በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ
ሰኞ፣ ኅዳር 14 2013የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ-መንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የመረጧቸው ሶስት የአፍሪካ አገራት የቀድሞ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት የኢትዮጵያን ፌድራል መንግሥት ከህወሓት ለማደራደር አይደለም ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ “ልዑካኑ በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን ለማሸማገል” በመጪዎቹ ቀናት ወደ አዲስ አበባ ይጓዛሉ ቢሉም ቢልለኔ ግን አስተባብለዋል።
ልዑካኑ ወደ ኢትዮጵያ የሚያመሩት “እኛ የተረዳንውም፤ የተቀበልንውም ከህወሓት ጋር መንግሥትን ለማደራደር አይደለም ” ያሉት ቢልለኔ "የተለያዩ መንግሥታት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፤ ሊገልጹም ይፈልጋሉ። ያ ፍላጎት አለ ማለት በዚህ በኩል ተቀባይነት አለው ማለት አይደለም" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
ቢልለኔ “በእኛ በኩል ክብርት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ [በደቡብ አፍሪካ] ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ነው። ከፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋ ውይይትም እያደረጉ ነው። እዚያ በነበራቸው ቆይታ እና ውይይት መሠረት እነሱ ደግሞ ቀጣይ ልዑክ እዚህ ልከው ከጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንዲነጋገሩ ተቀብለናል። ይኸ የድርድር ወይም የሽምግልና ጉዳይ ከህወሓት ቁጭ ብሎ ወደዚያ አይነት ይገባል ማለት አይደለም” ብለዋል።
የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ክጋሌማ ሞትላንቴ እና የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖን ልዩ ልዑክ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ ሊልኩ መዘጋጀታቸውን የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ያስታወቁት በአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነታቸው በሚገለገሉት ይፋ የትዊተር ገጽ በኩል ነው።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ጋር የተደረገውን ቃለ መጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።
እሸቴ በቀለ