክንያት ነው ። በአሁኑ ጊዜ ከአልቃይዳ ይልቅ በዓለማችን በአሸባሪነት ትልቁን ቦታ የያዘው ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ይኸው ቡድን ነው ።
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ