1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኮቪድ 19 ክፉኛ የተጎዳው የአፍሪቃ መገናኛ ብዙኃን

ሰኞ፣ ግንቦት 10 2012

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው ጫና በርካታ መገናኛ ብዙሃን አፍሪቃ ውስጥ ህልውናቸው ጥያቄ ላይ ወድቋል። ስለተሐዋሲው አስፈላጊና የተጣሩ መረጃዎች ከመገናኛ ብዙሃን በሚጠበቁበት በዚህ ወቅት አብዛኞቹ ለጋዜጠኞች የሚከፍሉት በጀት እያጠራቸው መምጣቱ ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/3cQOg
The Fate of Media Freedom and Media Development in East Africa
ምስል DW/N. Markgraf

የኮሮና ወረርሽኝ በአፍሪካ መገናኛ ብዙኃን ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

በኮቪድ 19 ክፉኛ የተጎዳው የአፍሪቃ መገናኛ ብዙሃን

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው ጫና በርካታ መገናኛ ብዙሃን አፍሪቃ ውስጥ ህልውናቸው ጥያቄ ላይ ወድቋል። ስለተሐዋሲው አስፈላጊና የተጣሩ መረጃዎች ከመገናኛ ብዙሃን በሚጠበቁበት በዚህ ወቅት አብዛኞቹ ለጋዜጠኞች የሚከፍሉት በጀት እያጠራቸው መምጣቱ ዘርፉን እየጎዳው መሆኑን ይናገራሉ።  የዶቼ ቬለዋ ክርቲና ክሪፓል የጻፈችውን ሸዋዬ ለገሠ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች።አገልግሎታቸው ከምንግዜውም በበለጠ በሚያስፈልግበት ወቅት አፍሪቃውያን ጋዜጠኞች ኑሮ ከብዶባቸዋል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተለው የኤኮኖሚ መዳከም ምክንያት በርካታ የግል መገናኛ ብዙሃን ህልውናቸውን ለማቆየት ግብግብ ይዘዋል። በደህናው ጊዜ ለናይጀሪያው የግል ዓለም አቀፍ የራዲዮ ጣቢያ ዳንዳል ኩራ የሚሠሩት ዘጋቢዎች በወር 100 ዶላር ገደማ ያገኙ ነበር። አሁን ራዲዮ ጣቢያው በያሉበት ያሉ ዘጋቢዎቹን ቁጥር ቀንሶ ሲያበቃ ሌሎች ተጨማሪ ሠራተኞቹንም ከቤታቸው እንዲቆዩ ለማሳሰብ መገደዱን አሳውቋል።«57 የሚሆኑ ሠራተኞች ናቸው ያሉን። 20ዎቹ ወደሥራ እንዳይመጡ የነገርን ሲሆን ቤታቸው ለሚቀመጡት መክፈል የምንችለው የደመወዛቸውን 20 በመቶ ብቻ ነው።» ይላሉ የጣቢያው ዳይሬክተር ፋሩክ ዳልሃቱ። ዳንዳላ ኩራ በሰሜናዊ ናይጀሪያ በቀውስ የምትናጠው ቦርኖ ግዛት ማይዱጉሪ ከተማ የሚገኝ ጋዜጠኛ ነው። የራዲዮ ጣቢያው በሰሜናዊ ናይጀሪያ ብቻ ሳይሆን የቦኮ  ሃራም መንቀሳቀሳ በሆኑት በቻድ፣ ካሜሮን እና ኒዠር በርካታ አድማጮች ያሉት ነው። ዳንዳል ኩራን ችግር ውስጥ የከተተው ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ተቋማት ቁጥር መቀነስ ነው። ከኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ስጋት በፊትም ቢሆን ከሰሜን ናይጀሪያ የሚገኘው የማስታወቂያ ገቢ ከጠቅላላ የሀገሪቱ የማስታወቂያ በጀት 20 በመቶ ብቻ የሚሸፍን ነበር። የጣቢያው ዳይሬክተር ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት አሁን ማስታወቂያ የሚባል ነገር የለም። በዚህም ምክንያት ቋሚ ወጪ የሆኑትን የሠራተኛ ደመወዝና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ማሟላት ከብዷቸዋል።የላይቤሪያው የሴቶች ድምፅ ጋዜጣም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ነው። የሠራተኞቻችንን ደመወዝ መክፈል ከልብ እንፈልጋለን የሚሉት የጋዜጣው አሳታሚ ሄለን ናህ ሳሚ፤ እነሱምጋ የማስታወቂያ ገቢ መንጠፉን ይናገራሉ።«ማስታቂያውን በእኛ በኩል የሚያስነግረው መንግሥት እንኳን ይህን ትቷል። መክፈል ያልቻሉት የጋዜጣው ዕዳ አለባቸው።»የላይቤሪያው ትሩዝ ኤፍኤም የዜና አርታኢ ኦስካር ሙልባህ ደግሞ ራዲዮ ጣቢያው የኤኮኖሚ አቅሙ ከኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ መከሰት አስቀድሞም የተዳከመ መሆኑን ነው የሚናገረው።«ላለፉት ስድስት ወራት ገደማ ደምወዜን አልወሰድኩም። ላይቤሪያ ውስጥ ጋዜጠኝነት ለሙያው ባለ ፍቅር ብቻ የሚከወን ነው።»ሙልባህ ችግሩ እውነተኛ እና ጥንቃቄ የተላበሰ የዜና ዘገባ በሚያስፈልግበት በኮቪድ ቀውስ መባባሱንም ያመለክታል።  የኒዠር መገናኛ ብዙሃንም ሌላው በማስታወቂያ ድርቅ መመታቱን የግል ራዲዮና ቴሌቪዥን  የሆነው ሳራውኒያ ጣቢያ ዋና አርታኢ ዑማሩ ጋዶ ይናገራል። ሰዎችን በቤታቸው የገደበው መመሪያ ለቀቅ ማለት ሲጀምር ግን ተስፋ አለ ባይ ነው። አንፋኒ የተሰኘው የግል ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ ጃዲ ማሀማዱ በበኩላቸው የኒዠር መንግሥት ሥራቸውን ለመቀጥ እየታገሉ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንን ለመርዳት ጣልቃ መግባት አለበት ይላሉ።«ወጪዎችን በራሳቸው እየከፈሉ የሚገኙ ካምፓኒዎችን መቼም እንዲዘጉ አትነግራቸውም። ያለምንም ጥርጥር ይረዳሉ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ።»የዳንዳል ኩራ ዳይሬክተርም ርዳታ ይገኛል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ፤ የገንዘብ ርዳታው ግን ከናይጀሪያ መንግሥት መምጣቱን አይቀበሉም።«የገንዘብ ርዳታ ከተሰጠን በዳንዳል ኩራ የአርትኦት ሥራ ገለልተኛነትን ጥያቄ ላይ የሚጥል የሆነ አካል እጁን ላያስገባ ይችላል።»እንደእሳቸው እምነትም ባለሥልጣናት መገናኛ ብዙሃኑን መደገፍ ከፈለጉ ለትምህርትም ሆነ ከወረርሽኙ ጋር ለተገናኘ ማስታወቂያ ክፍያ ቢያደርጉ ይሻላል። ይህንንም ቢሆን ክፉኛ ይጠራጠራሉ። በሚያገኙት የገንዘብ ድጎማ ምክንያትም አንዳንድ የራዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሀገሪቱ ፖለቲከኞች ቁጥጥር ሥር መሆናቸውንም ለዶቼ ቬለ ጠቁመዋል። እንዲህ ባለው ድጎማም የጣቢያቸውን የገለልተኝነት ነፃነት ማጣት እንደማይሹም አመልክተዋል።የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት መገናኛ ብዙሃኑ በባለሙያዎች ፍልሰት እየተጎዱ ነው። ላይቤሪያ ውስጥ ቀድሞ በዘርፉ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞች ወደ መንግሥት ዘርፎች የህዝብ ግንኙነት ወይም በሌላ የሥራ መስክ እየገቡ የባሰ ፕረሱን እያዳከሙት መሆኑ እየተነገረ ነው።  ኮቪድ 19 በናይጀሪያ የነዳጅ ገበዋያው ላይ ሳይቀር ተፅዕኖውን ክፉኛ በማሳረፉ መገናኛ ብዙሃኑ የገጠማቸው ተግዳሮት በቅርቡ ይቀላል ማለት እንደሚከብድ ጋዜጠኞቹ ለዶቼ ቬለ አመልክተዋል።