1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ናይጀርያ እና አክራሪ ሙስሊሞች

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 25 2001

በናይጀርያ እስላማዊ መንግስት ማቋቋም የሚፈልጉት አክራሪ ሙስሊሞች በሀገሪቱ ሰሜናዊ አካባቢ ሰሞኑን ከጸጥታ ሀይላት ጋር ተጋጩ።

https://p.dw.com/p/J0yk
በማይዱጉሪ የሞቱት ናይጀርያውያን
በማይዱጉሪ የሞቱት ናይጀርያውያንምስል AP

በሰሜናዊ ናይጀርያ ካለፈው እሁድ በኋላ በቀጠሉት አራት ቀናት ውስጥ በጸጥታ ኃይላትና አንድ ራሱን የአፍሪቃ ታሊባን ብሎ በሚጠራ የአክራሪ ሙስሊሞች ቡድን መካከል በተካሄደ ግጭት ወደ ስድስት መቶ የሚጠጋ ሰው ሲሞት ወደ ሶስት ሺህ አምስት መቶ የሚጠጉም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በቀይ መስቀል መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ። ሁከቱ በመጀመሪያ በተነሳባት በባውቺ ከተማ የጸጥታ ኃይላት ባለፈው እሁድ የአክራሪውን የሙስሊሞች ቡድን ደጋፊዎችን ካሰሩ በኋላ፡ ቡድኑ በአጸፋ በአያሌ ከተሞች የፖሊስ ጽህፈት ቤቶችን አጥቅቶዋል። ግጭቱ እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በቀጠለባት የአክራሪው ቡድን ማዕከል ነው በሚባልባት በቦርኖ ክፍለ ሀገር ርዕሰ ከተማ ማይዱጉሪ ፖሊስ የቡድኑን መሪ መሀመድ ዩሱፍን መኖሪያ ቤት በማጥቃት ዩሱፍን ማሰር ችሎ ነበር። ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዩሱፍ ከእስራት ሊያመልጡ ሲሞክሩ ባለፈው ሀሙስ ፖሊስ ተኩሶ እንደገደላቸው የብሪታንያ ዘና አገልግኮት ድርጅት አስታውቋል።
-----------
ልክ በሰሜን ናይጀርያ እንደሆነው ሁሉ በመላ ናይጀርያም እስላማዊውን መስተዳድር ማቋቋም የሚፈልገው ይኸው ቡድን የአምላክን ፈቃድ ይጥሳል ብሎ የሚያስበውን ሁሉ ያወግዛል። የሙስሊሞቹን ቅዱስ መጽሀፍ - ቆርዓንን በመሰለው መንገድ ብቻ የሚተረጉመው ይኸው ቡድን የሰው ልጅ በተለይ ዘመናዩን ትምህርት እንዳይከታተል እና የፈጣሪን ትዕዛዝ ብቻ እንዲያከብር ያበረታታል። የምዕራባውያኑ አስተሳሰብ በናይጀርያ መንግስትም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳረፈ ነው የሚሰማው። በዚሁ አስተሳሰቡ የተነሳም በሰሜናዊ ናይጀርያ የሚኖረው ህዝብ ቡድኑን « ቦኮ ሀራም» ወይም ዘመናዩ ትምህርት ተከልክሎዋል የሚል መጠሪያ ሰጥተውታል።


አክራሪዎቹ ሙስሊሞች ባካባቢው ለሚታየው ድህነት ዘመናዩን ትምህርት የማጠናቀቅ ዕድል ያገኙት ሀብታሞቹን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ባካባቢው ባለው ዛሪያ ዩኒቨርሲት የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ቤሎ ግዋርዞ ያስረዳሉ።« የቡድኑ ተከታዮች ለሚገጥማቸው ማህበራዊ ችግር፡ ለድህነት፡ ሞራላዊ እሴቶች ለጠፉበት ድርጊት ሁሉ፡ በምራባውያት ሀገሮች ትምህርት በተከታተሉት ናይጀሪያውያን ላይ የሚያዩትን ተጠያቂ ያደርጋሉ። »
በቦርኖ ክፍለ ሀገር ያሉት ሌላው የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ሀሩና ያሪማ እንዳስታወቁት፡ የሚገርመው ያለማረው ብቻ አይደለም የአፍሪቃ ታሊባን የሚባለውን አክራሪውን ቡድን የሚደግፉት። « አንዳንዶቹ አክራሪዎች ራሳቸው ትምህርት የተከታተሉና የስራ ዕድል ያላገኙ ናቸው። የሚኖሩት በከፋው ድህነት ውስጥ ነው። እና ለነርሱ የምዕራቡ ዓይነት ትምህርት ጥቅም አልባ ነው። »


በካኖ ፌዴራዊ ክፍለ ሀገር በታያው ሁከት ወቅት የታሰረ በኃይሉ ተግባር ውስጥ እንዳልተሳተፈ በአጽንዖት ያስታወቀው አንድ የአክራሪው ቡድን ደጋፊ ይህንኑ የሀሩና ያሪማ አባባል አረጋግጦዋል።
« ችግራችን የፍትሁ አውታር የሚሰራበት ህግ ከእግዚአብሄር የመጣ አለመሆኑ ነው። የሚከተለው በህግ መንግስቱ የሰፈረውን ህግ ነው። ይህ የሸሪዓን ህግ አይከተልም። በህገ መንግስቱ የሰፈረውን ህግ ያረቀቁት ሰዎች ናቸው። እኛ በምዕራቡ የትምህርት ስርዓት ሳይሆን በቆርዓን እና ከነቢዩ መሀመድ በቀጥታ በወረደ ህግ ነው። እኔ ራሴ ለምሳሌ ስህተቴን እሳካወቅሁ ድረስ፡ የምዕራቡን የትምህርት ስርዓት ተከታትዬ ነበር። »

አንድ መቶ ሀምሳ ሚልዮን ህዝብ በሚኖርባት ናይጀርያ ውስጥ አክራሪ ሙስሊሞች ቡድኖች በፖሊስ ላይ ጠንካራ የኃይል ርምጃ ሲወስዱ ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜአቸው አይደለም። እአአ በ 1980 ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ማይታትሲኔ የሚባል አንድ ቡድን ተመሳሳይ የኃይል ተግባር ማሃሄዱ ይነገራል። ያኔ በመቶ የሚቆጠሩ የቡድኑ ደጋፊዎች በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ በሚኖርባት በካኖ ከተማ መሽገው ከፖሊስ ጋር ያካሄዱት እና የብዙ ሰው ህይወት ያጠፋው ብርቱ የተኩስ ልውውጥ ሊያበቃ የቻለው የሀገሪቱ ጦር ኃይል ጣልቃ ከገባ በኋላ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ንዑሳን ግን ተመሳሳይ ሁለቶች በሀገሪቱ ታይተዋል።


ብዙኃኑ የናይጀርያ ሙስሊሞች እና ምሁራን የአክራሪዎ ቡድን የሚከተለውን ርዕዮተ ዓለም የእስልምና መመሪያዎችን የሚጻረር ነው በሚል አይቀበሉትም። የመሰለ ቡድን በአንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ የብረቱን ትግል እንዴት ማካሄድ መቻሉን ብዙዎች አጠያይቀዋል። የሀገሪቱ መንግስት በአክራሪዎቹ ቡድኖች አንጻር ለምን ቀደም ብሎ ርምጃ አለመውሰዱም የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪውን ሀሩና ያሪማ አስገርሞአቸዋል።
« የጸጥታ ኃይላት ስራቸውን በሚገባ አላከናወኑም። ቡድኑ አንዳችም ክትትል ሳይደረግበት እንዲጠነከር የተዉት ሲሆን፡ አሁን ይኸው ስህተታቸው ያስከተለውን መዘዝ መቀበል ግድ ሆኖባቸዋል። ማይዱጉሪ እና በጠቅላላ ሰሜን ናይጀርያ የሆነ ነገር በመካሄድ ላይ መሆኑን ብዙዎች፡ ጋዜጠኞች ጭምር ያውቁ ነበር። »


የናይጀርያ መንግስት በሀገሩ ለሚታየው ማህበራዊ ችግር መፍትሄ ካላስገኘ በስተቀር የሰሞኑ ዓይነት ሁከት በየጊዜው መከሰቱ እንደማይቀር የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ሀሩና ያሪማ አስጠንቅቀዋል። እንደ ያሪማ ግምት፡ ችግር የበዛበት ህዝብ በሀገሩ መንግስት አውታር ላይ ቅር የሚሰኝበት ድርጊት በናይጀርያ ለአክራሪዎቹ ቡድኖች መጠናከር አመቺውን ሁኔታ ይፈጥራል።

ቶማስ መሽ/አርያም ተክሌ/ማንተጋፍቶት ስለሺ