1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡሩንዲ ርዋንዳን ወነጀለች

ማክሰኞ፣ መጋቢት 20 2008

ርዋንዳ ‘’የዘር ፍጅት’’ን ለመቀስቀስ እየሞከረች ነው ስትል ቡሩንዲ ወነጀለች። በስልጣን ላይ የሚገኘው ፓርቲ የበላይ ፓስካል ንያቤንዳ ባወጡት መግለጫ የርዋንዳ ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ ‘’የዘር ፍጅት’’ን በአገራቸው ሞክረውታል ብለዋል። የቡሩንዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መንግስታቸው ርዋንዳን በፍርድ ቤት ለመክሰስ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/1ILQl
Bujumbura Burundi Protest Gewalt
ምስል picture-alliance/D. Kurokawa

[No title]

በቡሩንዲ በስልጣን ላይ የሚገኘው ፓርቲ የርዋንዳው ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ የዘር ፍጅትን ወደ አገሬ ለማሻገር ይፈልጋሉ በማለት ወንጅሏል። «ርዋንዳ የዘር ፍጅት ቤተ-ሙከራ ነች» ያለው የፓርቲው መግለጫ ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ «አነስተኛ ኢምፔሪያሊስት ለመሆን ከዚህ ቀደም የሞከሩትን የዘር ፍጅት ወደ ቡሩንዲ ለማሻገር ይፈልጋሉ።» ብሏል። የቡሩንዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አላን ኤሜ ኒያሚትዌ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ «ሉዓላዊነታችንን እና ክብራችንን ተጋፍታለች» ያሏትን ጎረቤት አገራቸውን በፍርድ ቤት ለመሞገት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።

«ርዋንዳ እንደ ሃገር የህዝባችንን ሉዓላዊነት እና ክብር መጋፋቷን የሚጠቁም ማስረጃ አለን። በማንኛውም ሰዓት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ክስ ልንመሰርት እንችላለን።ምክንያቱም ሁለቱም አገሮች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል በመሆናቸው በሰላም አብሮ ለመኖር በሚያስገድዱ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ለመገዛት ተስማምተዋል። አባል አገራት ከቅኝ-ገዢዎቻቸው የተላለፉ ድንበሮችን እንዲያከብሩ የሚያስገድዱ ሰነዶች እና ድንጋጌዎች በጸጥታው ምክር ቤት እና በጠቅላላ ጉባዔው ዘንድ ይገኛሉ። የሌሎች አገራት ድንበሮችን የሚጥሱ አገሮች ፍርድ ቤት ቀርበው ሊዳኙ ይገባል።»

Rwanda Referendum
ምስል picture-alliance/dpa/G. Ehrenzeller

ቡሩንዲ ከጎረቤቷ ርዋንዳ ጋር ያላት ግንኙነት ቀድሞም መልካም የሚባል ባይሆንም ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ለምርጫ መቅረብን ተከትሎ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ በኋላ ዕለት ተለት መሻከሩን ተያይዞታል። እንደ ቡሩንዲ ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ርዋንዳ ከስደተኛ መጠለያ ጣቢያ እየተነሱ በመንግስቱ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ተቃዋሚዎችን ትረዳለች ሲል በወርሃ የካቲት መግለጫ አውጥቶ ነበር። ገዢው ፓርቲ በዕለተ-ዕሁድ ባወጣው መግለጫ ላይ ኃላፊው ፓስካል ንያቤንዳ አንዳንድ የአውሮጳ አገራት ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ በማቅረብ ርዋንዳ ወደ ቡሩንዲ ልታሻግረው ባቀደችው የዘር ፍጅት ውስጥ እጃቸውን አስገብተዋል ሲሉ ወቅሰዋል።

በቡሩንዲ እና ርዋንዳ መካከል ለተፈጠረው መቃቃር «አዎንታዊ እና ሰላማዊ መፍትሔ እየፈለግን ነው» የሚሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አላን ኤሜ ኒያሚትዌ ክስ የመመስረት ውሳኔው መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን ግን አልተናገሩም። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ርዋንዳ በቡሩንዲ ላይ እየፈጸመችው ስላለው ደባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪዎች ጭምር መረጃ አላቸው ሲሉ ተናግረዋል።

«ማስረጃ ያለን እኛ ብቻ አይደለንም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጣሪ ባለሙያዎች ጉዳዩን አጣርተዋል። ሙሉ ዘገባው በመጪው ሰኔ ይፋ ይደረጋል ብዬ አምናለሁ። አጣሪ ቡድኑ ርዋንዳ ቡሩንዲን ለማተራመስ እንቅስቃሴ ማድረጓን የሚጠቁም መረጃ አግኝቷል። ዋናኛ ግቡ ደግሞ ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛን እና መንግስቱን ከስልጣን ማስወገድ ነው። ይህ የተረጋገጠ ነው። ከቡሩንዲ ፍትህ የሸሹ የመፈንቅለ-መንግስት ሞካሪዎች እና መሪዎች የተሸሸጉት በዚያች አገር ነው።»

nach Putschversuch - Präsident Pierre Nkurunziza zurück im Amt
ምስል Reuters/G. Tomasevic

በሑቱ አማጽያን የተመሰረተው የሲ.ኤን.ዲ.ዲ-ኤፍ.ዲ.ዲ. (CNDD-FDD) ፓርቲ ስልጣን የተቆናጠጠው በቡሩንዲ የርስ በርስ ጦርነት ወቅት ብሔራዊ ጦሩን ተቆጣጥሮ የነበረው አናሳ ቱትሲዎችን በመውጋት ነው። ፓርቲው በቡሩንዲ ወደ ስልጣን በመጣ ማግስት ከፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ የአርበኞች ግንባር ፓርቲ ጋር ጥብቅ ግንኙነት የነበረው ቢሆንም ወዳጅነቱ ቀስ በቀስ እየሻከረ ሄዷል።


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ