1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተስፋ ቢሱ የሶርያ የተኩስ አቁም ስምምነት

እሑድ፣ የካቲት 6 2008

በሙኒኩ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉባኤ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ መኾን አለመቻሉ ተገለጠ። «የሩስያ ጦር የሶሪያ መንግሥት ወታደሮችን በመደገፍ ከትናንት አንስቶ አማፂያንን እየደበደበ ነው» ሲሉ ምዕራባውያን ሃገራት ወቀሳ አሰምተዋል።

https://p.dw.com/p/1HvKz
München Sicherheitskonferenz - Moshe Yaalon
ምስል Reuters/M. Dalder

ውጥረቱን ተከትሎ የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የዩናይትድ ስቴትሱ አቻቸው ባራክ ኦባማ ዛሬ በስልክ ተነጋግረዋል። ፕሬዚዳንቶቹ በሶሪያ የተኩስ አቁም ስምምነቱ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን እንዲኾን ነው የተነጋገሩት። የሩስያው ጠቅላይ ሚንስትር ድሚትሪ ሜድቬዴቭ በሙኒኩ ጉባኤ «ወደ ቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት እያመራን ነው» ሲሉ ትናንት መናገራቸውን ተከትሎ ነው ፕሬዚዳንቶቹ በስልክ የተነጋገሩት። የዓለም ኃያላን ሃገራትን ያሳተፈው የሶሪያው የእርስ በእርስ ጦርነት መቀጠል አውሮጳ በስደተኞች ቀውስ አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ አድርጓል።
ይኽ በእንዲህ እንዳለ በሙኒኩ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉባኤ የጀርመኑ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ለስደተኞች ቀውስ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። «ይህ የስደተኞች ቀውስን ለመወጣት ምንም እንኳን በሁሉም ሀገራት ደረጃ ከባድ ቢሆንም ፤ ምክንያት ሊሆነን እና መጋረጃችንን ዘግተን ልንሸሸግ አይገባም። ይልቁንስ እኔ እንደሚመስለኝ ይህ የስደተኞች ቀውስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ለውሳኔ መትጋት እንዳለብን ማነቃቂያ ሊኾነን ይችላል።»

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) ዋና ጸሓፊ ዬንስ ሽቶልቴንበርግ በበኩላቸው በአኹኑ ወቅት የሚታየው የስደተኞች ቀውስ መፍትኄ እንዲበጅለት አሳስበዋል። ዛሬ የሚጠናቀቀው የሙኒኩ የጸጥታ ጉባኤ ዋና ትኩረት የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪቃ ግጭቶች ነበሩ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ