በጀርመን የፔጊዳ ንቅናቄና የሰልፉ እገዳ
ማክሰኞ፣ ጥር 12 2007በምሥራቅ ጀርመንዋ በድሬስደን ከተማ ባለፈው ጥቅምት የተጀመረው በጀርመንኛ ምሕጻር «ፔጊዳ» በመባል የታወቀው ጸረ እስልምና ቡድን እንቅስቃሴ በጀርመን አብይ የመነጋገሪያ ርዕስ ከሆነ ሰነበተ። የፔጊዳ ዓላማና የንቅናቄው አካሄድ ማከራከራከሩ ማወቃቀሱ ቀጥሏል ። የቡድኑ ዓላማና የንቅናቄው ዓላማና የደጋፊዎቹ ማንነትም በውይይቶቹ ከሚያነጋግሩት ነጥቦች ውስጥ ናቸው ፍራንክፈርት ጀርመን ነዋሪ የሆኑት የፖለቲካ ሳይንስና የህግ ምሁሩ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የፔጌዳን ዓላማ እንቅስቃሴውን እንዲህ ገልፀውታል ።
ከሰሞኑ ስለዚሁ ፔጊዳ የተሰባሰበ መረጃ እንዳመለከተው ቡድኑ በሚካሂዳቸው ሰልፎች ላይ የሚካፈሉት ሰዎች ስብጥር ከሌሎች ተቃውሞች የተለየ ነው ። መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከቀኝ ፅንፈኞችም ጋር በነዚህ ሰልፎች ላይ መካፈላቸው በጀርመን አዲስ ክስተት ሆኖ ተገኝቷል ። ዶክተር ለማ እንደሚሉት ደግሞ የፔጊዳ ዓላማው ግን ግልፅ ሆኖ አያታያቸውም ።
። ፔጊዳ ለ13ተኛ ጊዜ ትናንት በድሬስደን ሊያካሂድ የነበረው ሰልፍ በቡድኑ መሪ ሉትዝ ባህማን ላይ የግድያ ዛቻ መሰንዘሩን የሚጠቁም መረጃ ደርሶኛል ባለው ፖሊስ ታግዷል ። የጀርመን ፖሊስ ያገደው የድሬስደኑን የፔጊዳን ሰልፍ ብቻ ሳይሆን ፔጊዳን በመቃወም በዚያው ከተማ የተጠራውን ሰልፍም ጭምር ነበር ያገደው ። እርምጃው ድጋፍም ተቃውሞም ገጥሞታል ።
እገዳው አደጋን ለመከላከል የተወሰደ እርምጃ ነው በሚል ድጋፍ የቸሩት እንዳሉ ሁሉ የሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚፈቅደውን ሃሳብን በነፃ መግለፅን ማገድ ነው የሚል ወቀሳም የሰነዘሩበት አሉ ። ዶክተር ለማ ክልከላውን የሚቃወሙትን አስተያየት ነው የሚጋሩት ።
ስደተኞች በብዛት ወደ ጀርመን መግባታቸውን የሚቃወመው ፔጊዳ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው 12 ተኛ ሰልፍ 25 ሺህ ሰዎች ተገኝተዋል ። የንቅናቄው ደጋፊዎች መበራከት ትኩረት ስቧል ።ከዚሁ ጋር በዚህችው ከተማ የዛሬ ሳምንት ካሌድ ኢድሪስ ባህሬይ የተባለ አንድ ወጣት ኤርትራዊ በስለት ተገድሎ መገኘቱ ሲያነጋግር ከርሟል ። ፖሊስ ግድያው በመጣራት ላይ መሆኑን አስታውቋል። በከተማይቱ በውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ይህን መሰሉ ጥቃት ማስጋቱ አልቀረም ። ዶክተር ለማ መፍትሄው ያለው በሃገሪቱ ህግ ዘንድ ነው ይላሉ ።
በዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እምነት የፔጊዳ ንቅናቄ ጠንክሮ የሚዘልቅ አይሆንም ።በዚህ ሳምንት ሰኞ በድሬስደን የፔጊዳ ሰልፍ ቢታገድም ከዓላማው እንደማይደናቀፍ አስታውቋል ።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ