1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አይ ሲ ሲ» እና የቀድሞው የኮንጎ ሚሊሺያ መሪ ብይን

ቅዳሜ፣ የካቲት 29 2006

ዘ ሄግ ፣ ኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የጦር ባላባት ጀርሜን ካታንጋን እአአ የካቲት 24፣ በ2003 ዓም በአንድ መንደር 200 ሰዎች አንድም በስለት ተጨፍጭፈው ወይም በጥይት

https://p.dw.com/p/1BLzp
Niederlande Germain Katanga Internationaler Strafgerichtshof Den Haag
ጀርሜን ካታንጋምስል Michael Kooren/AFP/GettyImages

ተመተው የተገደሉበትን እና የተዘረፉበትን የኃይል ተግባር የፈፀሙትን አጥቂዎች ረድተዋል ሲሉ ችሎቱን የመሩት ዳኛ ብሩኖ ኮት ትናንት ጥፋተኛ ናቸው ሲሉ ብይን አስተላለፉ። ፍርድ ቤቱ ካታንጋን በተሰነዘረባቸው የክብረ ንጽሕና መድፈር፣ ወሲባዊ ጥቃት እና ሕፃናትን ለውትድርና መመልመል ክስ ግን ነፃ ብሎዋቸዋል።

እአአ በ2002 ዓም ስራውን የጀመረው የፍርድ ቤቱ ታሪክ ውስጥ ትናንት ለሁለተኛ ጊዜ ያስተላለፈው ብይን እንዳስታወቀው፣ ካታንጋ አጥቂዎቹ የጦር መሳሪያ እንዲያገኙ ባይረዱ ኖሮ ግድያው ባልተፈፀመ ነበር።

ጭፍጨፋው እና የኃይሉ ተግባር ከተፈፀመ ብዙ ዓመታት ቢያልፉም በሰለባዎቹ ላይ ግን ከህሊናቸው የማይጠፋ መጥፎ ትዝታ ትቶ ማለፉን ግድያው እና ዝርፊያው ከተካሄደበት የምሥራቃዊ ኮንጎ የቡንያ ከተማ እአአ ግንቦት 12፣ 2003 ዓም ባልተቤቱን እና አራት ልጆቹን ይዞ የሸሸው ሻርል ኪታምባላ ያስታውሳል። በዚያን ጊዜ በምሥራቃዊ ኮንጎ የኢቱሪ ግዛት ውስጥ ጦርነት ይካሄድ ነበር።

« ጥይቶች በአናታችን ላይ ነበር እያፏጩ የሚያልፉት። ኃይለኛ ዝናብ ይጥል እና ተርበንም ነበር። »

የተለያዩ ጎሣዎች የሚሊሺያ ቡድኖች በሲቭሉ ሕዝብ አንፃር አስከፊውን ጥቃት ነበር የሰነዘሩት። በዚያን ወቅት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የጎሣ ጭፍጨፋ የተካሄደ ነው በሚል ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው። ሻርል ኪታምባላ እንደሚለው፣ እሱ እና ቤተሰቡ ለጥቂት ነበር ከዘግናኙ ግድያ ያመለጡት።

« ጦርነት አራማጆቹ አንድ ሰው በጩቤ ሲገድሉ ተመልክተናል። ለኛ ይህን ማየት በጣም ከባድ ነበር። »

ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤትዘግናኙ ጭፍጨፋ ከተፈፀመ ከአስራ አንድ ዓመት በኋላ እአአ የካቲት 2003 ዓም ራሱን « የኢቱሪ አርበኞች መከላከያ ኃይላት» ብሎ የጠራው ያማፅያን ቡድን መሪ የነበሩትን እና በምሥራቃዊ ኮንጎ ከምትገኘው የቡንያ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኘው የቦጎሮ መንደር ጭፍጨፋው እንዲፈፀም ረድተዋል ያላቸውን ጀርሜን ካታንጋ ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ብይን ቢያስተላልፍም፣ ሲምባ በሚል የቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ካታንጋ ጥፋተኛ አለመሆናቸውን ነው በድጋሚ ያስታወቁት።

Niederlande Urteil Germain Katanga Internationaler Strafgerichtshof Den Haag Verteidiger
ምስል Reuters

የዚሁ የኢቱሪ አርበኞች መከላከያ ኃይላት ሚሊሺያዎች ከጥቂት ወራት በኋላ በቡንያ ከተማ ከሰነዘሩት ጥቃት ነፍሱን ለማዳን ሲል የሸሸው። ፍርድ ቤቱ በካታንጋ ላይ የሚያስተላልፈውን ቅጣት በሌላ ችሎት እንደሚወስን አስታውቋል። ካታንጋ በቅጣቱ ብይን አንፃር ይግባኝ ማመልከቻ እንደሚያስገቡ ከወዲሁ ይጠበቃል።

ከካታንጋ ጋ ክስ ተመሥርቶባቸው የነበሩትን ጓዳቸው ማትየ ንጉድዦሎን ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ባለፈው 2012 ዓም በነፃ ለቋቸዋል።

የማትየ ንጉድዦሎን እና የካታንጋን ችሎት የተከታተሉት የመብት ተሟጋቹ «ሂውመን ራይትስ ዎች » ባልደረባ ዤራልዲን ማቶሊ ሴልትነር ችሎቱን የመሩት ዳኞች አንዳንድ ትኩረት ሊሰጡዋቸው የሚገቡ ጉዳዮች ችላ ማለታቸውን እንደተገነዘቡት ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።

« ጉዳዩን የመረመሩት ዳኞች እንደሚፈለገው ጭፍጨፋው ወደተፈፀመበት ቦታ አዘውትረው አለመሄዳቸውን አስታውቀዋል። እርግጥ፣ የፀጥታው ጉዳይ ሚና ተጫውቷል። ግን፣ ለምሳሌ፣ ይላሉ ዳኞቹ፣ ምስክሮች የሰጡዋቸው የምስክርነት ቃል እውነት አልነበረም። የተሰጠውን የምስክርነት ቃል ሰው ራሱ በቦጎሮ መንደር ሆኖ ቢያጣራ እውነት አለመሆኑን ይታወቃል። »

ከዚህ ሌላም ሚሊሺያዎቹን በቅርብ ከሚያውቋቸው ጋ አልተነጋገሩም። እርግጥ፣ የተሰበሰበው ማስረጃ ካታንጋን ጥፋተኛ ማስባል ቢያስችልም፣ ፍርድ ቤቱ በቦጎሮ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ብቻ በመመልከታቸው ቅር መሰኘታቸውን ዤራልዲን ማቶሊ ሴልትነር ገልጸዋል።

« የፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ሌሎች ሁለት፣ ወይም ሦስት በኮንጎ የተፈፀሙ የጭፍጨፋ ተግባራትን አለመመልከቱ አዝነናል። ይህን አድርገው ቢሆን ኖሮ በ2003 ዓም ኢቱሪ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን በግልጽ ሊያሳይ ይችል ነበር። ሁለቱ ተከሳሾች ጀርሜን ካታንጋ እና ማትየ ንጉድዦሎ በጦር ቡድናቸው ውስጥ የተጫወቱትን ሚና እና ሲቭሎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ሆን ተብሎ መካሄዱን በቀላሉ በማስረጃ ማረጋገጥም ያስችላቸው ነበር። »

በበገጠሩ የምሥራቃዊ ኮንጎ አካባቢ ውዝግቡ በሌንዱ ጎሣ ገበሬዎች እና በሄማ ጎሣ አርብቶ አደሮች መካከል በመሬት ጉዳይ ንትርክ በተፈ,ጠረበት ጊዜ ነበር የተጀመረው። ይኸው ቆየት ብሎ ወደ ጎሣ ግጭት የተቀየረውን ውዝግብ የተለያዪት ቡድኖች ለራሳቸው እንደ ፖለቲካ መሳሪያ ተጠቅመውበታል። ካታንጋ የመሩት የኢቱሪ አርበኞች መከላከያ ኃይላት የንዑሱ የንጊቲ ጎሣ የጦር ቡድን ሲሆን፣ የሌንዱ ሚሊሺያ ጥምረት አባል ነበር። የሌንዱ ብሔረ ሰብ ተቃውሞ ግን የተጀመረው በጣም ዘግይቶ ስለነበር ፣ ካታንጋ በቦጎሮ መንደር ጭፍጨፋው በተፈፀመበት ጊዜ አንዱ የጦሩ ቡድን መሪ እንደነበሩ እና ለግድያው ተጠያቂ መሆናቸውን ማረጋገጡ አዳጋች እንደነበር ነው የተገለጸው።

Massaker im Ostkongo

ተጠያቂ የሆኑ ከፍርድ እንደማያመልጡ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሀምሌ 2012 ዓም የሄማ ጎሣ ዓማፅያን ቡድን መሪ የነበሩትን እና ሕፃናትን ለውትድርና ተግባር መልምለዋል በሚል የተከሰሱትን ቶማስ ሉባንጋን በ14 ዓመት እስራት በቀጣበት ብይኑ የማያወላውል መልዕክት ነበር ያስተላለፈው። ፍርድ ቤቱ የሉባንጋ ተቀናቃኝ የሆነ የጦር ባላባትን፣ ማለትም ፣ ካታንጋን ጥፋተኛ ብሎ ብይን ማስተላለፉ የሚሞገስ ቢሆንም፣ ባካባቢ ሚሊሺያ መሪዎች ላይ ብቻ መወሰኑ ነቀፌታ አስከትሎበታል። ምክንያቱም ውዝግቡ ሰፊ ፖለቲካዊ ትርጓሜ አግኝቶ የጎረቤት ሀገራትን ጣልቃ ገብነትን እንዳስከተለ ነው የሚነገረው፣ በዚያን ጊዜ ዩጋንዳ የሌንዱ ጎሣ ሚሊሺያዎችን ፣ ርዋንዳ ደግሞ የሄማ ሚሊሺዎችን ደግፈዋል።

ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በአሁኑ ጊዜ በስምንት ሀገራት የሚካሄዱ ውዝግቦችን በመመርመር ላይ ስለሚገኝ፣ የፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ ወደፊት የክሶችን ምርመራ ባካባቢ ላይ ብቻ ባይወስኑት፣ በተለይ ደግሞ ፣ ሚሊሺያዎችን እና የመንግስት ጦር ኃይላትን ማን በገንዘብ እንደሚረዳ ቢመረምሩ እንደሚመረጥ ማቶሊ ሴልትነር አስገንዝበዋል። የንጉድዦሎ ችሎት ከኮንጎ እና ከዩጋንዳ በኩል ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት እና የጦር መኮንኖች ጣልቃ ገብነት እንደነበር አሳይቶዋል።

Mathieu Ngudjolo Chui
ማትየ ንጉድዦሎምስል AFP/Getty Images

የካታንጋ ቅጣት ያም ሆንነ ይህ ከጭፍጨፋው የተረፉ ሻርል ኪታምባላን የመሰሉ የኮንጎ ዜጎች ሁሉ የሌንዱ እና የሄማ ጎሣዎች ወደፊት በሰላም እንዲኖሩ እንደሚፈልጉ ነው ከብይኑ በኋላ ያመለከቱት።

ፊሊፕ ዛንድነር/አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ