1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዋሚው የሐረሪ ዴሞክራሲዊ ድርጅት ከ12 አመታት በኋላ ወደ ሐረር ተመለሰ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2011

የሐረሪ ዴሞክራሲዊ ድርጅት (ሐዲድ) ከ12 አመታት በኋላ ወደ በኋላ ወደ ሐረሪ ክልል ተመልሶ በፖለቲካው ዘርፍ ለመስራትና በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ሀዲድ ክልሉን በመምራት ላይ የሚገኘው የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) ትላንት ባዘጋጀው የዕርቀ ሰላም መድረክ ላይም ተሳትፏል፡፡

https://p.dw.com/p/3HEMy
Stadtmauer von Harar Stadt im Südosten von Äthiopien
ምስል Azeb Tadesse Hahn

ፓርቲው በመጪው ምርጫ ለመወዳደር አቅዷል

የሐረሪ ዴሞክራሲዊ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ አብዲ ሰቡር ለዶይቼ ቬለ (DW) በስልክ እንደገለፁት ድርጅቱ ካለፉት አመታት ጀምሮ ከሀብሊ ጋርም ሆነ ወደ ክልሉ ገብቶ ቢሮ መክፈት እና መንቀሳቀስ ሳይችል ቆይቷል፡፡ መቀመጫውን አዲስ አበባ አድርጎ ሲታገል የቆየው የሐረሪ ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ ከ12 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ክልሉ የተመለሰው በክልሉ ያለው አዲስ አመራር ባቀረበው ጥሪ መሰረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ ከወራት በፊት ላለፉት አመታት ክልሉን እና ሐብሊን በበላይነት ሲመሩ የቆዩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሀዲ ከሀላፊነት ተነስተው አቶ ሁርዲን በድሪ በሀላፊነት መሾማቸው የሚታወስ ነው ፡፡ 

የሐዲድ ሊቀመንበር ድርጅታቸው በሐረሪ ክልል ጽህፈት ቤት መክፈት እና አባላት ማደራጀት “ቀጣይ እና ዋነኛ ስራው” እንደሚሆን ተናግረዋል። ሐዲድ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍም አረጋግጠዋል፡፡

የሐረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሐብሊ) ተወካይ እና የእርቀ ሰላም መድረኩ አስተባባሪ አቶ አሚር አሊ መድረኩ የሐረሪ ህዝብ ያሉበትን ችግሮች ለመፍታትና የተቀናጀ ስራ ለመስራት የክልሉ ገዢ ፓርቲ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለክልሉ ህዝብ በአጠቃላይ ጥሪ በማድረጉ የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “በተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ድርጅቶች የሚከናወኑ ተግባራትን ለመደገፍ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ዝግጁ ነው” ያሉት አስተባባሪው “የእነሱ በክልሉ መኖር ለሀብሊም ሆነ ለክልሉ ህዝብ ጠቃሚ ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ “ቢሮ ከፍቶ መስራትና መንቀሳቀስ በክልሉ ገዢ ፓርቲ የሚፈቀድ አሊያም የሚሰጥ ሳይሆን ህገ መንግስታዊ መብት ነው” ሲሉም አክለዋል። 

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ