1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢራቅ እና የዩኤስ አሜሪካ ጦር ኃይላት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 23 2001

በኢራቅ የተሰማራው የዩኤስ አሜሪካ ጦር ኃይል የሀገሪቱን ከተሞች ጸጥታ ቁጥጥር ዛሬ ለኢራቃውኑ አስረከበ።

https://p.dw.com/p/IeJJ
ምስል AP

በዩኤስ አሜሪካ እና በኢራቅ መካከል በተደረሰ ስምምነት መሰረት ዩኤስ አሜሪካ በዚያ ከሚገኙት ወታደሮችዋ መካከል 130,000 ዎቹ እስከዛሬይቱ ዕለት ድረስ ከሀገሪቱ ከተሞችና መንደሮች መውጣትና ወደጦር ሰፈራቸው መመለስ አለባቸው። ብዙዎቹ አሜሪካውያን ወታደሮችም እአአ እስከ ቀጣዩ ነሀሴ 31 ፡ የመጨረሻዎቹ ደግሞ እአአ እስከ 2011 ዓም ድረስ ኢራቅን ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ታዛቢዎች ይህንኑ ሁኔታ የስድስት ዓመቱ ያሜሪካውያን ወረራ የሚያበቃበት የመጀመሪያ ርምጃ አድርገው ተመልክተውታል። ታድያ ይህ፡ አሜሪካውያኑ ከወጡ በኋላ ኢራቅ ብቻዋን የሀገርዋን ጸጥታ እና መረጋጋት ማረጋገጥ ትችል ይሆን የሚለውን ጥያቄ አስነስቶዋል።

የአሜሪካውያኑ ጦር ከመላ ኢራቅ መውጣት ኢራቃውያኑ እአአ ከ 2003 ዓም የዩኤስ አሜሪካ ወረራ ወዲህ የግዛት ሉዓላዊነታቸውን ለማረጋገጥ ባካሄዱት ደም አፋሳሹ ትግላቸው ላይ እንደተገኘ ዋነኛ ርምጃ ታይቶዋል። ምንም እንኳን ባለፉት ቀናት በአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃቶች ከሁለት መቶ የሚበልጡ ኢራቃውያን ቢገደሉም፡ የኢራቅ ጠቅላይ ሚንስትር ኑሪ አል ማሊኪ በመላ ሀገሪቱ ብሄራዊ በዓል ሆኖ የተከበረውን የዛሬውን ዕለት ትልቅ ድል የተመዘገበበት ዕለት ብለውታል። አንዳንዶች ኢራቃውያን ለዚህ ተግባር ገና አልተዘጋጁም በሚል ያሰሙትንም ጥርጣሬ ማሊኪ ውድቅ በማድረግ የኢራቅ ብሄራዊ የጦር ኃይልና ፖሊስ በኢራቅ ጸጥታ የማስከበሩን ኃላፊነት በሚገባ እንደሚወጡ አስታውቀዋል። በኢራቅ የሚገኙት አሜሪካዊው ዋና የጦር አዛዥ ሬይ ኦዲየርኖም የሀገራቸው ወታደሮች የኢራቅ ከተሞችን ቁጥጥር ማብቃታቸው ትክክለኛ መሆኑን አስረድተዋል።

« ኃላፊነቱን ለኢራቃውያኑ የምናስረክብበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። »

ከዛሬ ጀምረው በመዲናይቱ ባግዳድ ብቻ ወደ 130,000 የኢራቅ ወታደሮች የጸጥታ ጥበቃ ቁጥጥር ስራ ያከናውናሉ። ኢራቅ ውስጥ በጠቅላላ 500,000 ወታደሮችና 250,000 ፖሊሶች ህግና ስርዓት ያስከብራሉ።

ምንም እንኳን የሺአ እምነት መስመር ተከታዮቹ ኢራቃውያን ሳዳም ሁሴን ከስልጣን በተወገዱበት ያሜሪካውያን ወረራ ብዙ ጥቅም ቢያገኙም፡ በተለይ ብዙዎቹ የሺአ ፖለቲከኞች ባሜሪካውያኑ ጦር መውጣት በጣም ተደስተዋል። በአንጻራቸው አሜሪካውያኑ የጦር ኃይላት ያካባቢ ጎሳዎችን በማስተባበር ለወትሮው ሁከት ይታይባቸው የነበሩ የሱኒ ክፍላተ ሀገርን ሊያረጋጉ ቢችሉምና እአአ ከ 2006 ዓም ወዲህ የተጣሉ ጥቃቶች ቁጥር በጉልህ ቢቀንስም፡ የሱኒ ኢራቃውያን ባሜሪካውያኑ ወታደሮች መውጣት አኳያ ስጋት አድሮባቸዋል።

በርካታ የምክር ቤት እንደራሴዎች ግን ብሩህ አመለካከት ነው ያላቸው። ለምሳሌ ለዘብተኛውን የሺአ እንደራሴ አያድ ዣማሌዲ የሀገራቸው ጦር ኃይላት ኢራቃውያንን ደህንነት መጠበቅ እንደሚችሉ እርግጠኛ ናቸው።

« የኢራቅ ጸጥታ አስከባሪ ኃይላት የከተሞችን ጸጥታ የማረጋገጥ አቅም አላቸው። እንዲያውም፡ ህዝቡንና አካባቢውን በይበልጥ ስለሚያውቁት የብዙ መንግስታት ወታደሮች ከተጠቃለሉበት የጦር ኃይል የበለጠ ስራ ሊያካሂዱ ይችላሉ። »

ይሁንና፡ የኢራቅን ጦር ኃይላት የሚጠብቃቸው ስራ ቀላል እንደማይሆን እንደራሴዎቹ አልዘነጉትም። እንደራሴው ዣማሌዲን አስተያየት መሰረት፡ በተለያዩት የፖለቲካ፡ የጎሳና የሀይማኖት ቡድኖች መካከል የሚካሄደው የስልጣን ሽኩቻ ብቻ ሳይሆን፡ የተለያዩት መንግስታት ያሳረፉትም ተጽዕኖ ድርሻ አበርክተዋል።

« ትልቁ ፈተና የተደቀነው ከሀገር ውስጥ የፖለቲካ ፍክክር እና ያካባቢ ኃይላት በኢራቅ ላይ ከሚያሳርፉት ጣልቃ ገብነት ነው። »

ኢራን፡ ሶርያ፡ ሳውዲ ዐረቢያና ሌሎች ያካባቢ ኃይላት በኢራቅ ተጽዕኖዋቸውን ለማስፋፋት ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ይህንኑ ጥረታቸውን ለማሳካቱ ተግባር በኢራቅ ከሚያፈሱት ገንዘብ መካከልም ከፊሉ ሀገሪቱን መረጋጋት ሊያናጉ ወይም የብሄራዊውን ጸጥታ ኃይላት ሊያዳክሙ ይችላሉ ለሚባሉት ሚሊሺያዎች እንደሚሰጥ ያደባባይ ምስጢር ነው።

ሀሰን ሁሴን/አርያም አብርሀ

ተክሌ የኋላ