1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተማሪ ቤት፤ መረጃዎችን በማቅረብ ተማሪዎችን የሚያግዘው መተግበሪያ

ረቡዕ፣ መስከረም 26 2014

«ተማሪ ቤት» በመባል የሚጠራው ይህ መተግበሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች የትምህርት መረጃዎችን በየደረጃው ለሚገኙ ተማሪዎች በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚያደርስ ነው።

https://p.dw.com/p/41LDO
Habitamu Assefa, App Temari Bet
ምስል privat

መረጃዎችን በማቅረብ ተማሪዎችን የሚያግዘው  መተግበሪያ


ትምህርት ነክ ቴክኖሎጅዎች የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ረገድ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጡት እገዛ ከፍተኛ  መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።ከወደ አዲስ አበባም ሁለት ወጣቶች  በየ ደረጃው ለሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታዊ መረጃዎችን በተንቀሳቃሽ ስልክ ለማድረስ  የሚያግዝ መተግበሪያ ሰርተዋል።የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም ትኩረቱን በዚሁ መተግበሪያ ላይ አድርጓል። 
በኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመማማር ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ፣የሳይንስ እና የባህል  ድርጅት  መረጃ ያሳያል። ይሁን እንጅ የትምህርት ጥራትን የሚወስኑት ብቁ መምህራን የመፃህፍትና  የቤተ-መፃህፍት እጥረት እንዲሁም የመማሪያ ክፍሎች ጥበት አሁንም ድረስ ችግሮች ናቸው።ሁለት የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች  ይህንን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ የሚያግዝ መተግበሪያ  ሰርተዋል። «ተማሪ ቤት» በመባል የሚጠራው ይህ መተግበሪያ በተለያዩ ቋንቋዎች  የትምህርት መረጃዎችን በየ ደረጃው ላሉ ተማሪዎች በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚያደርስ ነው።

Habitamu Assefa, App Temari Bet
ምስል privat

የመተግበሪያው መስራች እና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአራተኛ አመት የሜዲካል ቴክኖሎጅ ተማሪ  የሆነው ወጣት ሀብታሙ አሰፋ እንደሚለው ይህንን መተግበሪያ ለመስራት ምክንያት የሆነው በትምህርት ቤቶች በተጨባጭ የተመለከተው ችግር ነው።
የአንደኛ ዓመት የዩንቨርሲቲ ተማሪ እያለ ተማሪዎችን ለማስጠናት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተሰማራበት ወቅት ካጋጠመው ችግር  በተጨማሪ ተወልዶ ባደገባት መተሀራ ከተማ  የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበት  ወቅት ይመለከተው የነበረው የትምህርት አሰጣጥ፣ የመጽሃፍት ይዘት እና ትምህርትን ለዕውቀት ሳይሆን ለፈተና ብቻ አድርጎ የመመልከት ችግርም መተግበሪያውን ለመስራት ለወጣቱ ሌላው መነሻ  ነበር።
ሀብታሙ መተግበሪያውን የሰራው በጎርጎሮሳዉያኑ 2019 ዓ/ም ሲሆን ከዓመት በኋላ ግን የዩንቨርሲቲ ጓደኛው ናትናኤል ጉሽማ በስራው እንዲካተት በማድረጉ መተግበሪያውን በጋራ በማሻሻል  በዋናነት ሁለት አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ማድረግ ችለዋል።በዚህም የተማሪዎች የመማር ፍላጎት እንዲጨምር ከማድረግ አንፃር ጥሩ ምላሽ መገኘቱን ይገልፃል።

Habitamu Assefa, App Temari Bet
ምስል privat

በበይነ-መረብ ግንኙነት እንዲሰራ ተደርጎ የተሰራው ይህ መተግበሪያ ፤ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ በተጨማሪ በአማርኛ በኦሮምኛና በትግርኛ ቋንቋዎች ትምህርታዊ መረጃዎችን በፅሁፍ በድምፅና በምስል ለተማሪዎች የሚያደርስ ሲሆን ለወደፊቱም  ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን የማካተት ዕቅድ አላቸው።ወጣቱ እንደሚለው ይህንን ማድረግ የፈለጉበት ዋናው ምክንያትም እንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ትምህርት ነክ ቴክኖሎጅዎች የትምህርት ጥራትን በማሻሻል ረገድ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጡት እገዛ ከፍተኛ  ነው።በዚህ ረገድ መተግበሪያው  በኢትዮጵያ የመጽሐፍት እና የቤተ -መጻህፍት እጥረትን ለማቃለል ጥሩ አማራጭ በመሆን ያገለግላል። ያም ሆኖ የገንዘብ እጥረት፣የፈጠራ ስራዎችን ወደ ገንዘብ መቀየርን በተመለከተ እንዲሁም ከፈጠራ ጋር የተያያዙ የመንግስት አሰራሮች ላይ መረጃ የማግኘት ችግር  ወጣቱ እንደሚለው ፈተናዎች ነበሩ።ኦርቢት የተባለ የግል የቴክኖሎጅ ኩባንያ  ግን ይህንን ክፍተት እንደሞላላቸው ገልጿል። በዚህ እገዛም  በሙከራ ላይ የነበረው መተግበሪያ በዚህ ዓመት  ከጎግል ፕሌይ በማውረድ በተንቀሳቃሽ ስልክ መደበኛ አገልግሎት መስጠት  እንደሚችል ተናግሯል።
ትምህርት ነክ ቴክኖሎጅዎች  በአጠቃላይ በመረጃ ላይ የተመሰረተ የትምህርት ስርዓት ለመገንባት ትምህርቱን ግላዊነትን ማላበስ፣ ብቃትና ጥራት  ባለው መረጃ ላይ የተመሰረተ ማድረግ  እንዲሁም ፈጠራው ቀጣይነት ያለውና በየጊዜው መሻሻያ የሚደረግበት መሆን ያስፈልገዋል።በዚህ ረገድ «ተማሪ ቤት »መተግበሪያ  ልምድ እና በማስተማር ዘዴ ዕውቀት ያላቸውን የትምህርት ባለሙያዎችን በአማካሪነት  የሚያሳትፍ መሆኑን ገልጿል።ለወደፊቱም ከትምህርት ሚንስቴር ጋር በመሆን መተግበሪያውን የበለጠ ለማሻሻል እንደሚጥሩ አብራርቷል። ተማሪዎች ደስ ብሏቸው እንዲማሩ ማድረግ ተቀዳሚ ዓላማቸው መሆኑን የሚገልፀው ወጣቱ የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት በማነሳሳት በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ቢያንስ 50 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅደዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ