1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የቡሩንዲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 14 2007

በቡሩንዲ ሁከት የታየበት ትናንት የተካሄደው አወዛጋቢ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት በነገው ዕለት ይፋ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ። ሕገ ወጥ በሚል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውግዘት በተፈራረቀበት ምርጫ የሀገሪቱን ህገ መንግሥት በመጣስ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን የተወዳደሩት ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ እንደሚያሸንፉ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/1G2Hg
Burundi vor Parlamentswahlen
ምስል Getty Images/AFP/C. De Souza

[No title]

ምንም እንኳን የተቃዋሚ ቡድኖች ከምርጫው ቢርቁም፣ ባለፈው ወር ከተደረገው ምክር ቤታዊ ምርጫ ጋር ሲነፃፀር፣ የመምረጥ መብት ካለው 3,8 ሚልዮን የቡሩንዲ ዜጋ መካከል በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ላይ 74% ድምፃቸውን መስጠታቸውን የአስመራጩ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ፒየር ክላቨር ንዳይካሪዬ አስታውቀዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የቡሩንዲ ተቃዋሚ ቡድኖች ሀገሪቱን ከቀውስ ለመጠበቅ ሲባል የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲመሠረት ያቀረቡትን ሀሳብ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ሊቀበሉ እንደሚችሉ የፕሬዚደንቱ አማካሪ ዊሊ ንያሚትዌ ገልጸዋል፣ ይሁንና፣ የተቃውሞ ቡድኖች አምስት ዓመት የሚዘልቀውን የሀገሪቱን ፕሬዚደንት የሥልጣን ዘመን እንዲያጥር ያቀረቡትን ሀሳብ ንኩሩንዚዛ ውድቅ ማድረጋቸውን ንያሚትዌ አክለው አስታውቀዋል።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

------

የቡሩንዲ ምርጫ

አጨቃጫቂው የቡሩንዲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማክሰኞ ፣ እአአ ሀምሌ 21፣ 2015 ዓም ተኪያሂዷል። ከዋዜማው አንስቶ ፍንዳታዎች እና የተኩስ ሩምታዎች ሲደመጡ ነበር። ከትናንት አንስቶ በተፈጠረው ግጭት ሦስት ሰዎች ተገድለዋል። ሁለቱ ፖሊሶች ናቸው ተብሏል። ለሦስተኛ ዙር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከመሳተፍ የሚያግደኝ አንዳችም ኃይል የለም ያሉት ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ከተለያየ አቅጣጫ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም በእርግጥም በምርጫው ገፍተውበታል።

ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ
ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛምስል picture-alliance/dpa/C. Karaba

እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ2005 ዓም በቡሩንዲ እጅግ አስከፊው የእርስ በርሱ ግጭት ካከተመ ወዲህ ትናንት በዋዜማው መዲናይቱ ቡጁምቡራ በተኩስ እና ፍንዳታ ስትናወጥ ነው የነጋላት። የጥይት ሩምታውም የቦንብ ፍንዳታውም ሰበብ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ ዘመነ-ሥልጣን እወዳደራለሁ፣ ያን ከማድረግ ማንም አያግደኝም ብለው መነሳታቸው ያስከተለው ተቃውሞ ነው።

ቡሩንዲ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋዜማ
ቡሩንዲ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዋዜማምስል Getty Images/AFP/C. De Souza

የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ ተከትሎ በሀገር ውስጥ አንዳንድ ተቃዋሚዎች በምርጫው ላለመሳተፍ ሲቆርጡ፤ ሌሎች በምርጫ ዘመቻው እንዳይካፈሉ መገደዳቸውን ገልጠዋል። የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ የተቃወመው ሕዝብ ደግሞ ላለፉት ሦስት ወራት ተቃውሞን በተለያየ መንገድ ሲገልጥ ሰንብቷል። ፕሬዚዳንቱ ግን ፓርቲዬ በምርጫ እንድሳተፍ ባያስገድደኝ እዚህ ባልቆምኩ ነበር ሲሉ ዓይናቸውን በጨው አጥበው ብቅ ብለዋል።

«እኔ ዛሬ እዚህ ከፊታችሁ የቆምኩት ለመወዳደር ቆርጬ ስለተነሳሁ አይደለም። ፓርቲዬ ነው ወደዚህ እንድመጣ ያደረገኝ። እያንዳንዱ ለእኔ የሚሰጠኝ ድምጽ ለፓርቲያችን የተሰጠ ነው። የተቀረው በአጠቃላይ ውሸት ነው። እኔን የሚመርጠኝ ፓርቲያንን የሚመርጥ ነው።»

ፕሬዚዳንቱ ይኽን ይበሉ እንጂ ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ነው ለሦስተኛ ጊዜ የሚወዳደሩት ሲሉ ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እያከናወኑ ነው። በትናንትናው ምሽት በተቀሰቀሰ ግጭት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል። ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ፖሊሶች ናቸው ተብሏል። አንደኛው ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ ባለሥልጣን ሲሆን፤ አስክሬኑ ዛሬ ማለዳ ጎዳና ላይ ተጥሎ መገኘቱ ተገልጧል። ሁለቱ ፖሊሶች ትናንት ምሽት በጥይት ተመተው መገደላቸውን የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ዊሊ ኒያሚትዌ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በቡሩንዲ
ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በቡሩንዲምስል DW/S. Schlindwein

እንዲህ ከዋዜማው አንስቶ ጥላ ያጠላበት የቡሩንዲ አወዛጋቢ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ዛሬ የተጀመረው ከሌሊቱ 12 ሰአት አንስቶ ነበር። ፍንዳታዎች እና የጥይት ሩምታዎች ቢደመጡም፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱት ከጠዋቱ አንድ ሰአት አንስቶ መሆኑ ተጠቅሷል። በሀገሪቱ በስተምዕራብ ከምትገኘው የቡባንዛ አውራጃ ሙሴንዪ ከተማ የመጡ መራጭ በፍንዳታው እና በጥይት ድምጹ ስጋት ቢገባቸውም ለምርጫ ግን ወጥተዋል።

«የመራጭነት መብቴን ለማስጠበቅ እና ፕሬዚዳንቱን ለመምረጥ ነው የመጣሁት። እኔ እንደ አንድ የቡሩንዲ ዜጋ፣ እንደ አንድ አርበኛ ነው የመጣሁት። ምንም እንኳን ስጋት ቢገባኝም ማለት ነው።»

የዛሬው ምርጫ ከመድረሱ ቀደም ብሎ ብሩንዲ ለሣምንታት የዘለቀ የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍን ሲያምሳት ነው የከረመው። የከሸፈው መፈንቅለ-መንግሥትን ተከትሎም በፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ታማኝ ወታደሮች እና አፈንጋጭ ወታደሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ መኪያሄዱም ተጨማሪ ክስተት ነበር።

የ51 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ በዛሬው ምርጫ ያለ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚያሸንፉ ሳይታለም የተፈታ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የዛሬው የቡሩንዲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከፍተኛ ብጥብጥ ሊያስነሳ ይችላል ሲሉ በርካቶች ፍርሃታቸውን ገልጠዋል። እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር በ1961 ከቤልጂየም ነጻነቷን የተቀዳጀችው ቡሩንዲ አራት መፈንቅለ-መንግሥት ተከናውኖባታል። በሀገሪቱ ተቀስቅሶ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነትም 250,000 ያኽል ነዋሪዎች ተገድለዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ