1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

« አስተማማኝ የተባሉት የማግሬብ ሃገራት»

Lidet Abebeማክሰኞ፣ የካቲት 22 2008

ሰሞኑን ሦስት የሰሜን አፍሪቃ ሀገራትን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የጀርመን የሀገር አስተዳደር ሚንስትር ቶማስ ዴ ሜዚየር ግልጽ ዓላማ ይዘው ነው ወደነዚሁ የማግሬብ ሀገራት የተጓዙት። ጀርመን የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘላቸውን የሞሮኮ፣ አልጀሪያ እና የቱኒዝያ ዜጎችን በፍጥነት ወደ ሃገራቸዉ መመለስ ትሻለች።

https://p.dw.com/p/1I51V
Symbolbild Libyen Algerien Ägypten Maghreb Nordafrika
ምስል Fotolia/Elenathewise

[No title]

በዚህም የተነሳ የነዚህ ሀገራት መንግሥታት ከጀርመን ጋር ተባብረው እንዲሰሩ ሚንስትር ጠይቀዋል። ዴ ሜዚየር እስካሁን ከጎበኟቸው ሞሮኮ እና ቱኒዚያም መንግሥታትጋር ከስምምነት ደርሰዋል። ጀርመን ሶርያን እና አፍጋኒስታንን በመሳሰሉት ሀገራት አንፃር የማግሬብ ሀገራት የሚባሉትን ሞሮኮ፣ አልጀሪያ እና ቱኒዝያን «አስተማማኝ » በምትላቸው ሀገራት ዝርዝር ውስጥ አስቀምጣቸዋለች። ይህ አመዳደቧ የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘላቸውን ስደተኞች በቀላሉ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥሩ ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይታመናል። ይሁንና፣ አንድን ሀገር የተረጋጋ ወይም አስተማማኝ ብሎ ለመሰየም መስፈርቱ ምንድን ነው? በጀርመን ህግ መሰረት፣ አንድ ሀገር አስተማማኝ የምትባለው፤ የፖለቲካ ሁኔታዋ የተረጋጋ፣ ሰዎች በፖለቲካም ይሁን በሌላ ምክንያት ሀገራቸው ውስጥ ክትትል የማይደረግባቸው እና በደል የማይፈጸምባቸው ከሆነ ነው። ያም ቢሆን ግን፣ የዶይቸ ቬለው የንስ ቦርሸርስ ዘገባ ከሞሮኮ እንደጠቆመው፤ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ጉዳይም ይሁን ከነዚሁ ሀገራት መንግሥታት ጋር የሚደረገው የትብብር ስራ ቀላል አይሆንም።
ቱኒዚያዊው ጂሄድ 22 ዓመቱ ነው። ግብረሶዶማዊ ነው። ትክክለኛ ስሙን መናገር አይፈልግም። ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ በመሆኑ የተነሳ ከሌሎች አምስት ወንዶች ጋር ተይዞ ወህኒ ቤት ገብቷል።« እኔ የነበርኩበት ማረፊያ ቤት ውስጥ 190 እስረኞች ነበሩ። እስረኞቹ ግብረሶዶማዊ በመሆኔ ሁሌ ያንገላቱኝ ነበር። ጠባቂዎቹ ይደበድቡን ነበር። ለአንድ ወር ተኩል ያህል በየቀኑ ይደበድቡን ነበር። ወይ በዱላ እግራችንን ይገርፉናል ወይ ደግሞ ጭንቅላታችንን በቡጢ ይመቱናል፣ ይሰድቡናል። እኛ እዚህ ምንም መብት የለንም።»
ጂሄድ በዚህ ወህኒ ቤት ለሦስት ወራት ታስሮ ከቆየ በኋላ የከፍተኛ ትምህርቱን ይከታተልባት ከነበረባት እና ከታሰረባት የካይሮኡን ከተማ ለአምስት ዓመት ታግዶዋል።
ቱኒዚያ ውስጥ የሚሰራበት የቁም ስቅል የማሳየቱ ተግባር አሁንም በጣም አነጋጋሪ ርዕስ ነው። የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በርካታ የቁም ስቅል የማሳየት ተግባሮችን የሚመለከቱ ክሶች መዝግበዋል።« በአንድ የቱኒስ ፍርድ ቤት ብቻ 110 የቁም ስቅል ማሳያ ክሶች ይገኛሉ። የ 44ቱ ጉዳይ ታይተዋል፣ ይሁንና፣ እስካሁን አንዳቸውም ፍርድ አልተሰጠባቸውም። እነዚህ አዲስ ክሶች ሳይሆኑ ዓመታት ያስቆጠሩ ናቸው።»
ይላሉ፣ የቱኒዚያ የሰብዓዊ መብት ሊጋ የክብር ሊቀመንበር ሞክታር ትሪፊ። ይሁንና፣ በቱኒዚያ ለውጦችም ታይተዋል። ማንኛውም በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው ጠበቃ የመያዝ መብት አለው። ሌሎች ህጎችም ላይ ቢሆን ዕርማት ተደርጓል። ጥያቄው ግን የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ምን ያህል ህጉን ተግባራዊ ያደርጋሉ የሚለው ነው። ይህ የሞሮኮም ጥያቄ ነው። የሞሮኮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ካዲጃ ሪያዲ ሞሮኮን ፍጹም አስተማማኝ ሀገር ናት ብለው አያምኑም።« ገለልተኛ ፍትህ የለም። በሞሮኮ ህጎች እንደማይከበሩ በርካታ የሞሮኮ እና ዓለም አቀፍ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፉት ዓመታት ሞሮኮ ውስጥ የፍዳ እና መከራ የማሳየቱ ተግባር መቀጠሉን ዘግቦ ነበር።»
አልጄሪያ ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ነው የሚነገረው። ገሀዱ ይህን ከሆነ ታድያ፣ እነዚህ ሦስት ሀገራት የተረጋጉ ሊባሉ መቻላቸው አጠያያቂ ነው፣ በርግጥ፣ ጉዳዩ አሁንም እያወዛገበ ይገኛል። ወደ ጀርመን የሚገቡት የነዚህ ሦስት የማግሬብ ሀገራት ስደተኞች ቁጥር ከሌሎች ሀገራት ከሚመጡት ስደተኞች ጋር ሲነፃጸር በርግጥ ብዙ አይባልም። በአጠቃላይ ከነዚህ ሀገራት ባለፈው የጎርጎሪዎስ ዓመት 2015 ጀርመን የገቡት ተገን ጠያቂዎች ቁጥር 26 000 ሲሆን ፣ ይኸው ቁጥር 2016 ዓም ከገባ በኋላ መቀነሱ ተዘግቧል።

Flüchtlinge aus Nordafrika in Chemnitz
የሰሜን አፍሪቃ ስደተኞች በጀርመንምስል picture-alliance/dpa/H. Schmidt
Marokko Innenminister Thomas De Maizière
የጀርመን የሀገር አስተዳደር ሚንስትር ቶማስ ዴ ሜዚየርምስል Getty Images/AFP/F. Senna

የንስ ቦርሸርስ / ልደት አበበ
አርያም ተክሌ