1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተስፋና ጭንቀት፤ ሊቢያ በምርጫ ዋዜማ

ሰኞ፣ ሐምሌ 2 2004

ከአርባ ዓመታት በላይ ከዘለቀ የአምባገነን አስተዳደር በኋላ ሊቢያውያን እሁድ ዕለት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አከናውነዋል። ውጤቱን ሊቢያውያን በጉጉት እየጠበቁት እንደሆነም ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/15UHh
ቤንጋዚ፣ የምርጫው ሂደት ሲጠናቀቅ
ቤንጋዚ፣ የምርጫው ሂደት ሲጠናቀቅምስል Reuters
ምርጫ በሊቢያ
ምርጫ በሊቢያምስል DW/E.Zuber

ሊቢያውያን ታሪካዊና ዲሚክራሲያዊ የተባለለትን ምርጫ እሁድ፣ ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ማካሄዳቸው ተሰምቷል። አርባ ዓመታት ግድም በአምባገነን መንግስት የማቀቁት ሊቢያውያን የትናንቱን ፌሽታ ለመቋደስ በርካታ መስዋዕትነትን መክፈል ግድ ብሏቸው ነበር። መስዋዕትነቱ የሺዎችን ህይወት ግብር ጠይቆ፤ የበላውን በልቶ ያደማውን አድምቶ አልፏል። ታዲያ የሊቢያውያን አብዮት ከጠየቀው የህይወት ግብር የተረፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ትናንት በደስታ ከአደባባይ ወጥተው መፈንጠዛቸው ተሰምቷል። የህክምና ተማሪው ወጣት ሜፍታህ ላህዌል ግን ከጎዳናው ይልቅ በአንድ ሻይ ቤት ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር መምከርን ነው የመረጠው።

«ምርጫው በረዥሙ ጎዳና የመጀመሪያው ርምጃ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። የሂደቱ መጨረሻ ግን አይደለም። እስካሁን ምርጫውን ማካሄድ ነው የተሳካልን። ገና ብዙ ስራ ይጠብቀናል»

ሆኖም ወጣቱ የህክምና ተማሪ በሊቢያ ዲሞክራሲ መሰረት እንደሚይዝ ተስፋ ቢኖረውም ሂደቱ ግን ገና ብዙ ፈተና እንደሚጠብቀው ይሰማዋል። መላ ትሪፖሊ ትናንት በባንዲራ ደምቃ ነበር የዋለችው። ነዋሪው የአብዮቱን መዝሙር እየዘመረ በሲቃ ሲጨፍር አምሽቷል። የአውሮጳ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንደነበር ጠቅሷል። የታዛቢ ቡድኑ አባል እና የአውሮጳ ኅብረት እንደራሴው አሌክሳንደር ግራፍ ላምብስዶርፍ የምርጫ ሂደቱን «ታሪካዊ ርምጃ» ሲሉ አወድሰውታል። ወጣት ዋሴፍ
ሳሌም አልብድራይን እንደህክምና ተማሪ ጓደኛው የሊቢያ የወደፊት ዕጣ የተሻለ እንዲሆን ይመኛል።

«ነገሩ በጣም ነው ያጓጓኝ። የሆነ ጥሩ ነገር እንደሚያደርጉ ተስፋ አለኝ። ህገ-መንግስታችን ዲሞክራሲያዊ ይሆን ይሆናል። ጠንካራ ዲሚክራሲያዊት ሀገርም መመስረት እንችላለን። ወይንም ደግሞ ፈፅሞ የተለየ ነገርም ሊከሰት ይችላል። ልክ እንደ ሌሎቹ አረብ ሀገራት ሁሉ ባህላዊ ህገ-መንግስት ያረቁ ይሆናል፤ ያኔ የሆነው ነገር ሁሉ ዋጋ አጣ ማለት ነው። »

የህክምና ተማሪው ሜፍታህም ሆነ ጓደኛው ሳሌም የግብፅን እና የቱኒዚያን የአብዮት ማግስት ካጤኑ በኋላ የሊቢያም ተመሳሳይ እንዳይሆን ሳይሰጉ አልቀሩም። ወጣቶቹ የሀይማኖት እና የጎሳ ጉዳይ በሊቢያ የወደፊት ዕጣ ላይ ታላቅ ስጋት እንደደቀነ ይሰማቸዋል። ታዲያ ህልማቸው ሁሉ የቀን ቅዠት ሆኖ እንዳይቀር በሠብዓዊ መብቶች ጉዳይ እና ዲሞክራሲ በተመለከተ ብዙ መስራት እንዳለባቸው ይገልፃሉ። ሊቢያ ከአራት አስርት ዓመት በኋላ ከአምባ ገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ጎዳና እያቀናች ነው። ለወጣቶቹ ግን የትናንቱ ምርጫ የአብዮቱ ስኬት ገና መንደርደሪያው መሆኑ ነው።

ምርጫ እና ፌሽታ በሊቢያ
ምርጫ እና ፌሽታ በሊቢያምስል picture-alliance/dpa

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ