1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቴክኒዎሎጂን ለጤና

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2002

የድሃ አገራት ከፍተኛ የጤና ችግር የሆነችዉ ወባን ለማዳን ፍቱን መድሃኒት እንደሚያስፈልግ አያነጋግርም። በአፍሪቃ በአሳሳቢ ሁኔታ የበርካቶችን ህይወት የሚቀጥፈዉን ይህን በሽታ ለመቆጣጠር SMS FOR LIFE በሚል በታንዛኒያ ፕሮጀክት ተጀምሯል። የዘመኑን የተንቀሳቃሽ ስልክ ቴክኔዎሎጂ ለህይወት ማዳን ተግባር ማዋል መሆኑ ነዉ፤

https://p.dw.com/p/NELk
ምስል picture alliance/dpa

Per SMS zum Erntehelfer
ምስል Barbara Gruber

በወባ በሽታ የተያዘን ሰዉ ፈፅሞ ሊፈዉስ የሚችል ዉጤታማና ፍቱን መድሃኒት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ታክሞ መዳን ሲቻል በወባ መዘዝ በአፍሪቃ የሚያልቀዉን የሰዉ ዘር ህይወት ለመታደግ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና የአፍሪቃ አገራት መንግስታት የፍቱን መድሃኒቶች አቅርቦት እንዲጠናከር እየጣሩ ነዉ። መድሃኒቶቹ ከየስፍራዉ ቢሰባሰቡም ለወባ በሽታ ተጠቂዎችና ለፈላጊዎቹ የማዳረሱ ተግባር አጥጋቢ ባለመሆኑ የመድሃኒት እጥረት በተለይ በገጠሩ አካባቢ ዋነኛ ችግር ነዉ። ታንዛኒያ ዉስጥ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክን በመጠቀም የፅሁፍ መልዕክቶችን በማስተላለፍ የተጀመረዉ ፕሮጀክት ለችግሩ መፍትሄ ይዞ እንደቀረበ የዶቼ ቬለዋ አሱምፕታ ላቱስ በዘገባዋ ጠቅሳለች። በታንዛኒያ የገጠር መንደሮች ዉስጥ የሚገኙ በርካታ ትናንሽ የጤና ማዕከሎች በመድሃኒት እጥረት ሲቸገሩ ይታያሉ። ህመምተኞች ወደእነዚህ የጤና ጣቢያዎች ሲሄዱ የሚያገኙት ምላሽ መድሃኒት አልቋል የሚል ነዉ። ህዝቡም ለህመሙ መፍትሄ ያላቀረቡለትን ለጤና ጣቢያዎቹ አልቋል የሚል ቅፅል ሰጥቷቸዋል። ችግሩ ግን የመድሃኒት አቅርቦት ሳይሆን የአስተዳደር መሆኑን የአገሪቱ የጤና ጥበቃና የማኅበራዊ ደህንነት ሚኒስትር ዶክተር ዴቪድ ማዋኪዩሳ ተረድተዋል።

«በምክር ቤት ዉስጥ ከሚቀርቡልኝ በርካታ ችግሮች መካከል የመድሃኒት ማለቅ ጉዳይ አንዱ ነዉ። መድሃኒቶችን ወደአገራችን የሚያመጣ አንድ አካል አለን። የህክምና ማከማቻ ክፍል እንለዋለን። ይህ ማከማቻ ዘርፍ ተግባሩ መድሃኒቶች ወደአገራችን ማስገባት፤ ማከማቸትና ተገቢዉ መንገድ በወረዳ ደረጃ ማከፋፈል ነዉ። ከየወረዳዉ ደግሞ የወረዳዉ አማካሪዎች ወደየጤና ማዕከሉ ከዚያም ወደመድሃኒቱን ለተጠቃሚዉ የሚያዳርሱ አካላት ይከፋፈላል። እዚያ ነዉ እንግዲህ ችግሮቹ ያሉት።»

Impavido Medikament Leishmaniose Krankheit Zentaris AG

በመላዉ አገሪቱ የሚገኙ የየወረዳዉ አማካሪዎች በየሚገኙበት አካባቢ በየወቅቱ በመጋዘናቸዉ ያለዉን የመድሃኒት መጠን ለመቃኘት ይሞክራሉ። በዚህ ወቅት የሚታዘቡት አንደኛዉ የጤና ማዕከል ከሌላኛዉ ይልቅ ከበቂ በላይ መድሃኒት ለመጠባበቂያ ሳይቀር አከማችቶ ይታያል። ሌሎች ደግሞ ጭራሽ የመድሃኒት ያለህ የሚለዉ የየዕለቱ አቤቱታቸዉ ነዉ። ባብዛኛዉም በጤና ማዕከሎችና በየወረዳ አማካሪዎች መካከል ያለዉ ግንኙነት አዳጋች ነዉ። ለምን ቢባል የስልክ መስመሮች አለያም የኢንተርኔት ግንኙነቱ በበርካታ የገጠር አካባቢዎች እንደአብዛኛዉ የአፍሪቃ አገር የሚታሰብ አይደለምና ነዉ ምላሹ። እዚህ ጋ ነዉ እንግዲህ የተንቀሳቃሽ ስልኩ ሚና ብቅ ያለዉ። SMS FOR LIFE ተብሏል ሞባይል ስልክን ህይወትን ለመታደግ በታንዛኒያ የተጀመረዉ የሙከራ ፕሮጀክት። የዚህ ፕሮጀክት ተጓዳኞች የዓለም የጤና ድርጅት ROLL BACK MALARIA የተሰኘዉ ትብብርና የግል ኩባንያዎች እንዲሁም ቮዳፎን የተሰኘዉ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ሰጪና IBM የተባለዉ የኮምፕዩተር ፋብሪካ ነዉ። የፕሮጀክቱ ዓላማ በትናንሾቹ የገጠር ቀበሌዎች የሚገኝ አንድ የጤና ባለሙያ በአካባቢዉ ስላለዉ የመድሃኒት ክምችት መጠን በየጊዜዉ አጫጭር የፅሁፍ መልዕክት ወደማዕከላዊዉ የመረጃ ማህደር እንዲያስተላልፍ ነዉ። የታንዛኒያ ብሄራዊ የወባ መቆጣጠሪያ መርሃ ግብርና የየወረዳዉ አስተዳደር ታዲያ የኢንተርኔት መስመር ከተገናኘላቸዉ ኮምፕዩተሮች አለያም በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቻቸዉ መረጃዎቹን ያገኛሉ። ጂም ባሪንግቶን የሃሳቡ አፍላቂና የፕሮጀክቱ የፕሮግራም ዳይሬክተር ናቸዉ፤

«ሃሳቡ ከሁለት ዓመታት በፊት ነዉ የኖቫሪትስ ተባባሪ ዳይሬክተር በነበርኩበት ወቅት በአዕምሮዬ የተጠነሰሰዉ። ያኔ የኢንተርኔት ቴክኒዎሎጂን የሚመለከት ታላቅ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ነበረን። በጉባኤዉ ላይ ወባን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሰዉን ቡድን የሚመሩትን ሲልቪዮ ጋብርኤልን ጋብዘናል። በወቅቱ ያቀረቡትን መግለጫ ሲያጠቃልሉ በየጊዜዉ 50፤ 60 ብሎም ሰባ ሚሊዮን መድሃኒቶችን ወደታንዛኒያ ቢልኩም በየዓመቱ 3,000 ሰዎች በወባ እንደሚሞቱ ገለፁልን። እንደየኢንተርኔት ቴክኒዎሎጂ ባለሙያነቴ ይህ ከባድ ችግር ነበር የሆነብኝ። ትርጉም አይሰጥም፤ መድሃኒቱ ካለን ታዲያ ሰዎች እንዴት በበሽታዉ ዛሬም ይሞታሉ?»

ብሪንግቶንና ቡድናቸዉ ለዚህ እንቆቅልሽ ሳይታክቱ መፍትሄ ማፈላለግ ጀመሩ፤ ተንቀሳቃሹን ስልክና ኤሌክትሮኒክ ማፒንግን ቴክኒዎሎጂን በመጠቀም። በዓንድ ዓመት ጊዜ ዉስጥ ፕሮጀክቱን የሚቀርፅ ቡድን ተቋቋመ፤ መረጃ ማከማቻዉና ማስተላለፊያዉ ተዘረጋ በታንዛንያ ሶስት ወረዳዎች ደግሞ ቁልፍ የሚባሉ ሰራተኞች ስልጠና ተሰጣቸዉ። ዛሬ በእነዚህ ወረዳዎች ዉስጥ በሚገኙ 226 የገጠር መንደሮች ከ100 የጤና አገልግሎት ሰጪ ማዕከላት ትርጉም ያለዉ ዉጤት እያሳያኑ ነዉ። በመጀመሪያ አንድ አራተኛ የሚሆኑት ማዕከላት ለወባ የሚሆን ምን ዓይነት መድሃኒት በየመደርደሪያቸዉ አልነበራቸዉም። ዉሎ አድሮ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲሆን ግን 95 በመቶዎቹ ቢያንስ ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚዉል መድሃኒት እንዳላቸዉ አሳወቁ። ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደግሞ ከ800,000 በላይ የገጠሪቱ ኗሪዎች የወባ መድሃኒት ህክምና ማግኘታቸዉ ተረጋገጠ። በተመ የዓለም የጤና ድርጅት ROLL BACK MALARIA የተሰኘዉ ፕሮጀክት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አዋ ማሪየ ኮል ስክ ይህ ፕሮጀክት በሌሎች የአፍሪቃ አገራትም ሊሰራ ይችላል ነዉ እምነታቸዉ፤

«የተጣሩ መረጃዎችን ለማግኘት እንደዉም ይህ ስልት ሊጠቅም ይችላል። እንደዉም ሃሳቡን በቀጣዩ የቦርድ ስብሰባ ላይ እናቀርበዋለን። ምክንያቱም ዛምቢያ፤ ጋና እና ሌሎች አገራትም ይህን ቴክኒዎሎጂ ለመጠቀም እየተጣጣሩ ነዉ።»

እናም ሃሳቡ በየአገራቱ ተቀባይነት አግኝቶ ስራ ላይ ከዋለ በበርካታ የአፍሪቃ አገራት የወባ በሽታን የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አያነጋግርም። ይህ ስልት የሚጠይቀዉ አንድ ነገር ነዉ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ