1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኻርቱም "አንድ ጦር፤ አንድ ሕዝብ" የሚሉ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጡ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 6 2014

በሱዳን ጦሩን የሚደግፉና የጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ መንግሥትን የሚቃወሙ ሰልፈኞች ዛሬ አደባባይ ወጡ። ተቃዋሚዎቹ "አንድ ጦር፤ አንድ ሕዝብ" እንዲሁም "ጦሩ ዳቦ ያመጣልናል" የሚሉ መፈክሮች አሰምተዋል። ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር የምታደርገው ሽግግር "የከፋ ቀውስ" እንደገጠመው አስጠንቅቀው ነበር 

https://p.dw.com/p/41lwG
Sudan | nach Putschversuch | Premierminister Abdalla Hamdok
ምስል AFP/Getty Images

የሱዳን ጦርን የሚደግፉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ተቃዋሚዎች ዛሬ ቅዳሜ በኻርቱም አደባባይ ወጡ። በዋና ከተማዋ በሚገኘው ፕሬዝደንታዊ ጽህፈት ቤት ደጃፍ የተሰበሰቡ ተቃዋሚዎች "የረሐብ መንግሥት" ያሉት የጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ አስተዳደር ከሥልጣን እንዲለቅ ጥሪ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። የተቃውሞ ሰልፉ የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር አል በሺርን ከሥልጣን ለማውረድ ያመጹ ቡድኖችን ጨምሮ ለጦሩ በሚወግኑ የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች ስብስብ አንድ አንጃ የተጠራ ነበር።

"ወታደራዊ መንግሥት ያስፈልገናል። አሁን ያለው መንግሥት ፍትኅ እና እኩልነት ሊያመጣልን አልቻለም" ሲሉ በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፉት የ50 አመቱ አባውድ አሕመድ ተናግረዋል። ተቺዎች ሰልፉ በጦሩ እና በጸጥታ ኃይሎች ግፊት የተደረገ እና የቀድሞው መንግሥት ናፋቂዎች የተካተቱበት ነው ሲሉ ይወነጅላሉ። 

ተቃዋሚዎቹ መንግሥት እንዲበተን የሚጠይቁ መፈክሮች ይዘው የታዩ ሲሆን "አንድ ጦር፤ አንድ ሕዝብ" እንዲሁም "ጦሩ ዳቦ ያመጣልናል" ሲሉ መደመጣቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

Sudan Karthoum | Anti-Regierungsproteste
ከሁለት ሳምንታት ገደማ በፊት ወታደሮች እና ሲቪል ፖለቲከኞች በጥምረት የመሠረቱትን የሽግግር መንግሥት የሚቃወም ሰልፍ ተካሒዶ ነበር። ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

ኢናም መሐመድ የተባሉ የኻርቱም ነዋሪ የቤት እመቤት "ሰላማዊ ተቃውሞ ለማሰማት ነው የወጣነው። ወታደራዊ መንግሥት እንፈልጋለን" በማለት ከአባውድ አሕመድ የተስማማ አስተያየት ሰጥተዋል።

ከተቃውሞው በፊት ማንነታቸው ያልተለየ ታጣቂ ቡድኖች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዙሪያ ለጸጥታ ጥበቃ የተዘጋጁ ማገጃዎችን ማንሳታቸውን እና ፖሊስ እና የጸጥታ ኃይሎች ወደ ሥራ እንዳይሔዱ መከልከላቸውን የኻርቱም ግዛት አስተዳዳሪ አይማን ኻሊድ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። 

ትናንት አርብ የሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ አገራቸው ወደ ሲቪል አስተዳደር የምታደርገው ሽግግር "የከፋ ቀውስ" እንደገጠመው አስጠንቅቀው ነበር። 
የጠቅላይ ምኒስትሩ ማስጠንቀቂያ የተደመጠው በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2019 ዓ.ም. በተደረሰ የሥልጣን መጋራት ሥምምነት አገሪቱን በሚመሩት ሲቪል ፖለቲከኞች እና ወታደራዊ ሹማምንት መካከል በተፈጠረ ጥልቅ መከፋፈል ምክንያት ሱዳን በተቸገረችበት ወቅት ነው።

Libyen Sirte | Früherer sudanesischer Präsident | Omar Hassan al-Baschir
በአገሪቱ የታየው መከፋፈል በተለይ የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ኦማር አል-በሺር ከሥልጣን ያስወገደውን ተቃውሞ የመራው የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች የተባለ ጥምረት ክፉኛ ጎድቶታል።ምስል Photoshot/picture alliance

በአገሪቱ የታየው መከፋፈል በተለይ የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ኦማር አል-በሺር ከሥልጣን ያስወገደውን ተቃውሞ የመራው የነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች የተባለ ጥምረት ክፉኛ ጎድቶታል።
"አብዮታዊ እና የለውጥ ኃይሎች በብሔራዊ ፕሮጀክት ላይ መስማማት ሳይችሉ መቅረት" የቀውሱ ዋንኛ መሠረት እንደሆነ ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ ትናንት አርብ በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ባሰሙት ንግግር ገልጸዋል። ሐምዶክ እንዳሉት ይኸም በሲቪል ፖለቲከኞች ውስጥ እና በአገሪቱ ጦር ውስጥ እንዲሁም በሲቪል ፖለቲከኞቹ እና በጦሩ መካከል በተፈጠረ ልዩነት የተከሰተ ነው። 

ቀውሱን ጠቅላይ ምኒስትሩ ሱዳን ኦማር አል-በሺር ከሥልጣን ተወግደው ሽግግር ከጀመረች ወዲህ ከገጠማት ሁሉ "የከፋ እና አደገኛ" ብለውታል። 
ከየነጻነት እና የለውጥ ኃይሎች ተገንጥሎ የወጣ አንድ አንጃ ከዋናው የሲቪል ፖለቲከኞች ስብስብ የተለየ ጥምረት በቅርቡ መስርቷል። ይኸው ተቃዋሚ የሲቪል ፖለቲከኞች አንጃ በመጪዎቹ ቀናት የተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሔዱ ጥሪ አቅርቧል። 

Sudan Khartum | Straßensperre von Soldaten nach Putschversuch
መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም ተሞክሮ ከሸፈ ከተባለው መፈንቅለ-መንግሥት በኋላ የሽግግር መንግሥቱን በሚመሩት ሲቪሎች እና የጦር ሹማምንት መካከል ያለው ክፍፍል መበርታቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።ምስል Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

የሱዳን መንግሥት ኦማር አል-በሺር ይመሩት ከነበረው መንግሥት ግንኙነት አላቸው የተባሉ ወታደራዊ መኮንኖች እና ሲቪል ፖለቲከኞችን ከከሰሰበት እና መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም ተሞክሮ ከሸፈ ከተባለው መፈንቅለ-መንግሥት በኋላ የሽግግር መንግሥቱን በሚመሩት ሲቪሎች እና የጦር ሹማምንት መካከል ያለው ክፍፍል መበርታቱን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በርካታ ሲቪል ፖለቲከኞች ጦሩን ተጠያቂ ቢያደርጉም ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ ግን ለመፈንቅለ-መንግሥቱ "ሸክሙን አይሸከምም" ሲሉ ተከላክለዋል።  

የመንግሥት ተቃዋሚዎች የቀይ ባሕር ወደብን ከዘጉ በኋላ ሱዳን የመሠረታዊ ሸቀጦች እጥረት ጭምር ይፈትናት ይዟል። ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ ለአስርት አመታት በቆየ "መገፋት እና መገለል" ተፈጠረ ያሉትን የምሥራቅ ሱዳን ቀውስ ለመፍታት ቃል ገብተዋል።