1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለም የፊናንስ ጉባዔ ዋዜማ

ረቡዕ፣ ኅዳር 3 2001

የዓለም የፊናንስ ጉባዔ በፊታችን ቅዳሜ ዋሺንግተን ላይ ይካሄዳል። ጉባዔው እንዲጠራ መንስዔ የሆነው ዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች ክስረትና በዚሁ ሳቢያ የተደቀነው የኤኮኖሚ ቀውስ አደጋ ነው።

https://p.dw.com/p/Ft7S
ቻይና በንግዱ ዓለም
ቻይና በንግዱ ዓለምምስል AP

ችግሩን ለመፍታት ዓለምአቀፉን ሥርዓት ሥር-ነቀል በሆነ መልክ የመለወጡ ሃሣብ ባለፉት ሣምንታት ከመቼውም በላይ ሲነሣ ነው የቆየው። ለመሆኑ ጉባዔው ለዚሁ ለውጥ ጥርጊያ ከፋች ሊሆን ይበቃል ወይ? የታዳጊዎቹ ሃገራት ጥቅምስ የመጠበቁ ዕድል እስከምነው ነው? የዓለምን የኤኮኖሚ ሥርዓት ከዘመኑ ሁኔታ አጣጥሞ የመለወጡ ሃሣብ ሲነሣ በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባይሆንም ባለፉት ዓመታት የአሁኑን ያህል አስፈላጊነቱ ጎልቶ የታየበት ወቅት የለም። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሃያላን መንግሥታት ተጽዕኗቸው የሰፈነበትን የዓለም ኤኮኖሚ ሥርዓት ዕውን ካደረጉ ወዲህ የንግዱ፣ የገበያው፣ የፊናንሱ፤ በአጠቃላይ የሁሉም ነገር ሂደት ዘዋሪዎች ሆነው ቆይተዋል።
ችግሩን በቁጥጥር ሥር ማዋሉም እንደዛሬው የሚከብዳቸው አልነበረም። ይሁንና ዛሬ ቻይናን፣ ሕንድንና ብራዚልን የመሳሰሉት ሃገራት በተፋጠነ ዕድገት ችላ የማይባሉ ሆነው ከተገኙ ወዲህ ተጨባጩ ሁኔታ በጣሙን ነው የተለወጠው። በእጣት የሚቆጠሩት የበለጸጉ ቀደምት መንግሥታት የዓለምን የኤኮኖሚ ዕጣ ለብቻቸው የሚወስኑበት ጊዜ እንዳይመለስ ሆኖ አልፏል። በግልጽ ያከተመለት ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ከሰላሣኛዎቹ ዓመታት የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ወዲህ ሃያል የሆነውን የወቅቱን የፊናንስ ቀውስ ለመጋተር ቻይናን የመሳሰሉት አገሮች ተሳትፎ ቁልፍ ጉዳይ የሆነው።
በፊታችን ቅዳሜ ዋሺንግተን ላይ በሚካሄደው የዓለም የፊናንስ ጉባዔም ቀደምቱን የበለጸጉ መንግሥታትና እነዚሁኑ በፍጥነት የሚራመዱ ሃገራት የጠቀለለው የ G-20 ወይም የቡድን-ሃያ ስብስብ መሪዎች በአንድ ላይ መቀመጣቸው ያስፈለገውም ለዚህ ነው። ሃቁ ይህ ሲሆን በዓለም ኤኮኖሚ ሥርዓት ላይ ወሣኝ ለውጥ ለማስፈን ፍላጎቱና ብቃቱ መኖር-አለመኖሩ ብዙም አስተማማኝ አይደለም። በቤት ባለቤቶች የብድር ችግርና በቀደምት ባንኮች ክስረት የፊናንሱ ቀውስ በተቀሰቀሰባት በአሜሪካ ብሄራዊው ሸንጎ ቀውሱን ለማስታገስ የ 700 ሚሊያርድ ዶላር በጀት ቢመድብም የውስጥ ችግርን ከመታገል አልፎ የዓለም ኤኮኖሚ ሥርዓትን በመጠገኑ አኳያ ቁርጠኝነት መኖሩ በውል አልተከሰተም።
ምናልባት በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የአስተዳደር ዘመን ይህን ያጤነ አዲስ ፖሊሲ ይሰፍን እንደሆን ወደፊት የሚታይ ነው። ፕሬዚደንት ቡሽ በበኩላቸው ለምሳሌ አውሮፓውያን በዓለምአቀፉ የፊናንስ ገበዮች ላይ ለውጥ ለማስፈን ያላቸውን ዕቅድ ተቃውመዋል። በቅዳሜው ጉባዔ ላይም ይህንኑ ሃሣብ ይዘው እንደሚቀርቡ ነው የሚጠበቀው።

“የመንግሥት ሚና ውሱን እንደሆነ ይቀጥላል። የሚወሰዱት ዕርምጃዎች ነጻውን ገበያ ለማስወገድ ሣይሆን ለማዳን የተወጠኑ ናቸው”

አውሮፓውያን በአንጻሩ የወቅቱ ቀውስ ወደፊት እንዳይደገም በዓለምአቀፍ ደረጃ በፊናንስ ገበዮችና ባንኮች ላይ ቁጥጥር እንዲሰፍንና ለዚሁም የጋራ መርህ እንዲኖር ይፈልጋሉ። ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም የክትትልና ወደፊት ተመሳሳይ ቀውስ ሲያንዣብብ ቀድሞ የማስጠንቀቅ የበለጠ ሚና ሊኖረው ይገባል ባዮችም ናቸው። ግን የአውሮፓ ሕብረት በጉባዔው ላይ አንድ ሆኖ ለመቅረብ መቻሉ እስከምን ድረስ ነው? ሰሞኑን እንደታየው ቢቀር የመንግሥታቱን የቁጥጥር ሚና መጠን በተመለከተ ልዩነት መከሰቱ አልቀረም።

የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ኒኮላይ ሣርኮዚይ በበኩላቸው የኤውሮ ምንዛሪ ተገልጋይ ሃገራት የኤኮኖሚ አስተዳደር የሚል አስተሳሰብ ይሰነዝራሉ። ይህ ደግሞ በብዙዎች የምንዛሪው ተገልጋይ ባልሆኑት የሕብረቱ መንግሥታት ዘንድ የመገለል ስሜትን ሊቀሰቅስ የሚችል ነው የሚመስለው።, እና አንድ-ወጥ አቁዋም አለ ለማለት አይቻልም። ሣርኮዚይ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ብራስልስ ላይ ከተካሄደው የሕብረቱ መሪዎች ስብሰባ በኋላ እንዳስረዱት ከሆነ አውሮፓውያኑ በዋሺንግተኑ ጉባዔ የሚሰየሙት አንድነት-ልዩነትም እንደያዙ ነው።

“በአውሮፓ የኤኮኖሚ ፖሊሲ ረገድ አንድ አቁዋም መያዙ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉም የሚስማሙበት ነገር ነው። ግን መስማማት ማለት ሁሉም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ሁኔታው ለሁላችንም አንድ ዓይነት አይደለም። እርግጥ ሁሉም በአንድ መንገድ መራመድ ይኖርባቸዋል። ይህ ዛሬ የደረስንበት ውሣኔ፤ የ 27ቱ ዓባል ሃገራት ፍላጎት ነው”

እንግዲህ የሚፈለገው አቅጣጫ አንድ፤ አካሄዱ ግን የተለያየ መሆኑ ነው። አውሮፓውያኑ ለማንኛውም ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን አጉልተው ለማሣየት መጣራቸው የማይቀር ነው። ምክንያቱም የጀርመን መንግሥት አፈ-ቀላጤ ኡልሪሽ ቪልሄልም እንደሚሉት የወቅቱ የፊናንስ ቀውስ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም።

“ለኛ ዋናው ነገር ለወቅቱ ቀውስ ትክክለኛውን ምላሽ መስጠቱ ነው። ስምምነት በሚደረስባቸው ዕርምጃዎች የወቅቱን መሰል የፊናንስ ገበያ ቀውስ እንዳይደገም ማድረግ መቻል ይኖርብናል”

በአውሮፓም ከሞላ-ጎደል ትኩረቱ ያመዘነው የፊናንሱን ቀውስ በማለዘቡ ላይ ይመስላል። ከዚህ አንጻር ለዓለም የኤኮኖሚ ሥርዓት ለውጥ ተገቢውና የሚፈለገው ጥርጊያ ይከፈታል ብሎ ማሰቡ ጥቂትም ቢሆን የሚያዳግት ነው። በሌላ በኩል የፊናንሱ ቀውስ የደቀነው የኤኮኖሚ ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አሜሪካ ከለየለት ቀውስ አፋፍ ላይ ስትሆን በኤውሮው ምንዛሪ ክልልም የአውሮፓ ኮሚሢዮን እንደሚገምተው የመጪው 2009 ዓ.ም. አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት 0,1 ከመቶ የሆነች ዕድገት ሊያሳይ ቢችል ነው።
ሌላው ቀርቶ ባለፉት አሠርተ-ዓመታት የዕድገት ተዓምር ስትባል የቆየችው ቻይና እንኳ በመጪው ዓመት አሥርና ከአሥር በመቶ በላይ በሆነ ዕድገቷ መቀጠል እንደማትችል ተረድታዋለች። ከስምንት እስከ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት ብቻ ነው የምትጠብቀው። ቀውሱ ምዕራብ-ምሥራቅ ብሎ የሚለይ አልሆነም። ይህ ደግሞ መፍትሄ ፍለጋውን የጋራ፤ የዓለም ኤኮኖሚ ሥርዓትንም ከተለወጠው ሁኔታ ጋር አጣጥሞ በአዲስ መልክ ማቀናጀቱን ይበልጥ አጣዳፊ፤ ወሣኝም ያደርገዋል።

የዓለም የኤኮኖሚ ልዕልና ማዕከል ቻይናን በመሳሰሉት አገሮች ዕድገት ከቀድሞ ቦታው አሸግሽጓል። በመሆኑም በመፍትሄ ፍለጋው ረገድ እነዚህ ሃገራት ቀውሱን ለመግታት በሚደረገው ጉባዔ መሳተፋቸው ግድና አስፈላጊም ነው። ይሁንና የዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ሥርዓት ተሃድሶ በዚሁ መልክ ማቀናጀቱንና ድርሻውንም እንደ ክብደቱ መጠን መለወጡን ግድ ያደርገዋል። በዚህ በምዕራባዊ ጀርመን የቦሁም ከተማ የፖለቲካ መምሕር የሆኑት ፕሮፌሰር ጉ-ሹዌይ እንደሚሉት የወቅቱን የፊናንስ ቀውስ ለመፍታት በተለይ እነዚህ ሃገራት ያከማቹት ሃብት የግድ የሚፈለግ ነው።

“በመጀመሪያ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት አገሮች ግዙፍ የገንዘብ ክምችት አላቸው። በተለይ ቻይና በውጭ ምንዛሪ ክምችት በዓለም ላይ ዋነኛዋ ናት። በሁለተኛ ደረጃ እርሷና ሕንድ ወይም ብራዚል አጽናፋዊ በሆነው የዓለም ኤኮኖሚ ላይ ሰፊ ድርሻ አላቸው። እና ለጉባዔው መጋበዛቸውም ተገቢ ነው። ምናልባት ወሣኝ ለሆነ መፍትሄ አስተዋጽኦ ላያደርጉ ይችላሉ። ሆኖም በኢኦንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የፊናንሱን ገበያ ለማዳን የግድ ይፈልጓቸዋል”

ይህ ደግሞ ከፖለቲካ አንጻር ያለ ማካካሻ የሚሆን ነገር አይደለም። በሰፊው ሃብት ያከማቹት ቻይናን ወይም ሩሢያን የመሳሰሉት ሃገራት በጥቂት ሃይላን መንግሥታት ተይዞ ከቆየው የኤኮኖሚ ሞኖፖል ድርሻ መሻታቸው የማይቀር ነው የሚመስለው። ቻይናን ካነሣን አይቀር የአገሪቱ አመራር ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ያስከተለውን የውጭ ንግድ ማቆልቆል ለመታገል የአገሪቱን የኤኮኖሚ ዘርፍ ከ 500 ሚሊያርድ ዶላር በሚበልጥ በጀት ለመደጎም ወስኗል።

ዕቅዱ በአንድ በኩል የራስን የውጭ ንግድ በማዳበሩ ላይ ያለመ ሲሆን በሌላ በኩልም በፊናንስ ገበያው ላይ የሚፈሰው ገንዘብ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ሃገራት የቻይናን ምርቶች በነበረው መጠን መግዛት እንዲቀጥሉ የዕርጋታ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኗል። ከዚህ አንጻር በፊታችን ሣምንት የዋሺንግተን ጉባዔ የቻይና አካሄድ ተጨባጩን ሃቅ ያገናዘበ እንደሚሆን በብራስልስ የአውሮፓ የጥናት ማዕከል ባልደረባ የዶር/ አክሰል ቤርኮፍስኪም ዕምነት ነው።

“ይህም ማለት በምዕራቡ ዓለም የተከሰተው ቀውስ በቻይናም የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አለው ማለት ነው። ቻይና ደግሞ እንደማስበው ይህን ተገንዝባዋለች። እናም በስብሰባው ላይ እንደወትሮው እጣት በመቀሰር ፈንታ ተባባሪ ሆና ትቀርባለች ብዬ ነው የማስበው”

በምን መጠን? ጠብቆ መታዘቡ ይመረጣል። ሌላው በዋሺንግተኑ የፊናንስ ጉባዔ ዋዜማ እየጎላ የመጣው የታዳጊ ሃገራት ጥቅም የመረሳት ስጋት ነው። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በፊናንሱ ቀውስና በኤኮኖሚ ማቆልቆል አደጋ ተወጥረው በሚገኘት በአሁኑ ሰዓት የልማት ትብብሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለቱ በዕውነትም ያዳግታል። የልማት ዕርዳታው እንደተፈራው ማቆልቆሉ ካልቀረ ደግሞ ብዙዎች አገሮች ከተባበሩት መንግሥታት የሚሌኒየም ግቦች መድረስ መቻላቸው ከንቱ ተሥፋ ሆኖ መቅረቱ ነው።
ይሁንና የፈረንሣይ የልማት ሚኒስትር አላን ዦያንዴት በዋሺንግተኑ የዓለም የፊናንስ ጉባዔ ላይ ለታዳጊዎቹ ሃገራት ጥቅም እንደሚቆሙ ሰሞኑን ተናግረው ነበር። የታዳጊ ሃገራትን ችግር ሳንጠቀልል ዓለምአቀፉን የፊናንስ ዘርፍ ስለመጠገን ልናወራ አንችልም ነው ያሉት። የሚፈለገው የፊናንስ ለውጥ ድህነትን መቀነሱንም ዒላማው ያደረገ ቢሆን ምንኛ በበጀ!