1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ታዳጊው ዓለም፤ ወደ ከተሞች የሚደረገው ፈለሣና ድህነት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17 1999

በታዳጊው ዓለም በረሃብ፣ በድህነት፣ በጦርነት የተነሣ በያመቱ ከገጠር ወደ ከተማ የሚጎርፈው ሕዝብ ቁጥር ስፍር የለውም። በከተሞች ደግሞ አብዛኛው ፈላሽ የባሰ እንደሆን እንጂ የተሻለ ዕጣ አይገጥመውም። ትርፉ መንገድ አዳሪነት፤ ከምንኛውም የትምሕርትና የጤና አገልግሎት መነጠል፤ በአጠቃላይ ተሥፋ ቢስነት ነው። የበለጸጉት መንግሥታት የዕርዳታ ቃልም ቃል ብቻ እንደሆነ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/E0cy

ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው ፈለሣ ለመጀመር ይህ ችግር በታዳጊ አገሮች የልማት ዕርምጃ ላይ ያለው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የያዝነው 2007 በሰውልጅ ታሪክ ውስጥ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች ብዛት በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እኩል የሚሆንበት ዓመት ነው። የከተሞች ማደግ ደግሞ በየመንገዱና በየደሳሳው ጎጆ የሚኖረው ከተሜ ቁጥር መብዛት ይሆናል። የዓለም ገጽታ በዚህ መልክ እየተለወጠ መምጣቱ የተገለጸው ባለፈው ሣምንት ኬንያ ርዕሰ-ከተማ ናይሮቢ ላይ ተካሂዶ በነበረ 21ኛ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ሰፈራ ፕሮግራም ተቋም በአሕጽሮት ሃቢታት አስተዳደር አካል ጉባዔ ላይ ነው።

እንደ ተቋሙ አስተዳዳሪ እንደ አና ቲባይጁካ አባባል እየናረ የመጣው የከተማ ነዋሪ ቁጥር፤ አብዛኛው የሚገኘውም በታዳጊ አገሮች ነው፤ በዚህ ዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ከፍ ይላል። በሚቀጥሉት 13 ዓመታትም በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል ነው የሚገመተው። ሁለተኛው ቢሊዮን ችግር ሊታከል ብዙም አልቀረውም ማለት ነው። ገና ከዛሬው በቢሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከአንዲት ዶላር ባነሰች ከዕጅ-ወዳፍ የዕለት ገቢ ኑሮውን የሚገፋ መሆኑ ይታወቃል። አዝማሚያው ዛሬም አልሰምር ባለው ልማት ላይ ምን ያህል የባሰ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ለማሰብ ብዙም አያዳግትም። የከተሞች ድህነት ይበልጥ እየተስፋፋ በሚሄድባቸው የመጤ አካባቢዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ 2015 ዓ.ም. ድህነትን በከፊል ለመቀነስ የነደፈው የሚሌኒየም ዕቅድ ዕውን ይሆናል ብሎ ማሰቡ ዘበት ነው። ብዙዎቹ ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ከዛሬው ተጨባጭ ሃቅ አንጻር የሚሌኒየሙ ዕቅድ ካስቀመጣችው ሥምንት ግቦች አንድ ሁለቱን እንኳ ቢያሟሉ የተዓምርን ያህል ነው የሚሆነው። አንዳንዶቹ እንዲያውም ለምንም የሚበቁ ሆነው አይገኙም።

የመጸዳጃና የንጹሕ ውሃ እጦት፣ የጤና አገልግሎት አለመኖር ለተለያዩ በሽታዎች መከሰት ምንጭ ሲሆን ለብዙዎች ነፍሰ-ጡር እናቶችና ሕጻናት፤ ሌሎችም ሞት ዓቢይ ምክንያት ነው። በነገራችን ላይ የሕጻናትን በአጭር መቀጨት ማስወገዱም የሚሌኒየሙ ዕቅድ አንድ ግብ መሆኑ ይታወቃል። ችግሩ በዚህ ሁኔታ እንዴት? ነው። ለማንኛውም የድሆቹን የከተማ ነዋሪዎች ችግር መቋቋም ሳይቻል ከዚህ አዙሪት መውጣት የሚሳካ አይሆንም። ቁጥሩ እየናረ የሚሄደው ድሃ ሰፋሪ በፍጆቱም ሆነ በኤኮኖሚ እንቅስቃሴው የማይናቅ በመሆኑም አስፈላጊው ማህበራዊ መዋቅር ሳይመቻችለት ልማት መገኝቱ የሚያጠያይቅ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም ተቋም በበኩሉ በድሆች አካባቢዎች ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቋቋም የችግሩ ባለቤቶች ራሳቸው መኖራያቸውን እንዲያንጹ ብድር በመስጠት ለመርዳት ያቅዳል። ይህ የአማካይ ጊዜ ዕቅድ የተጸነሰው ባለፈው ሣምንት የተቋሙ አስተዳደር ስብሰባ ላይ ሲሆን የከተማ ድሆች መጠለያ እንዲያገኙ ማብቃቱ አጣዳፊ ተግባር መሆኑ ታምኖበታል። ጥያቄው እርግጥ እንዴት ዕውን ይሆናል ነው።

የታዳጊው ዓለም በተለይም የአፍሪቃ መንግሥታት የራሳቸውን ነዋሪዎች የመጠለያ ጎጆ ፍላጎት በማሟላቱ በኩል በተለያዩ ምክንያቶች ብቁ ሆነው አይገኙም። ሌላው ቀርቶ የመጸዳጃና የመጠት ውሃ ችግሮችን እንኳ መፍትሄ መስጠት የተሣናቸው ናቸው። ስለዚህም መንግሥታትና የግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ችግሩን ለመቋቋም መተባበር ይጠበቅባቸዋል። ማለት ድሆች የከተማ ነዋሪዎች የራሳቸውን ቤቶች እንዲሰሩ ገንዘብ የሚያገኙበትን ሁኔታ በዚህ የትብብር መልክ ማመቻቸቱ ግድ ነው። ዓለምአቀፉ የሰፈራ ተቋም በአማካይ ጊዜ ዕቅዱ ለነዚህ ፕሮዤዎች በተናጠል ተዘዋዋሪ ሂሣብ ለመክፈት ያስባል። ይህ ሂሣብ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ብድር የሚሰጥበት ነው። አንዴ መልሶ ከተከፈለ በኋላ ደግሞ በአዲስ ብድርነት እንዲቀርብ ይደረጋል። ገንዘቡ እንዲህ እየተዘዋወረ ለሁለት፣ ለሶሥትና ለአራት ፕሬዤዎች ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ማለት ነው። ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች መኖሪያ ቤትና መዋቅራዊ ፕሮዤዎች የታቀደው ብድር በሰፈራው ተቋም አጀንዳና ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት መርሆች መሠረት ሥራ ላይ እንዲውል ለማሕበራዊ ድርጅቶችና መዘጋጃ ቤቶች የሚቀርብ ይሆናል።

የተዘዋዋሪው፤ ማለት መልሶ-መላልሶ በስራ ላይ የሚውለው ብድር ዕቅድ እስከ 2016 ዓ.ም.ና ከዚያም ለዘለቀ ጊዜ በውል በተሰላ በሶሥት ደረጃ የሚካሄድ ነው። ይሁንና የታዳጊው ዓለም መንግሥታት ሃሣቡን ቢያወድሱትም አበዳሪ ሃገራት በአንጻሩ ለምን ተጨማሪ መንገድ አስፈለገ የሚል ጥያቄ ማንሣታቸው አልቀረም። እነዚሁ ዓለምአቀፉን የምንዛሪ ተቋም IMF-ን የመሳሰሉ ለድሆች አገሮች ብድር የሚያቀርቡ ድርጅቶች መኖራቸርን ያሳስባሉ። ይሁን እንጂ የሃቢታት አስተዳዳሪ አና ቲባይጁካ የገንዘቡ ተቋማት ለድሃ ድሃው ገንዘብ የሚያቀርቡበት መዋቅርም ሆነ በነዚህ ማሕበራዊ ችግሮች ረገድ ብቃት የላቸውም ባይ ናቸው። የገንዘብ ተቋማቱ በእርግጥም ብድሩን ለማዕከላዊ መንግሥታት ከማቅረብ ባሻገር ለድሆች ወይም በነርሱ ላይ ላተኮሩ ማሕበራዊ ቡድኖች አይሰጡም። የተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ፕሮግራም ተቋም በወቅቱ ዕቅዱ እርግጥ ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋም የመሆን ሃሣብ የለውም። ዓላማው እንደተነገረው ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ የድሆቹን የከተማ ሰፋሪዎች ችግር መቋቋም ነው።

የበለጸጉት መንግሥታት ለድሆች አገሮች በተለይም ለአፍሪቃ የልማት ዕርዳታቸውን ከፍ ለማድረግ የገቡትን ቃል የሚገባውን ያህል በተግባር ሲተረጉሙት አይታይም። ይህ ለነገሩ በየጊዜው የሚነሣ ጉዳይ ነው። የጀርመን መንግሥት በበኩሉ በዓመቱ መጀመሪያ እንደ አውሮፓ ሕብረት ሁሉ የ G-8 ን ርዕስነትም ከያዘ ወዲህ የአፍሪቃን የልማት ዕርዳታ ዓቢይ የአጀንዳ ርዕስ በማድረግ ጭብጥ ነገር ለመሥራት ቢቀር በሃሣብ መነሣቱ አልቀረም። ይህም የሚያበረታታ ሲሆን በርሊንም ለዚህ መሰሉ ዓላማ ትኩረት ሳቢ እየሆነች ነው።

የቀድሞውን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናንን የመሳሰሉ ታዋቂ ግለሰቦች አሁን በዚሁ በበርሊን በመሰባሰብ ለአዲስ የአፍሪቃ የልማት ጥረት ”Africa Progress Panel” የአፍሪቃ የዕድገት መድረክ ሕያው አድርገዋል። ከጥረቱ አንቀሳቃሾች መካከል ያለፈው ዓመት የሰላም ኖቤል ተሸላሚና የመለስተኛው ብድር ሃሣብ አንቀሳቃሽ የባንግላዴሹ ተወላጅ ሙሐማድ ዩኑስ፣ በፕሬዚደንት ክሊንተን ዘመን የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ሮበርት ሩቢንና የአንዴው የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም የ IMF አስተዳዳሪ ሚሼል ካምዴሱን የመሳሰሉት ይገኙበታል።

የነጻው አካል ሊቀ-መንበር የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን እንደሚሉት መድረኩ በአፍሪቃ ላይ ከሚያተኩሩት ድርጅቶች አንዱ ብቻ በመሆን መወሰኑን አይፈልግም። “ይህ ቡድን በተግባርና በተግባራዊ ውጤቶች ላይ የሚያተኩር ነው። ዘገቦችን የሚደረድር ሌላ ተጨማሪ ድርጅት ለመሆን አንፈልግም። ሰፊ ልምድና የሕሊና ፍርድ ብቃት ይዘን ነው የምንቀርበው። ይህን ደግሞ ከፖለቲካ መሪዎች በቀጥታ በሚደረግ ንግግርና ይፋ መግለጫ መንግሥታት ሃሣቡን ከግቡ ለማድረስ አዲስ ጥረት እንዲያደርጉ ልንገፋበት እንፈልጋለን”

አናን ግብ ያሉት በሚቀጥሉት ሥምንት ዓመታት ውስጥ መሣካት የሚኖርበትን ድህነትን በግማሽ የመቀነስ ሃሣብ ጭምር የጠቀለለ የሚሌኒየም ዕቅድ ነው። እንደርሳቸው ብቻ ሣይሆን እንደ ብዙዎች ታዛቢዎች ደግሞ ቀደምቱ የበለጸጉ መንግሥታት ከሶሥት ዓመታት ገደማ በፊት ስኮትላንድ-ግሌንኢግልስ ላይ የገቡትን ቃል አክብረው ዕርዳታቸውን በፍጥነት ዕውን ካላደረጉ አፍሪቃ ከተጣሉት ግቦች መድረሷ የማይታሰብ ነገር ነው።

የቀድሞው ዋና ጸሐፊ እንዳስረዱት መድረካቸው እርግጥ የአፍሪቃን መንግሥታትም ለጭብጥ ዕርምጃ የሚገፋፋ ነው። ኮፊ አናን፤ “ዋናው ሃላፊነት ያለው በአፍሪቃ መንግሥታት ዘንድ ነው። ግን ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ለነገሩ ዕርዳታ ለመስጠት ቃል መገባቱ አልቀረም። እናም ይህ የተገባው የዕርዳታ ቃል መከበር እንዳለበት ተሥፋ፤ ልበል ተሥፋ ተገቢው ቃል አይደለም፤ እንደሚከበር እጠብቃለሁ”

ሃቁ መላው የ G-8 ቡድን መንግሥታት፤ ጀርመንንም ጨምሮ ከገቡት ቃል ገና አሁንም ሲበዛ ኋላ ቀርተው መገኘታቸው ነው፤ የመድረኩ ባልደረባ ታዋቂው የሮክ ሙዚቃ ኮከብ ቦብ ጌልዶርፍ እንደሚያስገነዝበው። ጌልዶርፍ ለአፍሪቃ ዕርዳታ “Live-Aid” ትርዒቶችን በማዘጋጀት ታላቅ ዓለምአቀፍ ትኩረትን መሣቡ ይታወሣል። “ሃብታሞቹ አገሮች በኤኮኖሚ ወደ ኋላ ለቀሩት ድሆች አገሮች ቃል ሲገቡ፤ ይህ ቃል ከሁሉም በላይ የተቀደሰ ሆኖ ሊታይ ይገባዋል። ምክንያቱም ቃሉን ባታከብር ሰውን የምትገል መሆኑ ነው” ጌልስዶርፍ እንዳለው!

ቦብ ጌልዶርፍ በፊታችን ሰኔ ወር በዚህ በጀርመን በሃይሊገንዳም በሚካሄደው የሃያላኑ 8 መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ አኳያ የሚካሄዱትን ከአሁኑ “ጸረ-G-8 ጉባዔ” የሚል ቅጽል የተሰጣችውን ትዕይንቶች ከሚያዘጋጁትም አንዱ ነው። እርግጥ ጌልዶርፍ ዘመቻውን ጸረ G-8 አድርጎ አይመለከተውም። በርሱ አባባል፤ “የጀርመንን ጠበብት፤ ስለ ዓለም አጥብቀው የሚያስቡ ሰዎች፤ ፈላስፎችና ምሁራንን መሰብሰብ ማለት የተቃውሞ እንቅስቃሴ መፍጠር ማለት አይደለም። ለወደፊቱ ማሰብ እንጂ”
ታዲያ የ G-8 መንግሥታት መሪዎች ጉዳዩን እንዲህ ይመለከቱት ይሆን? ቢሆን ምንኛ በበጀ!