1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አብዛኞቹ ስደተኞች እስራኤልን መልቀቅ አይፈልጉም

ማክሰኞ፣ ጥር 29 2010

እስራኤል በሀገሯ የሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች በ60 ቀናት እስራኤልን ለቅቀው እንዲወጡ የሚያሳስብ ደብዳቤ ባለፈው እሁድ ማደል ጀምራለች፡፡ ስደተኞቹ በሁለት ወራት ውስጥ ከእስራኤል ካልወጡ እስራት እንደሚጠብቃቸውም አስጠንቅቃለች፡፡ 

https://p.dw.com/p/2sDCq
Israel eritreische Flüchtlinge demonstrieren in Jerusalem
ምስል picture-alliance/dpa/I. Yefimovich

አብዛኞቹ እስራኤልን መልቀቅ አይፈልጉም

በብዛት ኤርትራውያን እና ሱዳንውያን የሆኑት ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ከመመለስ ይልቅ እስርን እንደሚመርጡ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት ሀገራቸውን በፖለቲካ ምክንያት ለቅቀው መውጣታቸውን ነው፡፡ እስራኤልን ግን ስደተኞቹ ስራ ፈላጊዎች እንጂ ተገን ጠያቂዎች አይደሉም ስትል ትከራከራለች፡፡ ሀገሪቱ ወደ 40 ሺህ የሚጠጋውን ስደተኛ የማስተናገድ አቅም የላትም ሲሉ የእስራኤል ባለስልጣናት ሲገልጹ ይደመጣል፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ግን ሀገሪቱ ስደተኞቹን ለማስጠለል ያጣቸው “አቅም ሳይሆን የፖለቲካ ፍላጎት ነው” ይላሉ፡፡ 

ስደተኞችን ከሀገር የማስወጣቱ አወዛጋቢው የእስራኤል እቅድ በሀገሪቱ የመብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቃውሞ እንደገጠመው ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡ የተወሰኑ ቡድኖች እንደውም ስደተኞችን በቤታቸው ለማስጠጋት ሁሉ ፍቃደኝነታቸውን በይፋ አሳውቀዋል፡፡ ይህም በእስራኤል ውስጥ መከፋፈል መፍጠሩ እየተነገረ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ግፊት “የእስራኤል መንግስት የያዘውን አቋም ያስቀይር ይሆን?” ለሚለው ጥያቄ ግን የሀገሪቱ ነዋሪዎች እና ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች አሉታዊ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

የእስራኤልን እርምጃ እና የስደተኞቹን ምላሽ አስመልክቶ ከኢየሩሌሙ ዘጋቢያችን ዜናነህ መኮንን ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡ ሙሉ ቃለ ምልልሱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ፡፡    

ዜናነህ መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ

ሂሩት መለሰ