1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዐረቡ ዓለም የቀጠለው የህዝብ መነሣሣት ፣

ሰኞ፣ መጋቢት 12 2003

ሊቢያ፣ በጦር አኤሮፕላኖችና በሚሳይል በመደብደብ ላይ ሳለች፣ ፈንጠር ባሉት የዐረብ አገሮች፣ የመን፤ ባህሬይንና ሶሪያ «በቃ!» የሚል የህዝብ ቁጣ አይሎ ቀጥሎአል።

https://p.dw.com/p/RBC9
ምስል AP

በግብጽና በቱኒሲያ ጉብኝት ለማድረግ፤ ዛሬ ካይሮ የገቡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን፣ በዚህ ፣ ዓለም አቀፉ አጽናፋዊ የኤኮኖሚ ትሥሥርና ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች ባቀራረበው ዓለም፣ መሪዎች፤ ህዝብ ምን እንደሚጠይቅና ፤ ያለውንም ጽኑ ፍላጎት ተገንዝበው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሂደቶችን መከታተል ብቻ ሳይሆን፤ ፍትኅና ርትእ ፣ ነጻነትና ፤ ዴሞክራሲያዊ አመራር የተጠሙ አገሮችን ህዝብ የመርዳት ኀላፊነት አለበት ሲሉ ነው ያስገነዘቡት።

Jemen Demonstration gegen die Regierung in Sanaa
ምስል picture alliance/dpa

ተክሌ የኋላ----

ከ 32 ዓመት በላይ በሥልጣን ላይ የሚገኙትና ካለፈው ጥር ወር አንስቶ ፣ ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያስጨንቃቸው የሰነበተው ፤ የየመኑ ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳሌህ፣ ባለፈው ዓርብ፣ ሰንዓ ውስጥ በዩኒቨርስቲው አደባባይ 52 የተቃውሞ ሰልፈኞች እንዲገደሉ በማድረጋቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን፤ እርምጃውን ፤በጥብቅ ነው ያወገዙት። ባለፈው ዓርብ በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የተፈጸመውን ግድያ የተመለከቱ አንድ የዓይን ምሥክር እንዲህ ነበረ ያሉት።

«ይህ ግድያ ነው ዓለም በመላ ይህን በትክክል እንዲመለከተው ምን እየተደረገ እንዳለ እንዲያይ ጥሪ እናቀርባለን።»

Syrien Proteste Demonstration
ምስል AP

ፕሬዚዳንት አሊ አብደላ ሳሌህ ትናንት የሚንስትሮች ም/ቤት እንዲፈርስ ካደረጉ ወዲህ፤ በዛሬው ዕለት ከታወቁት ጥቂት ጀኔራሎች መካከል፤ ጀኔራል አሊ ሞህዜን ኧል አህማር የተባሉት የብረት ለበስ ክፍለ-ጦር አዛዥ ከሌሎች 2 ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኮንኖች ጋር «አብዮቱ»ን ተቀላቅዬአለሁ ሲሉ ካስታወቁ ወዲህ፤ በመዲናይቱ በሰንዓ ፣ የፕሬዚዳንቱ ቤተ-መንግሥት፤ ማዕከላዊው ባንክና የመከላከያ ሚንስቴር መ/ቤት በታንኮች ተከበው በመጠበቅ ላይ ናቸው። ጀኔራል አሊ ሞህሴን ኧል አህማር ፤ «እየተባበሰና እየተወሳሰበ በመሄድ ላይ ያለው ውዝግብ ፤ አገሪቱን ወደ ብጥብጥና የእርስ-በርስ ጦርነት እየገፋት ነው» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የምዕራብ የመን ጦር አዛዥ፣ ሙሐመድ አሊ ሞሆሴንም ተመሳሳይ እርምጃ ነው የወሰዱት። ሁለቱም ጀኔራሎች የፕሬዚዳንቱ ጎሣ አባላት ናቸው።

3 ሚንስትሮችና ዲፕሎማቶች፤ በሶሪያ የየመን አምባሳደር የነበሩት አብደል ወሃብ ታዋፍ ፤ እንዲሁም የየመን ደቡባዊ ጠ/ግዛት፣ አደን፤ አገረ- ገዥ፣ አህመድ ቓታቢ ፤ በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የተወሰደውን የጭካኔ እርምጃና አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታ በመቃወም ሥልጣናቸውን ለቀዋል።

የየመን ወታደሮችና ዛይዲ ሺዓ አማጽያን በሰሜናዊው የአገሪቱ ከፊል ባደረጉት ውጊያ 20 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። ውጊያ የተካሄደው፣ ኧል ጃዋፍ ወደተሰኘው ጠ/ግዛት በሚስገባው በር የሚገኝ ስልታዊ ጠቀሜታ ያለውን ወታደራዊ አውታር ለመቆጣጠር ሲሆን፤ «ሁቲስ» በሚል ሌላ መጠሪያ የሚታወቁት አማጽያን በእጃቸው እንዳስገቡ ናቸው።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት (HRW)ባለፉት 3 ቀናት የሶሪያ ባለሥልጣናት ፈላጭ ቆራጩን አገዛዝ በመቃወም ፣ ከመዲናይቱ ከደማስቆ በስተደቡብ 100 ኪሎሜትር ራቅ ብላ በምትገኘው ዳራ በተሰኘችው ከተማ ፣ አደባባይ የወጡ ሰዎችን ከሚገባ በላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ 5 ሰዎች ገድለዋል በማለት በጥብቅ ነው የነቀፈው። የሶሪያ መንግሥት ፤ ዜጎቹ ፍልጎታቸውን ስላንጸባረቁ ለመግደል የማያመነታ መሆኑን አሳይቷል ሲሉ የነቀፉት በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪቃ፣ የ HRW ሥራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ Sarah Leah Whitson ናቸው። በቱኒሲያና በግብፅ የተከናወነው ለውጥ ያስቀናቸው ሶሪያውያኑ የተቃውሞ ሰልፈኞች፤ ነጻነታቸው እንዲመለስላቸውና 48 ዓመታት እንደጸኑ የሚገኙ የአስቸኳይ ሁኔታ አዋጆችም ሆኑ ደንበኞች እንዲሻሩ ነው የሚጠይቁት።

የባህሬይን ንጉሥ፤ ሐማድ ቢን ኢሣ ኧል ከሊፋ፣ በባህሬይን ላይ በውጭ ኃይል የተዶለተው ሤራ ከሽፏል በማለት፤ በሱኒ ሙስሊም መሪዎች ከሚገዙት ጎረቤት አገሮች ፀጥታ ለማስከበር ተብሎ የገቡትን ወታደሮች አመሥግነዋል። ከ 60 ከመቶ በላይ የባህሬይን ዜጎች የሺዓ እስልምና ዘርፍ ተከታዮች ሲሆኑ፣ በኢራቅና ሊባኖስ ሺዓዎችን የምትደግፈው ኢራን፤ ለተባበሩት መንግሥታት ስሞታ ከማቅረቧም፣ በሱኒዎች የምትመራው ስዑዲ ዐረቢያ ጦሯን ከባህሬይን እንዳድታስወጣ ጠይቃለች።

«ዌፋቕ» የተባለው የባህሬይን ሺዓዎች ፣ የተቃውሞ ፓርቲ፣ በሳምንቱ ማለቂያ ላይ ተይዘው የታሠሩት ሰልፈኞች በነጻ ከተለቀቁ ፣ ከሱኒዎቹ መንግሥት ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛነቱን ገልጿል ነው የተባለው። ባለፈው ሳምንት ማለቂያ ላይ በተፈጠረው ሁከት 4 የተቃውሞ ሰልፈኞችና 3 ፖሊሶች መገደላቸው ታውቋል። ዌፋቅት እንዳስታወቀው፣ 2 ቀናት በእስር ላይ የቆየ ጎልማሣ ተደብድቦ ሀኪም ቤት ውስጥ በትናንቱ ዕለት ህይወቱ አልፋለች። መንግሥት ሐሰት ሲል አስተባብሏል። አብደል ኧል ማውዳ የተባሉት በባህሬይን ፓርላማ የህዝብ እንደራሴ እንዲህ ይላሉ--

« ይህ ፍጹም የለየለት ውሸት ነው። ትልቅ ውሸት በሚነገርባት ባህሬይን ውስጥ ነው የምንኖረው። የሆስፒታል ዘገባ ተቀይሮ ነው የሚቀርበው። በዚያ ለዋውጠው ነው የሚያቀርቡት። መንግሥት ፣ ሆስፒታሎች እንደሚዋሹ ነው የሚያስረዳው።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ