አፍሪቃ እና አንደኛ የጋዳፊ ሙት ዓመት
ዓርብ፣ ጥቅምት 9 2005ራሳቸውን «የአብዮት መሪ ወንድም» ወይም « የነገስታት ንጉስ» እያሉ ይጠሩ የነበሩት ሙአመር ኧል ጋዳፊ ብዙ ገፅታዎች ነበሩቸው። ለምዕራብ አገሮች ጋዳፊ፣ አምባገነን፣ ጨካኝ እና ከማህበራዊ ወግ ያፈነገጡም ነበሩ። ጋዳፊ ከተገደሉ ከአንድ አመት በኋላ አፍሪቃ ውስጥ በምን ይታወሳሉ?የዮጋንዳ የመንግስት ቃል አቀባይ ፍሬድ ኦፖሎት« ጋዳፊ ለብዙ አመታት የዮጋንዳ ወዳጅ ነበሩ። በዮጋንዳ ጸረ ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ ውስጥ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ጋዳፊ በዮጋንዳ ታሪክ ውስጥ አንድ ቦታ ይኖራቸዋል።»
በአጠቃላይ 375 ሚሊዮን ዶላር ጋዳፊ ዮጋንዳ ላይ አፍሰዋል። ከነዳጅ ሽያጭ የተገኘውን የሊቢያ ገንዘብ ፤ በዮጋንዳ ቴሌኮሚኒኬሽን ድርጅት እና ትሮፒካል ባንክ ላይ ውሏል።በዮጋንዳ መዲና ካምፖላ በጋዳፊ ስም የተሰየመ መንገድ እና መስጊድ ይገኛል። ጋዳፊ የአፍሪቃ ምጣኔ ሀብትን የሚያወድሱ ሰው ነበሩ። በመላው አህጉር የሊቢያ መዋለ ንዋይ ይታያል። በኬንያ እና ጋና ቅንጡ ሆቴሎች፣በላይቤሪያ ፤ የጎማ ዛፍ ፋብሪካዎች ፣ በጊኒ የፍራፍሬ ምርት እንዲሁም በምስራቅ አፍሪቃ የቴሌኮሚኒኬሽን እና ነዳጅ ማዲያዎች የሚጠቀሱ ናቸው።
ይሁንና በሊቢያ አብዮት ጊዜ የአፍሪቃ ሀገራት የተመድ የመፍትሄ ሀሳብን በመከተል ጋዳፊ እና ቤተሰባቸው በውጭ ሀገር ያላቸው ሀብት እንዲታገድ ነበር የተስማሙት። እርግጥ ዛሬ ይህ ማዕቀብ ተነስቷል። የሊቢያ የመዋዕለ ንዋይ መስሪያ ቤት LIAም በአገልግሎት ላይ ይገኛል። የመንቀሳቀሻ ገንዘቡ ግን ከሊቢያ አመፅ በፊት የተገኘ ነው። አዲሱ የሊቢያ መንግስት የት እና ምን ያህል ገንዘብ በውጭ ሀገር ዛሬም ተሸሽጎ እንደሚገኝ አያውቅም።
ለበርካታ የአፍሪቃ ሀገራት የጋዳፊ ሞት ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ነው ይላሉ የምዕራብ አፍሪቃ ተንታኝ ሰባስቲያን እስፒኦ ጋርብራህ።« በርካታ የአፍሪቃ ሀገራት በሊቢያ የንግድ ተሳትፎ ደስተኞች አይደሉም። አብዛኞቹም መዋለ ንዋዩን ለአዲሱ የሊቢያ መንግስት አላስረከቡም። ምንም እንኳን በዲሞክራሲያዊ አሰራር አዲሱን መንግስት ቢቀበሉም፤ ድርሻቸውን ገና አላስረከቡም። »
አክለውም ተንታኙ አንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራት እንደውም በሊቢያ ካለው አለመረጋጋት አትራፊ እንደሆኑም ገልፀዋል። ከጋዳፊ ግድያ አንድ አመት በኃላ አዳዲስ ሰዎች ወደ አፍሪቃ ህብረት መድረክ እየተቀላቀሉ ነው። በእንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ኃላፊነት ደቡብ አፍሪቃ በአፍሪቃ ህብረት የበለጠ ድምፅ ሊኖራት ይችላል። በምጣኔ ሀብታዊ ምዋለ ንዋዩም በኩል ቢሆን አዳዲስ እንደ ቻይና ያሉ አገሮች ይገኛሉ። መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው እና 200 ሚሊዮን ዶላር ያወጣው የአፍሪቃ ህብረት የቻይና ሽልማት ነው።
ቬራ ኬርን
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ