ተፅኖ ፈጣሪ አፍሪቃዉያን ሴቶች
አፍሪቃዉያን ሴቶች በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ተሳትፎአቸዉ ምን ይመስላል? በአህጉሪቱ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ሴቶች የከፍተኛ ስልጣናት መንበርን ሲረከቡ ይስተዋላል። በዓለማችን እጅግ ከፍተኛ ሐብት አላቸዉ ከሚባሉ ሰዎች መካከል አፍሪቃዉያን ሴቶች ይገኙበታል።
ከፍተኛ ድል ለኢትዮጵያ ሴቶች
አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከጥቅምት 15 ቀን፤ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሆዉ ተሾመዋል፡፡ አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዚደንት ናቸዉ። የወንዶች የፖለቲካ እና ኤኮኖሚ የበላይነት በሚታይበት ኢትዮጵያ አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ወደ ርእሰ ብሔርነት ሥልጣን መምጣት ለሃገሪቱ ለሴቶች ከፍተኛ ድል ሆኖ ታይቶአል። ከርዕሰ ብሔር አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ሌላ የሃገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴርነት ሥልጣንነትን ጨምሮ አዲሱ ካቢኔ ገሚሱ ሴቶች ከፍተኛ ባለስልጣናት ሆነዋል።
በአፍሪቃ የመጀመርያዋ ተመራጭ ሴት ፕሬዚዳንት
ኤልን ጆንሰን ሴርሊፍ በዴሞክራስያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡ የመጀመርያዋ አፍሪቃዊት ፕሬዚዳንት ናቸዉ። ሴርሊፍ ከጎርጎረሳዉያኑ 2006 እስከ 2018 ዓ.ም የላቤርያ ፕሬዚዳንት ሳሉ ሥራ አጥነትን፤ ሃገራቸዉ ያለባትን እዳ ለመቅረፍና በሴራሌዮን የኤቦላ ቫይረስ እንዳይሰራጭ ተግተዉ ሰርተዋል። ለሴቶች ደሕንነትና ፍትህ ላበረከቱት አስተዋጽኦ በጎርጎረሳዊዉ 2011 የሰላም ኖቤል ተሸላሚም ሆነዋል። ሰርሊፍ ዛሬ በተመድ የአህጉሪቱ የፍልሰት ጉዳይ ተመልካች ቢሮ ሊቀመንበር ናቸዉ።
ሩዋንዳዊቷ ከፍተኛ ጠበቃ
ሩዋንዳ ከ10 ዓመት ወዲህ ከፈረንሳይኛ ይልቅ ኢንጊሊዘኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ቢደነገግም የሩዋንዳ የቀድሞ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊዝ ሙሲኪዉቦ በጎርጎረሳዊዉ 2019 የሩዋንዳ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ማኅበረሰብ ዓለምአቀፍ ድርጅት ተጠሪ እንዲሆኑ ተሾመዋል። የሉዊዝ መመረጥ በተለይ በዲፕሎማሲዉ ሥራ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠዉ ነዉ ተብሎአል። ሉዊዝ ሙሲኪዉቦ ከፈረንሳዩ ፕሬዚደንትና ከሌሎች የዉጭ ሃገራት ባለሥልጣናት ድጋፍን አግኝተዋል።
አንዲት ሴት እና 193 ሃገራት
ከጎርጎረሳዉያኑ 2017 ጀምሮ በተመድ ተለዋጭ ፀሐፊ ሆነዉ በማገልገል ላይ ያሉት ናይጀርያዊትዋ አሚና ሞሐመድ ሌላዋ የአህጉሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ናቸዉ። አሚና ሞሐመድ ከጎርጎረሳዊዉ 2002 እስከ 2005 ድረስ በተመ በአምዕቱ የልማት ግቦች ዘርፍ አገልግለዋል። ከዝያ በመለጠቅ የቀድሞዉ የተመድ ዋና ፀሐፊ የባን ኪሙን ልዩ አማካሪም ነበሩ። በተመድ የአማካሪነት ሥራ ተልኮአቸዉን ሲያጠናቅቁ ደግሞ፤ በናይጀርያዉ ፕሬዚደንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የሥልጣን ዘመን የሃገሪቱ የአካባቢ ተፈጥሮ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ አገልግለዋል።
እዳን ለማቃለል የታገሉት ናሚቢያዊት
ናሚቢያዊቷ ሳራ ኩጎንጌላዋ አማዲላ ከጎርገረሳዉያኑ 2015 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዉ ናሚቢያን እያስተዳደሩ ነዉ። አሚና በሃገሪቱ የተመረጡ የመጀመርያዋ የሴት ጠቅላይ ሚኒስትርም ናቸዉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አሚና ወደዚህ ስልጣን ከመምጣታቸዉ በፊት የሃገሪቱ የገንዘብ አስተዳደር ሚኒስትር ሆነዉ አገልግለዋል። በዚህ ስልጣናቸዉ ሃገሪቱን ከእዳ ሊያቃልል የሚችል መርህ ቀርፀዉ ናሚቢያ ከተሸከመችዉ እዳ አቃለዋታል። የኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁርዋ ናሚቢያዊት ከጎርጎረሳዉያኑ 1995 ጀምሮ የናሚቢያ ብሔራዊ ምክር ቤት አባልም ናቸዉ።
በሃገራቸዉ የነዳጅ ዘይት የነገሡት ባለኃብት
ኢዛቤል ዶሻንቶስ በአንጎላ አወዛጋቢ ባለሥልጣን ናቸዉ። ከጎርጎረሳዉያኑ 2016 ጀምሮ የአንጎላ የነዳጅ ምርት ኩባንያን በዳይሬክተርነት የመሩት ኢዛቤል፤ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶሻንቶስ ልጅ ናቸዉ። አሁን ወደ ሥልጣን የመጡት የአንጎላ ፕሬዚዳንት ለባለሥልጣናት በዝምድና የሚሰጥን ድጋፍም ሆነ ሥራ የሚቃወሙ በመሆናቸዉ ወደ ስልጣን እንደመጡ ነበር የቀድሞዉ ፕሬዚደንት የኤድዋርዶ ዶሻንቶስን ልጅ ኢዛቤልን ከነበራቸዉ ስልጣን ያነስዋቸዉ። ሆኖም ግን ኢዛቤል ዶሻንቶስ ሲያስተዳድሩት የነበረዉን የሃገሪቱን የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ገቢ ዱባይ ወደሚገኝዉ የግል ባንካቸዉ ያከማቹ«ይሰርቁ»ስለነበር አሁንም በሃብት ዳጎስ እንዳሉ ናቸዉ።
ያልተነገረላቸዉ ተፅኖ ፈጣሪ የኮንጎ ሴት
ምስጢር በመጠበቅና ከፍተኛ ጥንቃቄያቸዉ የሚታወቁት ጃኔት ካቢላ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት የጆሴፍ ካቢላ መንትያ እህት ናቸዉ። ጃኔትና ጆሴፍ ደግሞ የቀድሞዉ የኮንጎ ፕሬዚዳንት ልጆች መሆናቸዉ ነዉ። ጃኔት ካቢላ በዴሞክራቲክ ኮንሆ የፓርላማ አባል ናቸዉ። ከዝያ በተጨማሪ የአንድ የቴሌቭዥን፤ ራድዮና የኢንተርኔት ማሳረጫ ኩባንያ ባለቤት እና አስተዳዳሪ ናቸዉ። ጃኔት አንድ ወቅት ለአንድ የፈረንሳይ መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ በሃገራቸዉ ከሚገኙት ተፅኖ ፈጣሪ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዷ ነኝ ብለዉ መናገራቸዉ ይጠቀሳል።
ወጣትዋ የማሊ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ወጣትዋ የማሊ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካሚሳ ካማራ በሃገሪቱ ታሪክ የተመረጡ የመጀመርያዋ ሴት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸዉ። የ 35 ዓመትዋ ወጣት ሚኒስትር ለዳግመኛ የሥልጣን ዘመን ለተመረጡት ለማሊዉ ፕሬዚዳንት ባቡከር ኪየታ ካቢኔ ከተሾሙት 11 ሴት ሚኒስትሮች መካከል አንዷ ናቸዉ። የማሊ የመንግሥት የሚንስትሮች ምክር ቤት በአጠቃላይ 32 ሚኒስትሮችን ያቀፈ ነዉ።
ናይጀርያዊቷ ባለሐብትና በጎ አድራጊ
ናይጀርያዊቷ ቱጃር ፍሎሩንሾ አላካጃ የ 1,6 ቢሊዮን ዶላር ባለንብረት መሆናቸዉ ይነገርላቸዋል። የነዳጅ ጥሪ ሃብትን በታደለችዉ ናይጀርያ ፍሎሩንሾ አላካጃ «ፋማ ኦይል» የተባለ የነዳጅ ማምረቻ ኮባንያ አስተዳዳሪና ባለንብረት ናቸዉ። ይኸዉ ንብረታቸዉ ታድያ በሃገሪቱ ከሚኖሩ ዜጎች በሐብት ክምችት ሦስተኛዋ የናይጀርያ ቱጃር አድርጎአቸዋል። እንደ አንጎላዋ ኢዛቤል ዶሻንቶስ ሁሉ ናይጀሪያዊቷ ፍሎሩንሾ አላካጃም በዓለማችን ከሚገኙ በጣም ቱጃሮች ከሚባሉት ጥቂት ሰዎች መካከል አንድዋ ናቸዉ። የ 67 ዓመትዋ ናይጀርያዊት ባለሐብት በአቋቋሙት የሕጻናት መርጃ ተቋም ወላጆች የሌላቸዉን ልጆች ይረዳሉ።